Tuesday, July 23, 2024
HomeSliderጎሰኝነት ሌላ ፤ ተራማጂነት ሌላ

ጎሰኝነት ሌላ ፤ ተራማጂነት ሌላ

የጎሳ ፖለቲካ ለስልጣን ሽሚያ የሚቀነቀን የስልጣን ተሻሚዎች (ስልጣን የያዙት ጠብቆ ለማቆያ እና ያልያዙት ለመያዣ) የፖለቲካ ጭምብል ሳይሆን ፤ ተራማጂነት ፤ የፍትሃዊነት ጥግ ፤ ለፍትህ የሚደረግ ትግል እና አብዮተኝነት እየመሰለ ነው። በመዋቅር ደረጃ አስተዳደራዊ እና የሜዲያ ሽፋን ስለተሰጠውም በዚሁ በጎሳ ፓለቲካ ስርዓት ውስጥ ተወልደው ላደጉ ፤ በተለይ በክልሎች ለሚኖሩ ወጣቶች መቀዣበር መፍጠሩ አልቀረም።

እንደሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች ሁሉ ከኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘው በወጣትነት የእድሜ ክልል ያለው የህብረተሰብ ክፍል ነው።በጣም አብላጫው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠር በመሆኑ ፤ አብዛኛውም ወጣት የሚኖረው በገጠር እና ትንንሽ ከተሞች እንደሆነ ለመናገር የስታስቲክ መረጃ ማገላበጥ አያስፈልግም።

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች ከናካቴው ደብዛው ሊጠፋ የደረሰው ነጻ ፕሬስ እንኳ ተጠቃሚ አይደሉም። አማራጭ ሃሳብ የማየት ዕድል የላቸውም። ስለሆነም ወደውም ሆነ በግድ ጠዋት እና ማታ የሚጋቱት የወያኔን እና ሌሎች ታዛዠ ፓርቲዎች የጎሳ ፖለቲካ ነው። የሚጋቱት የክልላዊነት እና የጎሰኝነት ስሜት ነው። በውጤቱ ኢትዮጵያዊነትን ከጎሰኝነት አሳንሶ ማየት ብቻ ሳይሆን ፤ በኢትዮጵያዊነት ላይ የጨለምተኝነት እና የጥላቻ አመለካካትም እየተገነባ እንደሆነ ለማንም የተደበቀ አይደለም ፤ በተለይ የማህበራዊ ድህረ ገጽ ለሚያዘውትር።

የኢትዮጵያን ታሪክ በጎሳ ፖለቲካ መነጸር መተርጎም ከተጀመረም ወያኔ በስልጣን ላይ የቆየውን ያህል እድሜ አስቆጥራል። ፖለቲካውን በጎሳ መነጸር እና በጨለምተኝነት ከማየት የተነሳ ኢትዮጵያዊነትን ከአንድ የቋንቋ ተናጋሪ ጋር አያይዞ ማየት ፤ እንደመጨቆኛ መሳሪያነትም እስከማየትም ተደርሷል። ስልጣን የያዘውም የጎሰኛ ቡድን ፤ ስልጣን ያልያዘውም የጎሰኛ ቡድን የሚፈራውም፤ የሚያጣጥለውም ኢትዮጵያዊነትን ነው። ኢትዮጵያዊነት ደሞ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ፖለቲካ ተደርጎ ተወስዷል።

ስልጣን ያልያዘውም የጎሰኛ ፖለቲካ ካምፕ ወጣቶችን ለጎሳ ፓለቲካ ጭፍራነት የሚጠቀም አዝማሚያ ይታያል። በየክልሉ ያሉ ወጣቶች የመንደሮቻቸው ልጆች ከውጭ ሃገር ሆነው በማህበራዊ ድህረ ገጽ የሚለቁትን የጎሳ ፖለቲካ መርዝ ከተቆርቋሪነት ስሜት የመነጨ ፤ ለፍትህ የሚደረግ ትግል አድርገው መውሰዳቸው አይቀርም፤ ጎሰኝነት የሚቀርብላቸው መልኩ ተቀይሮ በአዋቂነት ፤ በተራማጂነት፤ በአብዮተኝነት እና በጽድቅ መልክ ነውና። በዮኒቨርሲቲዎች ኔትወርክ ይዘረጋል። ወያኔ ጋር ከሚሰሩ የየጎሳ ፓርቲ ባለስልጣናት ጋርም የሚስጥር ግንኙነት ሊኖር ይችላል። በዚህም በዛም የጎሳ ፓለቲካ ነጋሪት ይመታል። ያ ሁሉ አልበቃ ብሎ በሙዚቃ የተቀናበረ የዘር ጥላቻ ቅስቀሳ የሚመስልም ነገር ይታያል። በታሪክ ጥቁር ነጥብ ተፈልጎም ሃውልት ተሰርቷል። የዛሬ ሃያ አመት ሩዋንዳ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን አሳዛኝ እልቂት የፈጠረው አይነት ድባብም በመጠኑ ይታያል።

በስርዓቱ ምክንያት የጎሪጥ የማይተያይ ፤ ቢያንስ በጥርጣሬ የማይተያይ ጎሳ አለ ለማለት አይቻልም። ሰሞኑን ነገሌ እና ቦረና የተለያየ ስለሆነ ነገሌ ከቦረና ተለይቶ ራሱን ችሎ እውቅና እንደሚፈልግ ፤ በዛም ምክንያት አታካራም ቢጤ እንደተጀመረም ሰማን። የጎሳ ፖለቲካ ከገመትነው በላይ አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ አስረግጦ ለመናገር ባለፉት ሁለት ዓመታት እንኳን የተስተዋሉ ክስተቶችን በጥሞና ማየቱ ይበቃል። ከሌላ ከሌላው የጎሳ ግጭት ምልክቶቹ በገጠር መንደሮች ፤ በዮኒቨርሲቲዎች ፤ በስታዲየሞች ታይተዋል ፤ በተደጋጋሚ።

ለሁለት እና ሶስት አስርት ዓመታት ከኖሩበት የገጠር መንደር ኢትዮጵያ ምድር ሳይሆን ልክ አረብ ሃገር እንደሆነው በባዕድ ሃገር እንደሰፈሩ ነገር እየተንከላፈቱ ፤እየተደበደቡ እንዲለቁ የተደርጉ ኢትዮጵያውያኖች አየን። ይሄም በአብዮተኝነት ስሜት የተደረገ ፤ የጎሳ ልሂቃን ምክንያታዊነት አይቶ እንዳላየ (ጮቤ እየረገጠም ይሆናል) ያለፈው ጉዳይ ነበር። መንግስትም መጀመሪያ የህገ-ወጥ ሰፈራ ውጤት አስመስሎ ሊያድበሰበሰው ሞከሮ ነበር።

ከመንደር ውጭም በየዪኒቨርሲቲ ካምፓሱ የሚነሱ የጎሳ ግጭቶች በተደጋጋሚ ተከስተዋል። ከትምህርት በኋላ ወደ ህብረተስቡ ገብተው የመስተዳድሩ አካላት የሚሆኑት ( አሁን ባለው አሰራር በየክልላችው) እነዚሁ ተማሪዎች ናቸው ፤መቸም የመንግስት ሰራተኛ ከህንድ ወይ ከቻይና አይቀጠር ነገር እንግዲህ። ዮኒቨርሲቲ ውስጥ ጎሳ ለይተው የተደባደቡ ተማሪዎች ነገ “በየክልላቸው” የኃላፊነት ቦታ ሲይዙ ለህብረተስቡ የሚያስተምሩት ምንድን ነው? የሚከተሉት ፖሊሲ ከአድሏዊነት እና የጎሳ ፓለቲካ ማራመጃ ከመሆን በምን ተዓምር ሊጸዳ ይችላል?

ስፖርታዊ ጨዋታዎች የጎሳ ጠብ ናሙና ማሳያነት ወደመሆን እየተቀየሩ ነው። በአዲስ አባባ ስታዲየም አልፎ አልፎ የሚከሰተውን ብንረሳው ፤ አንድ ወቅት ደብረዘይት የተከሰተውን ብንረሳው ፤ በቅርቡ በባህር ዳር በተካሄደው “የመላው ኢትዮጵያ” ጨዋታዎች የተከሰተው በፍጹም መረሳት የለበትም። በስታዲየም እንደሚፈጠር የተለመደ እና የጎሳ ፖለቲካ መገለጫ እንዳልሆነ አድርጎ ማየቱ ስህተት ከመሆኑም በላይ አይጠቅምም።

ራሱን የሳተ የተባለ የመንግስት ወታደር በባህርዳር 12 ሰው ከገደለ ዓመት እንኳን የሆነው አይመስለኝም። ያን ሰሞን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ላይ ያለ እፍረት ድርጊቱን የፈጸመው ወታደር የኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነው የሚል መንፈስ ያለው ዘገባ በማቅረባቸው የተፈጠረው ድባብ ጥሩ አልነበረም። እስከዛሬ ጥርት ባለ ሁኔታ ድርጊቱ እንዴት እና ለምን እንድተከሰተ ህዝብ የሚያውቅ አይመስለኝም። የባህርዳሩ ስታዲየም ብጥብጥም እንዲሁ የአማራ እና የኦሮሞ ብጥብጥ ከመምሰሉ በስተቀር እንዴት እና ለምን እንደተከሰተ ፤ ተዋናዮቹ እነማን እንደሆኑ በማያጠራጥር ሁኔታ የሚታወቅ ነገር ያለ አይመስለኝም። በተለይ በአማርኛ ተናጋሪ እና ኦሮሚኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን መካክል በፍጹም የማይጠፋ እሳት እንዲነሳ እንደሚፈለግ ብዙ አመላካች ነገሮች አሉ። ከላይ እንደገለጽኩት የወያኔ መንግስት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የኦህዴድ እጂ ብቻ አይደለም ያለበት። ተቃዋሚ ነን የሚሉ ጽንፈኛ የጎሳ ፓለቲከኞች ሌት ከቀን በመስራት የሚያጋግሉትም ይሄንኑ ነው። ኦህዴድ ለወያኔ እና ከወያኔ ጋር ይሰራል እንደሽፋን፤ ከውጭ ደሞ ጽንፈኛ ፖለቲከኞችም የሚጠቀሙበት ይመስላል።

ትግራይ ውስጥ ያለው ተቃዋሚ የችግሩን ምንጭ የተረዳ ስለሚመስል የትግል ሰልፉን አሳምሮ ከችግሩ ጋር እይተጋፈጠ ነው። ዛሬ የትግራይ ተቃዋሚዎች የኢትዮጵያ ስጋት ከመቶ አመት በፊት ያለፉት ምንሊክ እንዳልሆኑ የተረዱ ይመስለኛል። ሰሞኑን አንድ የፌስ ቡክ ጓደኛየ በገጼ ላይ የለጠፈው ቪዲዮ እጂግ ግራ እንዳጋባኝ አለ። መጠየቅ የሚችሉ የትግራይ ተወላጆችንም ግራ እንደሚያጋባ ጥርጥር የለኝም። ወያኔዎች ደደቢትን በሚያከብሩበት በየካቲት ወር የሱዳን ባለስልጣኖችን የመጋበዝ ልማድ እንዳላቸው አውቃለሁ። የሱዳን ባለስልጣናት ባደባባይ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ስለ ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ለወያኔ ወገንተኛ በሆነ መልኩ ይናገራሉ የሚል እምነት ፈጽሞ አልነበረኝም። ትንሽ አንገት ያላቸው መስሎኝ ነበር።

ከሱዳን ተጋብዞ የመጣው ባለስልጣን በሚናገረው ነገር ውስጥ ያስተጋባው መንፈስ ወደ ጎሳ እንደሚወስደው ከተረዳሁ በኋላ የወያኔ ድንጋይነት እና ግዴለሽነት ቅጥ ማጣት እጂግ በጣም ገርሞኛል – (ይሄን ተጭነው ቪዲዮውን ይመልከቱ)። የሱዳኑ ተወካይ በንግግሩ ተጨብጭቦለታልም። ወያኔ የአጼ ዮሃንስን አንገት የወሰደው ደርቡሽ (ሱዳኖች) እንደሆነም የረሱት ሁሉ ይመስለኛል። ከደርግ ጋር በነበረው ትግል ምክንያት መደበቂያ እና ስንቅ ሰጡኝ ብሎ ዛሬ ድረስ ሱዳን በቤተኛነት መንፈስ ትግራይ እየመጣ ስለ ኢትዮጵያ ፓለቲካ አፍ የሚከፍትበት ምክንያት ለወያኔ ባለስልጣናትም የሚገባ አይመስለኝም። ለመሆኑ ሱዳን ወያኔን የረዳው ለትግራይ ሕዝብ አስቦ ነበር እንዴ? ይቺን እንኳን አዙሮ ማየት አልቻሉም:: ባለራዕይ ነን ይባላል ደሞ?! (ወደ ሚቀጥለው ገጽ ዞሯል)

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here