Sunday, January 29, 2023
HomeEthiopian Newsማኅበረ ቅዱሳን በፓርቲ ፖለቲካ የማይጠረጠርባቸው ምክንያቶች

ማኅበረ ቅዱሳን በፓርቲ ፖለቲካ የማይጠረጠርባቸው ምክንያቶች

ስለዚህ አንድ አባል በግልጽ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ገብቶ የዜግነት ድርሻውን መወጣት ቢፈልግ ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። በማኅበሩ ውስጥ ያለውን የአመራር ኃላፊነት ማስረከብ ይኖርበታል። በዚህ ደረጃ በይፋ ከአመራርነታቸው በሰላም ተሰናብተው ወደፈቀዱት ይፋዊ የፖለቲካ መስመር መጓዝ የቻሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ። ማኅበሩንም የፖለቲካ ድርጅታቸውንም መምራት የሚችሉበት መንገድ አይኖርም። እነርሱ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለማቸውን በማኅበሩ ላይ ለመጫን ቢፈልጉም እንኳን “የፍላጎት መላተም” (“conflict of interests”) ስለሚኖር ሊሳካላቸው አይችልም። የማኅበሩ አባላት በፖለቲካ መሳተፍ የዜግነት መብታቸው ሲሆን በማኅበሩ አገልግሎት መሳተፍ ደግሞ ሃይማኖታዊ የትሩፋት ሥራ እንደመሆኑ ማቻቻል የአባሉ ፈንታ ነው።

ማኅበሩ በፖለቲካ ውስጥ ገብቷል የሚለው (በተለይ በቤተ ክህነቱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች) ከ1980ዎቹ ጀምሮ ሲያዜሙት የነበረ የሰለቸ ዜማ ነው። የሚነቅፉት ግን ማኅበሩ “ኢሕአዴግን አይደግፍም” ብለው ስላሰቡ እንጂ “ተቃዋሚ ነው ብለው ስላመኑ” ብቻ አይደለም። ለነገሩ እነዚህ መንግሥትን በዱላነት ለመጠቀም የሚፈልጉ፣ በመንፈሳዊም በዓለማዊም ሚዛን ቢመዘኑ ውኃ የማያነሱ ደመናዎች “ፖለቲካ” የሚሉት አጎብዳጅነትን ነው። መንግሥት እነሱን ይጠቀማል። እነሱም በአቅማቸው በመንግሥት ይጠቀማሉ።

ታዲያ ማኅበሩ የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት እንደማይደግፍ ነገሩን ሥራዬ ብሎ ለሚከታተል ለማንኛውም ሰው ግልጽ ሆኖ ሳለ በዚህ ጉዳይ መወንጀሉ ለምን አስፈለገ? ክርስቶስ አምላካችን ራሱ “ግብር አትክፈሉ ይላል? ለቄሳር አትገዙ ብሏል፤ ንጉሣችን ሳይሆን ንጉሥ ነኝ ብሏል” የሚል ፖለቲካዊ ክስ እንደቀረበበት ሃይማኖትን ብለው የሃይማኖት አገልግሎት ላይ የተሠማሩ ሰዎች በየዘመኑ የሚከሰሱበት ጉዳይ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልገናል።

ቅዱስ ሉቃስ “ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም፦ እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር” ሲል እንደጻፈው (ሉቃስ 23፥2)። በሌላው ዓለም ያለውን እንኳን ትተን በአገራችን ያለውን ብናስታውስ፣ ነገር ሰሪዎች በየዘመኑ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችንን ከነገሥታቱ ጋር በማጋጨት በአደባባይ እስከመገረፍ ያደረሱበት ጊዜ፣ በግዞት በእስር እንዲማቅቁ ያደረጉበት ወቅት እንዳለ ታሪክ ያስተምረናል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን እና የደብረ ሊባኖስ እጬጌ ጻድቁ አባ ፊሊጶስን ለአብነት ብናንሣ አባ ጊዮርጊስ እንደተጋዘ፣ አባ ፊሊጶስ በአደባባይ ራቁቱን እንደተገረፈ እናነባለን።

ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ላይ ያለ ማኅበር ትናንት እንደፈላ እንደ ክረምት አግቢ ሊታይ አይችልም። መንግሥት ይኼ ሁሉ ሐቲት አይጠፋውም። ማኅበሩ ተቃዋሚም ደጋፊም እንዳይደለ መግለጹ እስካሁን ጉንጭ አልፋ ከመሆን አልዘለለም። መደገፍ የማይችል አካል፣ ባይቃወምም እንኳን ገለልተኛ መሆኑ ለአደጋ ያጋልጠናል በሚል “ባልበላውም ጭሬ ላፍሰው” የዶሮ ፍልስፍና የተቃኘ ነው።

ከዚህም ባሻገር አባላቱ ከአንድ ዘርና ቋንቋ፣ ባህልና ፖለቲካዊ አቋም የመጡ አለመሆናቸው፤ ይልቁንም ሕብረ ብሔረሰባዊና ኢትዮጵያዊ መሆናቸው እንቅልፍ የሚነሣቸው አካላት መኖራቸው ግልጽ ነው። “አዳሜ በየቅርጫትህ ግባ” ሲባል አንድ ቅርጫት ውስጥ የማይጨመሩ፣ ከሌላውም ቅርጫት ካለው ጋር ዝምድናና ፍቅር ያላቸው፤ ከቅርጫታቸው ውጪ የሚያስቡ ሰዎች ያሉበት ማኅበር መሆኑ የሚያስፈራቸው አሉ።

በውጪ አገር ባሉ የተለያዩ የመንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖች ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ሲጠረጠር እንደኖረ እነርሱም በፈንታቸው “ማኅበረ ቅዱሳን የኢሕአዴግ ደጋፊ መሆን አለበት” ሲሉ ኖረዋል። ለምን እንዲህ አላችሁ ሲባሉ ምክንያቱም “ይህንን የሚያህል ትልቅ ተቋም እንዴት ነጻና ፍፁም ሃይማኖታዊ ብቻ ሊሆን ይችላል? ጠርጥር ጠርጥር” የሚል ጥርጣሬ ያቀርባሉ።

ማኅበሩ አብሯቸው ጀብ ጀብ ላለማለቱ ምክንያቱ ዓላማውና ተፈጥሮው መሆኑን ለመቀበል የአገር ውስጡም የዳያስጶራውም ቡድን፣ እነዚያም እነዚያም ይኸው እንደተቸገሩ አሉ። እነዚያ “የዚያ ደጋፊ ነው” እንዳሉት፣ እነዚያም “የዚያ ደጋፊ ነው” እንዳሉት። ማኅበሩ ደግሞ “አነ ዘክርስቶስ፣ አነ ዘቤተ ክርስቲያን፤ እኔ የክርስቶስ ነኝ፣ እኔ የቤተ ክርስቲያን ነኝ” እንዳለ አለ። መጨረሻውን ደግሞ ዕድሜ ይስጠን እንጂ፣ እናየዋለን።

ይቆየን – ያቆየን

ምንጭ-  አደባባይ ብሎግ

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here