Tuesday, May 28, 2024
HomeEthiopian Newsግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ ‹‹የተቀናጀ የድርጊት መርሐ ግብር›› አለኝ አለች

ግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ ‹‹የተቀናጀ የድርጊት መርሐ ግብር›› አለኝ አለች

Source - Reporter
የኢትዮጵያና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብራሰልስ ይገናኛሉ

(ሪፖርተር) የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሦስተኛ ዓመት እየተከበረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በግድቡ ላይ የተለየ አዲስ ፖሊሲ የለኝም ያለችው ግብፅ ቀስ በቀስ ተግባራዊ የሚደረግ ‹‹የተቀናጀ የድርጊት መርሐ ግብር›› እንዳላት አስታወቀች፡፡

ይህ የግብፅን የውኃ ደኅንነት ያስጠብቃል የተባለለት መርሐ ግብር ‹‹ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊና ሌሎች ቴክኒካዊ›› የሚባሉ ጉዳዮችን ያቀፈ መሆኑን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስታውቀዋል፡፡

የግብፅ ዴይሊ ኒውስ ጋዜጣ እንደዘገበው፣ ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተለየ ፖሊሲ ባይኖራትም፣ ነገር ግን ግድቡን በተመለከተ የምታራምደው አቋም የተለመደው መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

የዓባይን ውኃ በተመለከተ ከብሔራዊ ደኅንነቷ ጋር ያስተሳሰረችው ግብፅ ግድቡን በተመለከተ ግልጽ የሆነ አቋም እንዳላት የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፣ የግብፅን ፍላጎት በሚፃረር ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ድርድር እንደማይኖር በግልጽ አስታውቀዋል፡፡ የግብፅን ፍላጎት የሚፃረር ያሉት የግድቡ ግንባታ ነው፡፡

ከፖለቲካዊና ከሕጋዊ ማዕቀፎች ውጪ የግብፅ ‹‹የተቀናጀ የድርጊት መርሐ ግብር›› ያካተተው ‹‹ቴክኒካዊ ጉዳዮች›› የተባለው ምንን ለማመልከት እንደሆነ ቃል አቀባዩ ባይገልጹትም፣ የፖለቲካ ተንታኞች ግን የተለመደው የግብፆች ማስፈራሪያ ነው ብለውታል፡፡ የግብፅ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር መነጋገር ሲኖርባቸው ለምን ይህንን ዓይነቱን ማስፈራሪያ እንደሚጠቀሙ ግራ ያጋባል ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ዓመታት እየገነባችው ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት 33 በመቶው መጠናቀቁ ሲገለጽ፣ ግብፅ በበኩሏ የግድቡ ግንባታ ሕገወጥ ነው በማለት በመግለጽ ላይ ናት፡፡ በግብፅ የውኃ ደኅንነት ላይ የሚከሰት ችግር እንደሌለ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ ግብፅ አሁንም በግድቡ ምክንያት ብሔራዊ ደኅንነቴ ተነክቷል ማለቷን ቀጥላለች፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋህሚ ከኢትዮጵያ አቻቸው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር በብራሰልስ ለመነጋገር ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል፡፡ በአውሮፓ ኅብረትና በአፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመገኘት ሁለቱ ሚኒስትሮች ብራሰልስ ይገኛሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ እንደሚነጋገሩም ተሰምቷል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስና ሚስተር ፋህሚ እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 2013 ካይሮ ተገናኝተው በግድቡ ምክንያት የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡

የግብፅ ባለሥልጣናት ግድቡን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አቋሞችን እያራመዱ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1902 ኢትዮጵያና እንግሊዝ የዓባይን ውኃ በተመለከተ አድርገውታል የተባለውን ስምምነት በመጥቀስ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንሄዳለን እያሉ ናቸው፡፡ እነሱ ያልነበሩበትን ስምምነት ይዘው የትም መድረስ እንደማይችሉ የፖለቲካ ተንታኞች እየገለጹ ሲሆን፣ ያ ስምምነት በትርጉም ስህተት ምክንያት ሥራ ላይ አለመዋሉ ይነገራል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋህሚ በተጨማሪ ግድቡን በተመለከተ ከአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካትሪን አሽተን ጋር ተነጋግረዋል፡፡ የሁለቱ ባለሥልጣናት ውይይት ውጤት ግን አልተሰማም፡፡

ግብፅ ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር ጀምራቸው የነበሩ ሦስት ዙር ውይይቶችን በተለያዩ ምክንያቶች ካሰናከለች በኋላ፣ በግድቡ ላይ የተለያዩ ዘመቻዎችን መጀመሯ አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህ ዘመቻዎች መካከል የቅርቡ ግድቡን ዓለም አቀፍ ገጽታ ማላበስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ‹‹የተቀናጀ የድርጊት መርሐ ግብር›› የሚሉት ብዙዎችን ግራ አጋብቷል፡፡

በኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ሦስተኛ ዓመት በማስመልከት በተለያዩ መርሐ ግብሮች የተለያዩ ዝግጅቶች የተደረጉ ሲሆን፣ መጋቢት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ግድቡ በሚገነባበት ሥፍራ በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት አከባበር ተደርጓል፡፡

ስለዘገባው የበለጠ ለማወቅ እዚህ ይጫኑ

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here