Monday, June 24, 2024
HomeEthiopian Newsየማንነት ብዙነትና ወሳኝ ማንነት

የማንነት ብዙነትና ወሳኝ ማንነት

Tessema Simachew

ከስማቸው ተሰማ

የኤርትራን ነጻ አገር መሆን ተከትሎ በጥቂት አመታት ውስጥ የኢትዮጵያና የ ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር በብዙ አስር ሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ኤርትራ ተባረሩ፤ ከተባረሩት ውስጥ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች ተወልደው ካደጉባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጋር ያላቸው ምስ ስል እና ቅርበት በዘር ሀረግ ከሚዛመዱት ከ ኤርትራ ማህበረሰብ ጋር ካላቸው ምስ ስል የበለጠ እንደነበር ግልጽ ነው። ከ ኢትዮጵያ ለመፈናቀላቸው ኤርትራዊ ማንነታቸው ምክንያት ይሁን እንጅ፣ በሄዱበት ኤርትራ ደግሞ ብዙ ርቀት አቋርጠው ከመሄዳቸው ጋር በሚያያዝ መልኩ “አምቼ” መባላቸው የማንነታቸው አንዱ መገለጫ ሊሆን ችሏል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲኖሩ ኤርትራዊነታቸው የጎላውን ያህል፣ ኤርትራ ውስጥ ሲኖሩ ከ ኢትዮጵያ መሄዳቸው ወሳኙ የማንነታቸው መገለጫ ሆኗል።

በተመሳሳይ መልኩ ዜግነት ስለሌላቸው ብቻ ተወልደው ካደጉበት አገር በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ወላጆቻቸው አገር እንዲሄዱ የሚጠየቁ ሰዎች ተመሳሳይ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ባደጉበት አገር ከሌላ አገር ከመጡ ወላጆች መወለዳቸው ጎልቶ የሚታይ በመሆኑ ወሳኝ ማንነታቸው እሱ እንደሆነ ተደርጎ ቢቀርብም እውነተኛ አገራቸው ወደተባለው አገር ሲሄዱ ግን ካደጉበት አገር የወረሱት ቋንቋ፣ ባህል ፣ የ አመለካከት እና ሌሎችም ዝንባሌዎች ጎልተው ይወጣሉ። ከልጅነታቸው ጀምሮ አሜሪካ አድገው በወንጀልና በህገወጥነት ምክንያቶች ወደ ሌሎች አገራት እየተባረሩ ያሉ ሰዎችን በዜግነት አሜሪካዊ ባይሆንም ከ አገሪቱ ጋር ባላቸው ቁርኝት የተነሳ ተባረው በሚሄዱበት ቦታ እንደ አሜሪካ ስደተኞች እንደሚኖሩ ለማሳየት Daniel Kantstroom የተባለ ስድተኞችን በተመለከቱ ህጎች ዙሪያ የታወቀ ምሁር እነዚህን ሰዎች “the new American Diaspora” በማለት ይገልጿቸዋል።

ከዚህ ጋር አያይዘን በተለያዩ ጊዚያት ወደ እስራ ኤል የተጓዙ ቤተ እስራኤላውያንንም ማንሳት ይቻላል። ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ ጎልቶ የሚታየው የማንነታቸው መልክ ከ እስራ ኤል ጋር ያላቸው ቁርኝት ቢሆንም እስራ ኤል ውስጥ ደግሞ ከቆዳቸው ቀለም ጀምሮ ኢትዮጵያዊ መነሻቸው የማንነታቸው ጉልህ መገለጫ የሚሆንበት ብዙ አጋጣሚ አለ።

ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ማንነት አንድና ወጥ እንዳልሆነ ከማሳየት አልፈው በተለያዩ ሁኔታዎች ጎልቶ የሚወጣው የ አንድ ሰው የማንነት ገጽታ የተለያየ ሊሆን እንደሚችል የሚያመላክቱ ይመስለኛል። ማንነት፣ ምስ ስልና ልዩነትን፣ ርቀትና ቅርበትን፣ እንዲሁም መዛመድንና አለመዛመድን መሰረት አድርጎ የሚደረግ ክፍፍልንና መቧደንን የምንረዳበት፣ የምንገልጽበትና የምንተነትንበት ጽንሰ ሃሳብ ነው። የምንመሳሰልባቸው እና የምንለያይባቸው፣ የምንራራቅባቸውና የምንቀራረብባቸው፣ የምንዛመድባቸውና የማንዛመድባቸው ነገሮች በጣም ብዙ ስለሆኑ የተለያዩ ማንነቶች ይፈጥሩልናል። የወላጅ፣ የ አያት፣ ቅድመ አያት ወዘተ መጋራት ቤተሰብነትና ዝምድናን ይፈጥራል፤ በጾታ መመሳሰል የጾታ ማንነትን ይፈጥራል፤ በሃይማኖት መመሳሰል የሃይማኖት ማንነትን ይፈጥራል፤ በቋንቋ መመሳሰል፣ የቋንቋ ማንነትን ይፈጥራል፤ በ አገር መሳሰል፣ የ አገር ማንነትን ይፈጥራል፣ በ አህጉር መመሳሰል አህጉራዊ ማንነትን ይፈጥራል፤ በፖለቲካ አቋም መመሳሰል ፣ የፖለቲካ ማንነትን ይፈጥራል፤ በቆዳ ቀለም መመሳሰል፣ የቀለም ማንነትን ይፈጥራል። አንድ ሰው ልብስ ደራርቦ እንደሚለብሰው ሁሉ ከ እነዚህን የተለያዩ የማንነት መገለጫዎችንም ደራርቦ ይይዛል። ከነዚህ ሁሉ ማንነቶች ጀርባ ሰው በሰውነቱ ከሁሉም ሰዎች ጋር የሚጋራው ሰብ አዊ ማንነት አለው።

ከዚህ በመነሳት ስለ ማንነት የተወሰኑ ምልከታዎችን ማድረግ የምንችል ይመስለኛል። አንድ ሰው ካሉት ተደራራቢ ማንነቶች ውስጥ አስበልጦ የሚያየውን ሊወስን ይችላል። ነገር ግን ይሄ ውሳኔ ከሚኖርበት ከባቢ ተጽእኖ ነጻ መሆን የሚችል አይደለም። ይሄ የሆነበት አንዱ ምክንያት የሚኖርበት ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ከባቢ አጉልቶ የሚያያቸው የማንነት አይነቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ነው። ራሱ አስበልጦ የሚያየው የማንነቱ ቀለም እና ሌሎች ሰዎች አጉልተው የሚያዩት የማንነቱ ቀለም አንድ ላይሆን መቻሉም ሌላው ገዳቢ ነገር ነው። ለምሳሌ ባሁኑ ሰ አት የ አለም ህዝብ በዋነኝነት የተከፋፈለው እና የተቧደነው በ አገራት እንደመሆኑ አንድ ግለሰብ ከሁሉም አስበልጬ የማየው ማንነቴ ሰው መሆኔን ነው በማለት ብቻ በፈለገው አገር ሄዶ የመኖር እድል አያገኝም። ወይም ደግሞ ከ እምነት ከማይመሳሰሉኝ ኢትዮጵያዊያን በእምነት የሚመሳሰሉኝ የሳውዲ ሰዎች ይበልጡብኛል ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ በህገ ወጥነት ወደ አገርህ ሂድ ተብሎ ከመባረር አይድንም፤ከላይ መግቢያው አካባቢ በተጠቀሰው አይነት ሰዎች ጥርስ ነቅለው ካደጉበት አገር ወደ “አገራችሁ” ሂዱ እየተባሉ የሚባረሩበት እውነት ይህ አለም የሰዎች ሳይሆን የ አገሮች ነው እንድንል ያስገድደናል።

ከሁሉም የማስበልጠው የ ትግራይ ማንነቴን ነው፣ በዚህም ከ ትግርኛ ተናጋሪ ኤርትራውያን ጋር ያለኝ ዝምድና ይበልጥብኛል የሚል ሰው፣ በ ኤርትራ ሲኖር በሌሎች ዘንድ ከትግራይ መምጣቱ የጎላ የማንነቱ መገለጫ ተደርጎ እንዳይታይ መከላከል ይከብደዋል። ከሁሉም የማስበልጠው አማራ መሆኔን ነው የሚል አንድ የጎጃም አካባቢ ሰው፣ ወደ ጎንደር ቢሄድ የጎጃሜነት ማንነቱን ደጋግሞ እንዲያስታውስ የሚያደርግ ከባቢ ውስጥ ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል። ከሁሉም የማስበልጠው ማንነቴ ጎጃሜ መሆኔን ነው የሚል ሰው ወደ ኦሮምያ ወይም ደቡብ ክልል ቢሄድ ጎልቶ የሚጠቀስለት ማነነቱ አማራነቱ ሊሆን እንደሚችልም መገመትም ይቻላል።

ከሌላ አገር በስደት ከመጡ ወላጆች ተወልደው የሚያድጉ ህጻናት ከሚገጥማቸው ማንነት ነክ ፈተና አንዱ ባደጉበት አገር ከሌላ አገር ጋር ያላቸው የትውልድ ቁርኝት እነሱ ባይፈልጉት እንኳን በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ጎልቶ የሚታይ መሆኑ ነው። እነሱ ተወልደው ካደጉበት አገርና አካባቢ ያገኙትን ማንነት ማጉላት ቢፈልጉ እንኳን በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ወላጆቻቸው የመጡበትን አካባቢ እና ከዚያም የሚቀዳውን ማንነት ደጋግመው ያስታውሷቸዋል። ማንነት መመሳሰልንና ልዩነትን መሰረት የሚያደርግ እንደመሆኑ በ አንድ አካባቢ ውስጥ አንድን ሰው ወይም ቡድን በ አካባቢው ካሉ ሰዎች ወይም ቡድኖች ለየት የሚያደርገው የማንነቱ ቀለም ጎልቶ ይወጣል። በነጭ ወረቀት ላይ በነጭ ቀለም ቢጻፍ እንደማይታይ ሁሉ፣ በነጭ ወረቀት ላይ ከነጭ በተለየ ቀለም ሲጻፍ ጎልቶ እንደሚወታው ሁሉ በማንነት ውይይት ውስጥ ጎልቶ የሚወጣው የሚያመሳስለው ሳይሆን የሚያለያየው ነገር ነው። እስካሁን ባለው ሀተታ ወሳኝ ሊባል የሚችለው ማንነት በምርጫ እና በሁኔታዎች ሊለያይ እንደሚችል ግልጽ የሆነ ይመስለኛል። ስለዚሁ ነጥብ አንድ ተጨማሪ አስተያየት በመስጠት ይህን ጽሁፍ ላጠቃልል።

ማንነት ተኮር ግጭቶች ስለሚነሱበት እውነት እያሰብን የ አለምን ሁኔታ ብናስተውል በየ አካባቢው ያሉ የተለያዩ አይነት ልዩነቶች፣ ከህዝቦች ታሪካዊ መስተጋብር ጋር ተዳምረው ስር በሰደደ እና በከረረ ፉክክር፣ በጥላቻ እና በግጭት ውስጥ ጎልተው እናስተውላለን። በቋንቋ አንድ በሆኑ እንደ ሱማልያ ባሉ አገራት የጎሳ ልዩነት ጎልቶ ሊወጣ ይችላል። በደቡብና ሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው ልዩነት መሰረቱ ርእዮታለማዊ ነው። እስልምናን በመከተል ተመሳሳይ የሆኑ ማህበረሰቦች፣ በተለያዩ ሴክቶች መካከል ባለው ልዩነት እና ፉክክር ተጠምደው ወደ ግጭት ያመራሉ። ቀደም ባለው ጊዜ በሶሻሊዝም አስተሳሰብ የተቃኙ የኢትዮጵያ አንዳንድ ወጣቶች ከብሄር ወይም ከቋንቋ ዝምድና ይልቅ መደባዊና ርእዮተ አለማዊ ወገንተኝነት የበለጠ ትርጉም የሚሰጣቸው ነገር እንደሆነ መረዳት ይቻላል። የእያንዳንዱ አገር ወይም አካባቢ ሁኔታ ራሱን በቻለ የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊና ሌሎችም ዝርዝር እውነታዎች የሚወሰን አካሄድ ያለው በመሆኑ፣ በቋንቋ ይሁን በርዕዮተ አለም፣ በጎሳ ይሁን ወይም በአካባቢ፣ በሃይማኖት ይሁን ወይም ሌላ ልዩነቶችና በ አንድ አካባቢ ባለ ግጭት ግልጽ የሆነ የምክንያትና የውጤት ግንኙነት መፍጠር ይከብዳል። ቢያንስ ግን በየሁኔታው ከሚያመሳስለው ነገር ይልቅ የሚያለያየው ነገር ጎልቶ እንደሚወጣና ወሳኝ ተደርጎ እንደሚወሰድ መመልከት ይቻላል። በተጨማሪም የሚጎላው ማንነት እያንዳንዱ ግለሰብ ወይም ቡድን ለራሱ በሚመርጠው ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች ሰዎች ወይም ቡድኖች ጋር በሚያደርገው መስተጋብር ከእነሱ በሚለይበትና እንዲጎላ በሚፈልጉት እንዲሁም በሌሎች ታሪካዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ሊወሰን እንደሚችል መረዳት ይቻላል። በተለያየ ሁኔታ ጎላ ብሎ ስለሚወጡ ወይም ስለሚቀርቡ ማንነቶች በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተነሱ አንዳንድ ነጥቦችን በቀጣይ ጽሁፎችም በተሻለ ቅርበት ለማየት እሞክራለሁ። ቸር ይግጠመን።

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here