Friday, September 29, 2023
HomeEthiopian Newsጊዜ ይፈጅ ይኾናል እንጂ ለውጡ አይቀሬ ነው

ጊዜ ይፈጅ ይኾናል እንጂ ለውጡ አይቀሬ ነው

ምንጭ ሃራ-ዘተዋህዶ
ሃይማኖት ከአስተዳደሩ የተለየ በጣም ጥልቅ ነገር ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት ከአንድ ግለሰብ ኾነ ከጥቂት ሰዎች አመራር የተለየና የራሱ ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት፣ ባህልና ሥርዓት ያለው መኾኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

በሥነ ምግባር ደረጃ እኔን ጨምሮ ኹሉም ሰው ችግር ሊኖርብን ይችላል፡፡ ይኹንና ይኼ የሥነ ምግባር ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በመነጋገርና ተገቢውን ርምጃ በመውሰድ ነው፡፡ ስለ አስተዳደር ጉዳዮች ሲነሣ ነገሩ የሃይማኖት ሳይኾን የሥነ ምግባር መኾኑ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚኽ ለእኔ አስተዳደሩን ከሃይማኖቱ ጋራ ማቀላቀል ተገቢ አይኾንም፡፡

ዘመኑን ካልዋጀን ሌላው ቀርቶ የዘመኑ ትውልድ አብሮን ሊሔድ አይችልም፡፡ ትውልዱን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋራ ለማስቀጠል ከፈለግን አስተዳደራዊ ሥርዓታችንን የግድ ዘመናዊ ማድረግ አለብን፡፡ ሃይማኖት አንዴ ተሰጥቶ ያለቀ ስለኾነ የምንጨምርበት ኾነ የምንቀንስበት ነገር አይኖርም፡፡ አስተዳደራችን ግን በየጊዜው ከሚሻሻለው ዕውቀት ጋራ ተዘምዶ መሻሻል አለበት፡፡

የአንድ ደብር ጸሐፊ የኾነ ሰው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከኹለት ሺሕ ብር በማይበልጥ ደመወዝ ኹለት ሦስት መኪና፣ ኹለት የመኖሪያ ቤቶች በፍጹም ሊኖረው አይችልም፡፡ የአንድ ወር ደመወዛቸው ለመኪና ነዳጅ ወጭ የማይሸፍንላቸው አገልጋዮች መኪና እየለዋወጡ ሲይዙ በድሎት ሲኖሩ፣ የልጆችን ይኹን የራሳቸውን ወጭዎች ያለችግር ሲሸፍኑ ይኼ ነገር ከየት መጣ ያሰኛል፡፡

ቤተ ክርስቲያን አኹን እየተጠቀመችበት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ዓለም በ፲፯ኛው መ/ክ/ዘ የተወውንና የነጠላ ሒሳብ አሠራር (single entry) የሚባለውንና በሞዴል የሚሠራ የሒሳብ አሠራር ነው፡፡ በዓለም ላይ እንዲኽ ዓይነት የሒሳብ አሠራር የሚከተል ምንም ተቋም የለም፡፡

የነጠላ ሒሳብ አሠራር ወጪን ወጪ ይላል እንጂ ምክንያቱን አይናገርም፡፡ ስለዚኽ ወጪን ከነምክንያቱ ገቢን ከነምንጩ የሚጠቅሰው የኹለትዮሽ(ደብል) ሒሳብ አሠራር ሥርዓት የላትም፡፡ በመኾኑም ይኼን ተረድቶ የፋይናንስ ሥርዓቱን በአፋጣኝ ማዘመን ይገባል፡፡

ካሽ ሬጅስተር በመጠቀም እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ያለውን አቅም የላይኛው አስተዳደር አካል በሚገባ ለማወቅና ከፍተኛ ብክነትን ለማስወገድ ይችላል፡፡ አኹን እየጠፋ ያለውኮ ብሩ ብቻ ሳይኾን ሰነዱም ጭምር ነው፡፡ የካሽ ሬጅስተርን መረጃ ግን ማጥፋት ስለማይቻል የቁጥጥር ሥርዓትን ማጉላትና ተጠያቂነትን ማስፈን ይቻላል፡፡

የተጀመሩትን የለውጥ እንቅስቃሴዎች የሚቃወሙት በአስተዳደር ላይ ያሉ ጥቂት ሰዎች ናቸው፤ አስተዳደር ላይ ኾነውም ለውጡን የሚደግፉ አሉ፡፡ ምናልባት ጊዜ ይፈጅ ይኾናል እንጂ ችግሩ መፈታቱ አይቀሬ ነው፡፡ ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here