Tuesday, March 21, 2023
HomeEthiopian Newsመንግስት ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት አልፈረጅኩም አለ

መንግስት ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት አልፈረጅኩም አለ

“በይፋ አክራሪ ናችሁ ያለን አካል የለም”
አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ
የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ፀሐፊ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በ1994 ዓ.ም ፀድቆ በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የተቋቋመው ማኅበረ ቅዱሳንን የኢትዮጵያ መንግሥት በአክራሪነት አለመፈረጁን አስታወቀ። በሌላ በኩል ማኅበረ ቅዱሳን በበኩሉ በይፋ በአክራሪነት የፈረጀው አካል እንደሌለም አስታወቀ።

በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቁ እና የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ፀሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ማኅበረ ቅዱሳንን መንግስት በአክራሪነት ፈርጆ ሊያፈርሰው ነው የሚለውን አስተያየት በተመለከተ ተጠይቀው እንደመለሱት፤ ማኅበሩ በአክራሪነት በይፋ መፈረጁን እንደማያውቁ ተናግረዋል።

“የተነሳው የአክራሪነት ጉዳይ ከምን አንፃር እንደተነሳ ግልፅ አይደለም። በየትኛውም መድረክ ላይ ማኅበረ ቅዱሳንን አክራሪ ነው ተብሎ የተነሳበት ሁኔታ የለም። ማኅበረ ቅዱሳንን የማሳደግ፣ የመደገፍ የራሱ የሃይማኖቱ ተቋም እንጂ የመንግስት ጉዳይ አይደለም። የማፍረስም ዓላማ አለው የተባለውም ስህተት ነው” ያሉት አቶ አበበ መንግስት ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ ሕገ-መንግስቱም አይፈቀድለትም፤ የመንግስትም ባህሪ አይደለም ብለዋል።

የመንግስት ፍላጎት ሃይማኖት በአግባቡ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ በዚህች ሀገር ላይ ሰላማዊ የአምልኮ ስርዓት እንዲፈፀም እንጂ፤ በሲኖዶሱ የተደራጀን ተቋም ሊያፈርስ የሚችልበት ሕገ-መንግስታዊ ስልጣን የለውም ሲሉ አቶ አበበ ጨምረው ገልፀዋል።

“መንግስት ማኅበረ ቅዱሳንን ሊያፈርስ ነው” የሚለው ጉዳይ የተለያየ መነሻ እንደሚኖረው የጠቀሱት ህዝብ ግንኙነቱ፤ ጉዳዩ ከግንዛቤ እጥረት ወይም ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የአክራሪነት አስተሳሰብን የማስፋፋት ፍላጎት ባላቸው አካላት የተነሳ ሊሆን እንደሚችልም ገምተዋል።

“ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ የሚካሄድን እንቅስቃሴ ሊሸከም የሚችል ትከሻ እንደሌለው በተደጋጋሚ አሳይቷል፤ ትልቅ ትግልም አካሂዷል” ያሉት አቶ አበበ የአሉባልታው ምንጭ አክራሪነትን በማስፈንና አክራሪነትን በመዋጋት መካከል ባለው ፍልሚያ የተነሳ አሉባልታ ነው ብለዋል።

“ጉዳዩ በሬ ወለደ ነው” የሚሉት ሕዝብ ግንኙነቱ፤ ከዚሁ አካባቢ [ከማኅበረ ቅዱሳን] አክራሪነትን ሊደግፉ የሚችሉ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ ብለዋል። “የሰላማዊው አምልኮ ስርዓት እየጠነከረ በሄደ ቁጥር የአክራሪው መድረክ እየጠበበ ስለሚመጣ ከህዝብ ልንነጠል ነው በሚል ፍራቻ ልክ በሕዝበ-ሙስሊሙ አካባቢ የሐሰት ወሬ ተዘርቶ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ገብቷል እንዳሉት ሁሉ አሁን ደግሞ ወደ ሕዝበ-ክርስቲያኑ በማሰራጨት በባዶ ጩኸት ሕዝቡን ለማሳሳት የታለመ ነው” ብለዋል።

“መንግስት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ምንም አይነት ስጋት የለውም” ያሉት አቶ አበበ፣ ማኅበረ ቅዱሳን ከመንፈሳዊ ስራው ጎን ለጎን እያካሄደ ያለው የልማት፣ የሰላም የዴሞክራሲ ስራ ስለሚሰራ መንግስት ከያዘው አጀንዳ ጋር ስለሚጣጣም በአጋዥነት ስለሚያየው ይደግፈዋል እንጂ አያፈርሰውም ብለዋል። ይህ ሲባል ግን እንደ ማንኛውም ተቋም የተቀደሰውን ዓላማ የሚያራክሱ፣ ማኅበሩን ወዳልሆነ አቅጣጫ የሚወስዱ ግለሰቦች አይኖሩም ማለት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። በተለይም “አንድ ሃይማኖት! አንድ ሀገር! አንድ ጥምቀት!” እያሉ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደዚህ አይነቶቹ ግለሰቦች በአክራሪነት ሊፈረጁ ይችላሉ ብለዋል።

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ፀሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና አግኝቶ መተዳደሪያ ደንብ ተቀርጾለት የሚተዳደር ማኅበር እንደሆነ አስታውሰው፤ ማኅበሩ በቤተክርስቲያኗ ስር የሚያገለግል ማኅበር በመሆኑ ከአክራሪነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብለዋል።

“ክርስትናችን አክራሪነትን የሚያስተምር አይደለም። የማኅበሩም አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ከአክራሪነት ጋር ምንም አይነት የሚያገናኝ ስራ የለውም። የቤተክርስቲያን አገልግሎት እየሰጠ ያለ ማኅበር ነው። በጉዳዩም ላይ በይፋ የደረሰን የተፃፈ፣ በቃልም የተባልነው ነገር የለም። ካለም ልንወያይ፣ አስፈላጊውን ነገር ልንተባበር እንችላለን” ሲሉ አቶ ተስፋዬ ከአክራሪነት ፍረጃ ጋር በተያያዘ በይፋ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። ማኅበሩም የተለመደ አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሚገኝም ጨምረው ገልፀዋል።

ማኅበሩን በተመለከተ እየተነሳ ያለው ኀሳብ ምንጩ ምን እንደሆነ አናውቅም ያሉት አቶ ተስፋዬ ምንጩን ሊያውቁ ይችላሉ ብለን የምንገምተው ሚዲያዎቹ ናቸው። እኛ ምንም የምናውቀው ነገር የለም። እንደማንኛውም ጉዳዩን እንደሚከታተል አካል ነው የምናየው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ከአክራሪነት ጋር በተያያዘ በወጡ ሰነዶች ላይ ማኅበሩ መጠቀሱን በተመለከተ አቶ ተስፋዬ ተጠይቀው በማኅበር ደረጃ በይፋ በግልፅ የተጠቀሰ ነገር እንደሌለ ገልፀዋል። ማኅበሩን በቀጥታ የሚመለከት በደብዳቤም ሆነ በሌላ መንገድ የተባለ ነገር የለም ብለዋል።

አንዳንድ የማኅበሩ ምንጮች መጋቢት 2005 ዓ.ም “የአክራሪነት የወቅቱ አደጋና ቀጣይ መፍትሄዎቹ” በሚል በፊዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በተዘጋጀ ሰነድ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ውሰጥ የአክራሪነት አደጋ ያለው በማኅበራት አደረጃጀት ነው መባሉ፤ በቅርቡም ሐዋሳ ከተማ “አክራሪነትና ፅንፈኝነት ችግሮችና መፍትሔዎቹ” በሚል በቀረበ ፅሁፍ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ወጣት ማኅበራትና አደረጃጀት ውስጥ አክራሪነት ማቆጥቆጡን ይህም በሃይማኖት ተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ይሁንታ ያለው ከመሆኑም በላይ ማኅበራቱ ከፅንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ግንኙነት እንዳላቸው መጠቀሱ እንዲሁም ከፓትርያሪክ ምርጫው፣ ከቀድሞ ፓትሪያርክ ጋር እርቅ ለመፍጠር በተደረገው ጥረትና ማኅበሩን ከከሰሩ ፖለቲከኞች ጋር ለማስተሳሰር መሞከሩና ከሌሎችም ጉዳዮች ጋር ተያይዘው የማኅበሩ አባላት መንግስትን በጥርጣሬ እንዲያዩት መደረጉን ይገልፃሉ።

በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ከነበራቸው ግለሰቦች አንዱ የነበሩት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በግል ስለ ሁኔታው ተጠይቀው በጉዳዩ ላይ የጠራ ነገር አለመኖሩን፣ ነገር ግን ጢስ መኖሩን ገልፀዋል። ከጢሱ በስተጀርባ ያለው እሳት ይሁን እሳተ-ገሞራ ባይታወቅም፤ ለጊዜው ግን ማኅበሩን በተመለከተ ግልፅ የሆነ ነገር የለም ብለዋል።

በግላቸው መንግስት ማኅበረ ቅዱሳንን በማፍረስ ስህተት ይሰራል ብለው እንደማይገምቱና ምናልባትም ለማኅበሩ ያሰቡ ሰዎች መስለው ለማኅበሩ የተሳሳተ መረጃ ያቀበሉ እንዲሁም በመንግስት በኩል ማኅበሩን በተመለከተ አፍራሽ አቋም ሊያንፀባርቁ የሚችሉ አንዳንድ ግለሰብ ባለስልጣናት ሊኖሩ እንደሚችሉ ያላቸውን ጥርጣሬ ተናግረዋል።

ማኅበረ ቅዱሳን በ1984 ዓ.ም በዋናነት በእምነቱ ተከታዮች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተመሠረተ ሲሆን፤ የአባልነት መዋጮ በመክፈልና ከፍተኛ የአገልግሎት ተሳትፎ ያላቸው ከ30 ሺህ በላይ አባላትና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተባባሪ አባላት አሉት፤ ማኅበሩ በዋናነት ስብከተወንጌል ረገድ ከሚሰራቸው መንፈሳዊ አገልግሎቶች ባሻገር ገዳማትንና የገጠር አብያተ ክርስትያናትን በልማት እራሳቸውን እንዲችሉ፣ የአብነት ት/ቤቶች እንዲጠናከሩና እንዲጎለብቱ የሚያደርግ ማኅበር ነው።

ምንጭ ሰንደቅ

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here