Thursday, August 18, 2022
HomeSliderጎሰኝነት ሌላ ፤ ተራማጂነት ሌላ

ጎሰኝነት ሌላ ፤ ተራማጂነት ሌላ

በኦህዴድ በኩል ሃያ ሚሊዮን ብር ወጥቶበት በተመረቀው የአኖሌ ሃውልትም የወያኔ ትሮጃን ፈረስ ከሆነው ኦህዴድ በላይ ወያኔ እንደሚደሰትበት በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ባለራዕኖቹ ወያኔዎች ሃውልቱን ባይፈልጉት ኖሮ እንደማይሰራም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በህዝቦች መካከል በተለይ በአማርኛ እና በኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል የመቀራረብ ስሜት የሚፈጥር ፤ ይልቁንም ከየትኛውም የኢትዮጵያ ቋንቋ ተናጋሪዎች በበለጠ የተዋለዱ ኢትዮጵያውያኖች እንደሆኑ የሚያሳይ ሓውልት ቢሆን ኖሮ ወያኔ እንደማይፈልገው እና እንደማይሰራ (ጭራሽ ሃያ ሚሊየን ብር ወጥቶ! ) አምናለሁ። ይሄንን ሃውልት ከወያኔ እና ዲያስፖራ ካሉ የዘር እልቂት ጠንሳሾች ሌላ የሚፈልገውም የሚጠቀምበት ያለ አይመስለኝም። በትርጉም ደረጃ የጎሳ ፖለቲካን አስከፊነት ከማመላከት ያለፈ የሚናገረው ነገር የለም። የህግ ስርዓት ቢኖር ኖሮ የቅድመ ጀኖሳይድ ምልክትነቱ ታውቆ፤ በችግር ደረጃ ሳይገዝፍ መቀየር ያለበት ጉዳይ ነበር። ከሃውልቱም ጀርባ ያሉ ሰዎች በሃውልቱ ማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት ምን እንደሆነ ፤ በእርግጥም ሃውልቱ ያሰቡትን ነገር የሚያስተላልፍ መሆኑን እና መጥፎ አንድምታ እንደማይኖረው ማስረዳት ይጠበቅባቸው ነበር – ህግ እና ስርዓት ቢኖር ኖሮ! ሃውልቱ የምንሊክ ዘመነ መንግስት ከኦሮሞ ህዝብ ጋር የነበረውን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉስ ያሳያል? ሌላ ጥያቄ ነው።

ሌላው ዓለም ወደ ኋላ ዘወር እያለ ብርሃን እየወሰደ ወደ ፊት በሚገሰግስበት ሰዓት ጉሰኝነትን ከተራማጂነት እና ከአብዮተኝነት መለየት የተሳናቸው ወደ ኋላ ብቻ እያዮ ወደፊት መሄድ አልቻሉም። ወደ ኋላም ዞረው የሚያዮት ጥቁር ነጥብ ብቻ ነው። ሌላ ነገር ማየት አይፈልጉም፤ አይችሉምም ጎሰኝነት-አይናቸውን ጋርዶታል::

ሰሞኑን በዓለም ዓቀፍ ዜና ማስራጫዎች ሶስት ክስተቶች ትኩረቴን ስበውታል። ሶስቱም ሁነቶች ተራማጂነትን (በእኔ ትርጉም!)የሚያንጻባርቁ ስለሆነ ፤ ለጎሳ ፓለቲከኞች እና እየደከሙበት ስላለው የጎሳ ግጭት እና የተበታተነች ኢትዮጵያን የመፍጠር ፕሮጀት የሚሰጠው ትምህርት ያለ ስለሚመስልኝ ላስታውሳቸው እፈልጋለሁ።

ዛሬ የሩዋንዳ ህዝብ ብዛት አድጎ 11 ሚሊየን አካባቢ ደርⶃል። የዛሬ 20 ዓመት 800 000 ያህል ሩዋንዳውያን ሁለት ወር በሚሆን ጊዜ ውስጥ እንደ በግ በአስከፊ ሁኔታ ታርደዋል። አራጆቹን ለማስቆም ከስደተኛ ካምፕ ጫካ የገባው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር የዘር ፍጂቱን ካስቆመ በኋላ የዘር ፖለቲካ ማቀንቀን በህገ መንግስት የተከለከለበት ስርዓት መስርቷል። ሰሞኑን የዘር ፍጂቱን 20ኛ ዓመቱን ሲያስቡም ያ ሰቆቃ እንዳይመለስ እና ሩዋንዳ የሁሉም ሩዋንዳውያን እንደሆነች አጽንኦት በመስጠት ነው። እንዲህ ያደርጉት በጎሳ አንጻር የታረዱት ጎሳ ወገኖች ናቸው። የጥላቻ ሃውልት ተክለው በቀልን አላብሰለሰሉም። ተራማጂነት! ሌላውን ችግራቸውን ለመፍታት ( የኢኮኖሚ እና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ)እንደሚጠቅማቸው አስባለሁ።

ሕንዶች 815 ሚሊየን መራጭ የሚሳተፍበትን በዓለም ግዙፍ የተባለለትን ምርጫ ከጀመሩ ዛሬ ሶስተኛ ቀናቸው ነው። ምርጫው ላይ የሚሸናነፉበት አጀንዳ ሙስናን በመዋጋት እና በስራ ዕድል ፈጥራ ላይ ያጠነጥናል። ገዢው የህንድ ብሔራዊ ኮንግረስ ፖርቲ ህንድ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዥ ነጻ ከሆነችባቸው 67 ዓመታት ውስጥ 54 ዓመታት ያህል ያስተዳደረ ፓርቲ ነው። ቁም ነገሩ እሱ ሳይሆን የቤተሰብ አገዛዝ እና ሙስና የነገስበት ስርዓት የመራ ፓርቲ መሆኑ ነው። እንግሊዝ በህንዶች ላይ የተከለችው መርዝ እና በህንድ ማህበረሰብ ሃይማኖታዊ መሰረት ያለው የሚመስለው ማህበራዊ ጭቆና ህንድን አልበታተናትም። ከመናቃቸው የተነሳ እንኳንስ ከሌላው ማህበረሰብ ሊጋቡ ቀርቶ የማይነኩ የሚባሉ ህንዳውያን ነበሩ። ጽንፈኛ የሆነ የፓለቲካ መንገድ አልያዙም። ስለ ምርጫው ያላቸው ቀናዒነት፤ ተስፈኝነታቸው ያስቀናል። ወደ ዘር እልቂት የሚያመራ ፓለቲካም በዘር ፓለቲካ የዳቆነ የፓለቲካ ሰይጣንም የላቸውም ህንዶች። የሸመቁት ኮሚኒስቶችም ሆኑ በሰላም እየተንቀሳቀሱ ያሉት ኮሚኒስቶችን የዘር ጥላቻ አጀንዳ የላቸውም። የናጋላንድ ሸማቂዎችም አጀንዳ የጎሳ ፓለቲካ አይደለም። ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍትህን ለማምጣት የዘር ፓለቲካ ርባና እንዴሌለው ተረድተዋል። ተራማጂነት ነው! በቅርቡ “ዘ ኢኮኖሚስት” በህንድ ምርጫ ላይ ያወጣው ዘገባ ስለ ህንድ የምርጫ አጀንዳዎች ጥሩ መረጃዎች አይቸበታለሁ።

በክሬሚያ የሆነው እና አሁን በዶኒየስክ እየሆነ ያለውም አይኑን ላልጨፈነ ሰው የሚናገረው ጉዳይ አለ። ክሬሚያ ከ60 ዓመት በላይ ተዋህዳት ከኖረችው ዮክሬን ተገንጥላ ወደ ራሺያ የሄደችብት ምክንያት ከሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪነት ጋር የተያያዘ አይመስለኝ። የዶኒየስክም የሰሞኑ ዓመጽ ከዚያ ጋር የተያያዘ አይደለም። ነገሩ የርዮተዓለም ጉዳይ ይመስለኛል። የተጋረጠባቸውን አደጋው ጥልቀት ተገንዝበውታል ፤ አቅማቸውንም ተገንዝበውታል። ዮክሬን ከራሺያ የበለጠ ጉልበተኛም አስፈሪም ሆና አይደለም። ነገር ግን የምትቀጥለዋ ዮክሬን የከዚህ በፊቷ ዮክሬይን እንዳልሆነች እና በዛም በኩል የሚመጣው የማንነት መመሰቃቀል ተረድተውታል። የተሻለ ያሉትን መፍትሄ የሚሆነውን ወስደዋል። የእኛ ሃገር የጎሳ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም የአፍሪካ ሃገሮች በጎሳ ግጭት እየተነከሩ በሄዱ ቁጥር ጣልቃ ገብነትን እና በጣልቃ ገበነት ስበብ የሚመጣውን ቀማኛ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ከአፍሪካ በተፈጥሮ ሃብት የታደሉ ከሚባሉት ጎንጎ አንደኛዋ ነች። የተፈጥሮ ሃብቷ ምን ጋበዘ-ከፖትሪስ ሉሙምባ ጊዜ ጀምሮ! ዛሬስ ጎንጎ ምንድን ናት?!ኮንጎ ሰላም አላት? የጎሳ ፖለቲካ ያለቅጥ ሚዛንን ያስታል። የጎሳ ፖለቲካ በሚመጣው ሳይሆን ባለፈው ጨለምተኝትን ማላበስ እና የሚመጣውን የማመሰቃቀል አዝማሚያ ይታይበታል። አብዮተኝነትም፤ተራማጂነትም አይደለም።

ድሜጥሮስ ብርቁ
ቲዊተር : @dimetros

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here