Thursday, November 30, 2023
HomeEthiopian Newsማኅበረ ቅዱሳን በፓርቲ ፖለቲካ የማይጠረጠርባቸው ምክንያቶች

ማኅበረ ቅዱሳን በፓርቲ ፖለቲካ የማይጠረጠርባቸው ምክንያቶች

ኤፍሬም እሸቴ

ይህ ጽሑፍ የእኔን የግል ምልከታና አስተያየት ብቻ የሚመለከት እንጂ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ስሙ የተጠቀሰውን ማኅበርም ሆነ ከእርሱ ጋር የአገልግሎት ግንኙነት ያላቸውን ተቋማት የማይመለከት መሆኑን አበክሬ በመግለጽ ልጀምር።

አንድ ብሒል አለ። ውሸትን ደጋግመው ቢናገሩት እንደ እውነት የሚቀበለው ሰው መፍጠር ይቻላል። ስለዚህም ሐሰተኞች ሐሰታቸውን ሳያሰልሱ በተናገሩት መጠን፦ አንደኛ ራሳቸውንም በሐሰታቸው እውነትነት ያሳምናሉ፤ ብሎም ሌሎችን ማሳመን ይችላሉ። ደጋግሞ የመናገር ጥቅሙ ይኼው ነው።

አንዳንድ እውነት የያዙ ሰዎች ደግሞ “እውነት እስከያዝን ድረስ ደጋግሞ መናገር ለምን ይገባል?” ብለው ያቀርባሉ። እውነት አላቸው። ፀሐይ ሲወጣ ጨለማ መሸሹ፣ ሻማ ሲለኮስ ብርሃን MK Logoመፈንጠቁ ላይቀር “ጨለማን ማውገዝ ምን ጥቅም አለው?” ይላሉ። ይህም እውነት ነው። “ጨለማን ደጋግሞ ከማውገዝ አንድ ሻማ ማብራት” እንደተባለው። ነገር ግን ሐሰት ተደጋግማ በመነገሯ ተከታይ መፍጠር እስከቻለች ድረስ እውነትን ደጋግሞ በመናገር የሚመጣ ምን ችግር አለ? ሻማውንም እየለኮሱ እውነቱንም ደጋግሞ መናገሩስ? ስለዚህ በእውነት ተደጋግሞ መነገር፣ በሻማ መለኮስም አምናለኹ። ደጊመ ቃል እንዲሉ የኢትዮጵያ ሊቃውንት።

እንኳን አገር ቤት ያለው አንባቢ ይቅርና እኛ ከአገራችን በብዙ ሺህ ማይሎች ርቀን የምንገኘው ሳንቀር በየዕለቱ የምንኮመኩመው አዲሱ ትኩስ ዜና የማኅበረ ቅዱሳን እና “የተጠመደለት ወጥመድ” ጉዳይ ነው። በማኅበራዊ ድረ ገጾች እና በጡመራ መድረኮች፣ እንዲህ በሕትመት ውጤቶች በሰፊው ሽፋን ያገኘ ጉዳይ ሆኗል። ብዙ ኢትዮጵያውያን (እምነት ሳይለይ) ይህንን ጣልቃ ገብነት በጽኑዕ እየተቃወሙት እያወገዙት ነው። “ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ የሚባል ከሆነ እኔም አክራሪነትን እወደዋለኹ” የሚሉ ሐሳቦች በብዛት ተጽፈው ተመልክቻለኹ።

“የአክራሪነቱ ነገር”፣ ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ በፓርላማ ተናግረውት በነበረ ጊዜ፣ እኔን ጨምሮ ብዙ ፀሐፍት አስተያየታቸውን የሰጡበት ከመሆኑ አንጻር ወደዚያ መመለስ አይገባ ይሆናል። ማኅበሩ ከፓርቲ ፖለቲካ ጋር ግንኙነት እንዳለው በመንግሥት ሰዎች እና በደጋፊዎቻቸው የሚነሣውን ሐሳብ በተመለከተ ግን የግል አስተያየቴን ላሰፍር እወዳለኹ።

ማኅበሩ ፖለቲካ ውስጥ አለበት? ለመሆኑ ፖለቲካ ውስጥ መግባት/ አለመግባት ምንድነው? ማንኛውም ሰው የተባለ ፍጡር ፖለቲካዊ አመለካከት አለው። ፖለቲካ አልወድም የሚሉ ሰዎች ራሳቸው እንኳን ፖለቲካዊ አቋም አላቸው። ልዩነቱ እያወቁ ማወቅ እና ሳያውቁ መኖር ናቸው። የተለያዩ ሐሳቦች እስካሉ ድረስ፣ አስተዳደሮች፣ ገዢዎችና ተገዢዎች እስካለን ድረስ ፖለቲካዊ አመለካከቶች መኖራቸው ግድ ይመስለኛል። “ፖለቲካ እና ኮረንቲ በሩቅ” የሚለው ሰው ራሱ በኮረንቲ ከመጠቀም፣ ሕይወቱ በፖለቲካ ተጽዕኖ ሥር መውደቁ እስካለ ድረስ ፖለቲካ የማይነካው ኢትዮጵያዊ አይኖርም።

ይኼ በፖለቲካ ምሁራን ሳይሆን እኔን በመሳሰሉ ለፖለቲካው ዕውቀት ተርታ በሆንን ሰዎች ቋንቋ “ፖለቲካ ውስጥ መግባት ወይም አለመግባት” የምንለው የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ማለታችን እንደሆነ ይሰማኛል። ፖለቲከኞች የምንላቸው እንደዚያ ያሉ ሰዎችን ነውና። ማኅበረ ቅዱሳን “ፖለቲካ ውስጥ ገባ/ አልገባም” የሚለውንም የምፈታው በዚሁ አንድምታውና አገባቡ ብቻ ነው።

ማኅበሩ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ አባላት አሉት። አባላቱ ሰዎች እንደመሆናቸው ፖለቲካዊ አመለካከት አላቸው። ማኅበሩን በአባልነት ለመቀላቀል የሚያበቃቸው ግን ይህ ፖለቲካዊ አመለካከታቸው አይደለም። የአባላቱ የዓላማ አንድነትና መሠረቱ ማኅበሩ የሚያራምደው ቤተ ክርስቲያናዊ አቋም ብቻ ነው። በሃይማኖትና በአገልግሎት ዓላማ አንድ ናቸው እንጂ በፖለቲካ ርዕዮት የተሰባሰቡ አይደሉም። ሲጀመርስ ስለ ፖለቲካ አመለካከታቸው የት ተጠያይቀው? የት ተገማግመው? የት ተለካክተው? በየትኛው ጊዜ?

ስለዚህም ማኅበሩ አንድ ሃይማኖታዊ አቋም ያራምዳል እንጂ “አንድ ፖለቲካዊ አቋም” የሚባል የለውም። ሊኖረውም አይችልም። ለምን? ምክንያቱም “ፖለቲካዊ አቋምን ለማራመድ” መጀመሪያ ፖለቲካዊ አቋም መያዝ ያስፈልገዋል። ያንን ለማድረግ ደግሞ አባላቱን በሙሉ በዚህ ፖለቲካዊ አቋም ማሳመን ያስፈልጋል፤ ያንን ማድረግ ደግሞ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ማኅበሩ የያዘውን ሃይማኖታዊ አቋም የሚጻረርና ማንም ሳይነካው እንዲፈርስ የሚያደርገው ድማሚት ነው።

እዚህ ላይ መነሣት ያለበት ቁምነገር፤ የማኅበሩ አባላት በሃይማኖታዊም ሆነ በፖለቲካዊ አስተሳሰባቸው ራሳቸውን የቻሉ (ማለትም ማመዛዘን የሚችሉ) ክርስቲያኖች እንጂ የአንድ ቡድን ጀሌዎች አለመሆናቸውን ነው። ራሱን የቻለ አስተሳሰብ ያለው ማንኛውም ሰው፣ አባል የሚሆንበትን ድርጅት ያያል፤ ይመዝናል፣ ያስባል። እንደማይጠቅመውና እንደማይስማማበት ከተረዳ ይተወዋል። ጀሌ ግን የተነገረውን ተቀብሎ እንደ በቀቀን ያስተጋባል፤ ሳያውቅ አባል ይሆናል፤ በጥቂት ጥቅም ይደለላል፣ የሚኖርለትም-የሚሞትለትም ቋሚ መርሕ አይኖረውም።

ማኅበረ ቅዱሳንን እና አባላቱን በአገራችን ላለፉት 40 ዓመታት በጠነነው የፖለቲካ ድርጅት ጀሌነት መገምገም ትክክል የማይሆነው ለዚህ ነው። አባላቱ አገልጋዮች እንጂ ካድሬዎች አይደሉም። አመራር ላይ የሚቀመጡት ሰዎች በተራቸው ለማገልገል እንጂ ከሌላው አባል የተለየ መርሕ ለማራመድ አይችሉም። እናራምድ ቢሉም አባላቱ ጀሌዎች ስላልሆኑ ሊከተሏቸው የሚችሉበት ምንም መንገድ አይኖርም። የአባላቱ አንድነት በሃይማኖት እና በሃይማኖት ብቻ ነው። በበሰለ ሚዛን የሚለካቸው ቢኖር ኖሮ በዘር፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አቋም፣ በትምህርት ደረጃ፣ በዕውቀት፣ በዕድሜ ወዘተ ወዘተ የተለያዩ እንጂ እንደ ሜዳ አህያ አንድ ወጥ እና ልሙጥ አለመሆናቸውን ይገነዘባል።

(ወደ ገጽ 2 ዞሯል)

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here