ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በመኖር የሚታወቁት የሮማዎች ወይም ጂፕሲዎች ጎዳና ዳር ሰብሰብ ብለው ተቀምጠው ማየት የኢትዮጵያ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ማየት የሚፈጥረው ስሜት ይፈጥራል። ጄኔቫ ከተማ ውስጥ ለምሳሌ የሚያዘወትሯቸው የተወሰኑ ቦታዎች አሉ። ላጋር ባቡር ጣቢያው አካባቢ (በነገራችን ላይ እኛም ላጋር ለማለት ብለን ሳይሆን አይቀርም አዲስ አበባ ውስጥ ለገሃር የሚል ሰፈር የኖረን)፣ ፕላን ፓሌ የሚባል አካባቢና አውግስቲን የሚባል አካባቢ አያቸዋለሁ። መጀመሪያ አካባቢ በጣም እገረም ነበር። ባለቤት የሌለው ውሻና ድመት በማይታይበት አገር፣ ቤት የሌለው ሰው ማየት እንዴት አያስገርም? ሱፐር ማርኬት መውጫ ላይ ቁጭ ብለው ሳንቲም የሚለምኑ አሮጊት እናቶችንም አስተውዬ አውቃለሁ።
ታዲያ አንድ ቀን ከአንድ ሃበሻ ጓደኛዬ እነዚህ ሰዎች እኮ ጥቁር በጣም ነው የሚንቁት የሚል አስተያየት ሰማሁ። እኔ ለነሱ እያዘንኩ እነሱ እኔን ይንቃሉ ማለት ነው? የሚለው ሃሳብ ራሱ አሳቀኝ። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የ አፍርካ አገራት የሚመጡ ወንድሞቻቸውን የሚያዩበትን መንገድ አሰብኩና በራሳችንም ፈገግ አልኩ።
***************************************
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እያለን ደግሞ አንድ ናይጄሪያዊ መምህር ደብረማርቆስ ፕሪፓራቶሪ ትምህርትቤት (ድብዛ) መጥቶ ሂሳብ ትምህርት እንዲያስተምረን ተመድቦልን ነበር። ሉክ ይባላል። በእምነቱ ካቶሊክ ይመስለኛል። ገና ወደ ክፍል ሳይገባ የሚቀባው ሽቶ መምጣቱን ይነግረን ነበር። በ አካባቢው ከ አስተማሪዎች በማይጠበቅ መንገድ በጣም ነጻ ነው። እኛን ለማዝናናትና ለመቀራረብ እንዲረዳው የዳንስ እንቅስቃሴዎችን ሳይቀር አድርጎልን ያውቃል። አክሮባት እንደሚችል ነግሮናል። ክፍል ውስጥ ስለነበርን ነው እንጅ አክሮባት ሰርቶ ሊያሳየንና ሊያዝናናን እንደሚችልም እገምታለሁ። አንዴ ደግሞ አዲስ አበባ ደርሶ ሲመጣ ኮሌጅ የሚባል በአምሳ ሳንቲም የሚገዛ እስክርቢቶ በብዛት ገዝቶ መጥቶ ለእያንዳንዳችን አድሎን ያውቃል። ለመቀራረብ ብዙ ጥረት ያድርግ እንጅ እንደ አካባቢው መምህራን “ኮስተር” ብሎ አያስተምርም ነበር። መጽሃፉ ላይ የተሰራውን ምሳሌ አብሮ ያሳየናል። መልመጃ ላይ የተቀመጡትን ጥያቄዎች ግን ለመስራት ብዙም ፍቃደኛ አይደለም።ያው እኛ ስለማይችል ነው ብለን ወስነናል። ክፍል ውስጥ ደጋግሞ የሚጠቀመው ቃል ‘ቆንጆ’ የሚለውን የአማርኛ ቃል ይመስለኛል። ክፍል ውስጥ ያሉ ሴት ተማሪዎችን በሙሉ ቆንጆ ሲል ነው የሚውለው።
በማስተማር ላይ የሚያሳየው ቸልታ፣ በሳቅ እና በጨዋታ የሚያሳልፈው ጊዜ ወዘተ በተማሪዎች ዘንድ ትንሽ መከፋትን ፈጠረ። ወደ አስተዳደሩ እየተሄደም ክስ መክሰስ ተጀመረ። አፍሪካዊ ሆኖ፣ ጥቁር ሆኖ፣ ከሌላ አህጉር እንደመጣ ነጭ በብዙ እንግድነት መታየቱ ሳያንስ፣ ተማሪዎች እያጉረመረሙበት መሆኑን ሲረዳ፣ አንድ ቀን በከፍተኛ ስሜት ስለ አንድ መሆናችን፣ በክርስትና ስለመመሳሰላችን ስብከት የሚመስል ንግ ግር ሲያደርግልን አስታውሳለሁ። በተዘዋዋሪ ዘረኞች ናችሁ እያለን የነበረ ይመስለኛል። ያም ቢሆን የብዙ ተማሪዎችን ስሜት አልቀየረውም። በወቅቱ እያሳሳቀ ከማያስተምረው አቶ ሉክ፣ ፈገግ እንኳን የማይሉልንን ኢትዮጵያውያን አስተማሪዎች እንደምንመርጥ ግልጽ ነበር። የተማሪዎቹ ትግል ተሳክቶ አቶ ሉክ በኢትዮጵያዊ አስተማሪ ተቀየረ።
************************************
አንድ ኬንያዊ የቀድሞ የክፍል ጓደኛዬ በዚህ አመት መጀመርያ ለስራ ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ብሎ ነበር። በቅርቡ ሳገኘው አዲስ አበባ ሂደህ ምን ታዘብክ አልኩት። የተለመደው የመጀመሪያው አስተያየት ተከተለ-የሴቶቹ ውበት። ሁለተኛው “ማህበረሰቡ በጣም ኮንሰርቫቲቭ” ነው አለኝ። ሶስተኛው፣ የስልክ ኔትወርክ ችግር ነው። አራተኛው የጠቀሰልኝ ነገር በባቡር መስመር ግንባታው ምክንያት ስላለው የትራፊክ መጨናነቅ። ማህበረሰቡ ኮንሰርቫቲቭ ነው ስትል ምን ማለትህ ነው አላልኩትም።የገባኝ መስሎኛል። እኔ ራሱ ነጻነቱን እና ለሰው ያለውን ፍቅር ስለማውቅ ኢትዮጵያ ሂዶ የሚያገኘውን እያንዳንዱን ሰው ቀርቦ ለማናገር በሚያደርገው ጥረት ሊገጥመው የሚችለውን ምላሽ እያሰብኩት ስለነበር ምን ማለትህ ነው ብዬ ገፍቼ መጠየቅ አልፈለኩም። በቅርቡ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኬንያታ ኢትዮጵያ ቤተ መንግስት ውስጥ የተደረገለትን አቀባበል፣ ሃይለማርያም ሰለሜ ሲጨፍር፣ እሱ፣ ሃይለማሪያም እና ቴድሮስ አድሃኖም እስክስታ ሲሞክሩ የሚያሳዩ ፎቶዎች ፌስ ቡክ ላይ ለጥፎ ከ አንዳንድ ሰዎች የነበረውን ምላሽ አስታወስኩ። ኬንያታ ያደረገው ነገር በእርግጠኝነት የኢትዮጵያ ባለ ስልጣናትን እንደሚያስከፋቸው መገመት ይቻላል። እኔም ብሆን ነገሩን በደስታ እና በፈገግታ መቀበልን ተምሬው ነው እንጅ አብሮኝ ያደገ ጠባይ አይመስለኝም።
**************************************
ከላይ በግል ገጠመኞቼ ላይ ተመርኩዤ የጻፍኩትን ሃተታ መለስ ብላችሁ ብታዩት ፣ ጽሁፌ የተለያዩ ማንነትን(identity) በሚገልጹ ቃላት እና በብዙ ጠቅላላ ድምዳሜዎች(generalizations) የተሞላ ነው።
ሮማነት፣ እናትነት፣ አሮጊትነት፣ ሀበሻነት፣ ጥቁርነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አፍሪካዊነት፣ ናይጀርያዊ መሆን፣ ካቶሊክነት፣ ተማሪነት፣ አስተማሪነት፣ ሴት መሆን፣ ክርስትያን መሆን፣ እነዚህ ሁሉ ወይ የዘር ወይ የሚና(role) ፣ ወይ የእድሜ፣ አልያ የቀለም፣ ወይም አገራዊ፣ አህጉራዊ ወይም ሃይማኖታዊ ማንነትን የሚገልጹ ናቸው። እነዚህን የማንነት ገላጮች በመጠቀም ብዙ ድምዳሜዎች ተሰጥተዋል። እነሱን በተመለከተ የተወሰኑ ነጥቦች ጠቁሜ እና አንዳንድ ጥያቄዎችን አንስቼ ይህንን ጽሁፍ እቋጫለሁ።
በመጀመሪያ ጄኔቫ ውስጥ ጎዳና ላይ የማያቸው ሰዎች ሁሉ ሮማዎች መሆናቸውን ራሳቸውን ጠይቄ አላረጋገጥኩም። ሌሎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። ነገር ግን በመልካቸው፣ ባለባበሳቸው እነሱ እንደሆኑ ገምቻለሁ። በመሰረቱ በጣም በምሽት አንድ አካባቢ ሰብሰብ ብለው ስላየኋቸው እንጅ ሁሉም እዛው ጎዳና ላይ እንደሚያድሩ አላረጋገጥኩም።
ሁለተኛ፣ ሮማዎቹ ጥቁር ይንቃሉ የሚል ድምዳሜ ከጓደኛዬ ልስማ እንጅ እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የተበቃበትን ምክንያት ምን እንደሆነ አልጠየኩም። የሚንቁ ቢኖሩ እንኳን ከመካከላቸው ምን ያህሉ እንደሆኑ አላውቅም።
ሶስተኛ፣ “ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የ አፍርካ አገራት የሚመጡ ወንድሞቻቸውን የሚያዩበትን መንገድ አሰብኩና በራሳችንም ፈገግ አልኩ” የሚል አገላለጽ ተጠቅሚያለሁ። ሆን ብዬ ነው የተጠቀምኩት። “አንዳንድ ኢትዮጵያውያን” ብል ኖሮ የተሻለ ድምዳሜ እንደሚሆን ግልጽ ነው። አንድ ከጋንቤላ የሚመጣ ኢትዮጵያዊ እና ከናይጄሪያ የሚመጣ አፍሪካዊ በኢትዮጵያ የደጋ ክፍሎች ተመሳሳይ አቀባበል ሊኖረው እንደሚችል እገምታለሁ። ስለዚህ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ አይነት አገላለጽ የምንጠቀምባቸውን ጽሁፎች ሲያነቡ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያዊ እና ኢትዮጵያዊነት ሲሉ የሚያወሩት ስለ አማራ እና ስለ ትግሬ ባህል፣ አኗኗር እና አመለካከት ነው የሚለውን ቆየት ያለ አስተያየት ያጠናክርላቸዋል።
አራተኛ ከናይጄሪያ የመጣው ሉክም ሆነ ኬንያዊው ጓደኛዬ ኢትዮጵያ መጥተው የሚሰጡት ዋናው አስተያየት ስለ ሴቶቹ ቁንጅና መሆኑም ሌላው ችግር ነው። እነሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያዩትን ማህበረሰብ በመልኩ የሚመዝኑት ከሆነ፣ እነሱን የሚያያቸው ማህበረሰብ ከእሱ በመጠኑ ለየት በማለታቸው እንደ እንግዳ ቢያያቸው ምኑ ይገርማል? የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሆነን ናይጄሪያዊውን ሉክ በሌላ ኢትዮጵያዊ አስተማሪ እንዲቀየርልን የፈለግነው ዘረኛ ስለነበርን ነው ወይስ እሱ ጥሩ የሂሳብ አስተማሪ ስላልነበረ? ሌሎች ጥያቄዎችንም ማንሳት ይቻላል።
ለማጠቃለል ያህል፣ አስቀድሞ የተሰጠው ሃተታም ሆነ እሱን ተከትሎ የተነሱት ነጥቦች እና ጥያቄዎች ስለ ማንነት ምንነትና ስለ ማንነት ስለምናወራበት መንገድ የጠቆሙት ቁምነገር እንዳለ ተስፋ አደርጋለሁ። በቀጣይም ስለ ማንነት፣ ስለ አካባቢ ማንነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊ ማንነት፣ ስለ ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ሌሎች የ አካባቢ ብሄርተኝነቶች እና ስለ ተዛማጅ ጉዳዮች ከራሴ ተሞክሮ እና ፍላጎት በመነሳት ተከታታይ ጽሁፎችን ለማቅረብ እሞክራለሁ። ቸር ይግጠመን።