ከኢትዮጵያ ጋር የፍቅር ቁርኝት ያለው አስተሳሰብ እና ተቋም ለወያኔ አሸባሪ ነው። ማህበረ ቅዱሳንን ከ1988 ዓመተ ምህረት ኮተቤ ኮሌጅ ስማር ጀምሮ ነው የማውቀው። ጊቢ ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት እከታተል ነበር። በቅድስተ ማርያም የሚሰጠውንም ትምህርት በየወሩ እከታተል ነበር።
ማህበረ ቅዱሳን ትኩረቱ ወያኔ እንደሚለው የፓለቲካ አጀንዳ ቢሆን ኖሮ የዛሬ ስንት ዓመት (ወደ ኋላ )ወያኔን ሽባ ማድረግ የሚችል አቅም መፍጠር ይችል ነበር ፤ በሰላማዊ መንገድ!
ወያኔ የሚያየውን ነገር የሚያየው በፓለቲካ መነጸር ስለሆነ (ያውም በጎሳ ፓለቲካ መነጸር ) ማህበረ ቅዱሳንን እንደፓለቲካ ተቋም ቢያየው የሚገርም ነገር የለውም። ወይ የፖለቲካ ሸውራራነት ነው ፤ ወይ በስልጣን ማጣት ስጋት ከሚመጣ ችግር ጋር የተያያዘ ቅዠት ነው። ወይንም ደሞ ሁለቱንም ነው።
ዙሪያውን ቢፈልግ ቢፈልግ የተደራጀ የሚያሰጋ ኃይል ስላላየ በእምነት የተደራጁ ተቋማትን መፍራት ጀመረ። የእምነት ተቋማት በደርግ እንኳን ዘመን እንዲህ አልተፈተኑም። ትኩረቱ ደሞ የኢትዮጵያ እስልምና እና የኢትዮጵያ ክርስትና ላይ! የወያኔ የፖለቲካ አጀንዳ ብቻ ነው ፤ ወይንስ ሌሎችም ኃይሎች ወያኔንን በገንዘብ እየደለሉ (ገንዘብ ይወዳል መቸም)ከበስከኋላ እያጋፈሩ ነው ጥያቄ ነው ለኔ።
ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል መንግስት ማህበራዊ ቀውስ እየተስፋፋ ባለበት ዘመን ፤ ለህብረተሰቡ ባዕድ የሆኑ ማህበራዊ አስተሳሰቦች እና ጸያፍ የአኗኗር ዘየ በህብረተሰቡ ላይ ለመጫን ብዙ እየተሞከረ ባለበት ሁኔታ የእምነት ተቋማትን ለማፈራረስ መሞከር ማለት ስለ ወያኔ ተልዕኮ የሚናገረው ነገር የለም? ከገጠር ወደ ከተማ ፤ ከከተማ ወደ ገጠር እያፈራረቁ እምነትን የማጥቃት ስትራቴጂ የፖሊሲ ግቡ ምንድን ነው? በገጠር በቅጥረኞች ቤተ ክርስቲያን እስከማቃጠል፤ የኃይማኖት ግጭት እስከማስነሳት ፤ ዋልድባን እስከማሳረስ ተሄደ! በከተማም የሃይማኖት ተቋማቱን ተቆጣጥሮ ቅጥ ያጣ የካድሬ ተቋም እና የወንበዴ ዋሻ ተደረገ። በውድቅት ሌሌት ሊቃነ ጳጳሳትን በር እያስቆረቆሩ የሚያስፈራሩ ካድሬዎች ሰማን! የእስልምናውን እንዲሁ ካድሬ ከነ ሌላ አይነት እምነት ለመጫን ተሞከረ። ዓላማው ምንድን ነው? በርግጥ ወያኔን እና የወያኔን ሰዎች ብቻ የሚጠቅም አካሄድ ነው?
የማህበረ ቅዱሳንን ምንነት ዲፋይን ማድረግ ያለባቸው የእምነቱ ተከታዮች ናቸው ፤ ወይንስ “በሃይማኖት አባትነት” ስም ወያኔ ቤተ ክርስቲያን የሰገሰጋቸው ሙሰኛ ካድሬዎች እና የህወሃት አመራሮች? እንደው ትንሽ ሼም የሚባል ነገር አልፈጠረባቸውም? ይሄ ደደቢት ማለት ምን አይነት ውሃ ነው ያጠጣቸው?
የፖለቲካ አጀንዳ ምንድን ነው? ለመሆኑ ማህበረ ቅዱሳን የፖለቲካ አቋም እና የፖለቲካ ዓላማ ቢኖረው ኖሮ አሸባሪ የሚባልበት አገባብ ምንድን ነው?! አሸባሪነት ምንድን ነው?
ምናልባት ወያኔ ማህበረ ቅዱሳንን ያመላከተው ነገር ቢኖር እስከዛሬ የፖለቲካ አቋም ሳይዝ እምነትን ብቻ የሙጥኝ ብሎ መያዙ ስህተት እንደነበረ ይመስለኛል።
ለመሆኑ ወያኔ ውስጥ ምን አይነት ሽብር ገብቶ ነው አገር እንዲህ የሚታመሰው?!
ከድሜጥሮስ ብርቁ