ነገ የሦስት ወር ንቅናቄውን በአዲስ አበባ ይጀምራል
(አዲስ አድማስ) ከመድረክ ጋር ያለውን ጥምረት አቋርጦ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የውህደት ድርድር የጀመረው አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤በመጪው ዓመት ምርጫ የሚሳተፈው የምርጫው አስፈፃሚ አካላት ነፃና ገለልተኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ ብቻ እንደሆነ ሊቀመንበሩ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ገለፁ፡፡
በ97 ምርጫ ቅንጅት የነበረውን ጥንካሬ ፓርቲያቸው መድገም እንደሚፈልግ የገለፁት ኢ/ር ግዛቸው፤ ህዝቡ ብሶት ላይ ስለሆነ በምርጫው ተቃዋሚዎች በቀላሉ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲያቸው ወደ ምርጫው የሚገባው ግን ለምርጫው ነፃና ፍትሃዊ መሆን አስፈላጊ የሚባሉት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ ሚዲያ እና የፍትህ ተቋማት መኖራቸውን ካረጋገጠ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ይህ ጥያቄያችን ከተመለሰ በምርጫው በእርግጠኝነት እናሸንፋለን” ብለዋል የፓርቲው መሪ፡፡
ፓርቲያቸው ከመድረክ ጋር ስላለው ግንኙነት የተጠየቁት ኢ/ር ግዛቸው፤ አንድነት ከቢሮ እና ከመግለጫ ፖለቲካ ተላቆ ትግሉን ወደ ህዝብ ለማውረድ ያደረገው እንቅስቃሴ የመድረክ አመራሮችን እንዳስኮረፈና እገዳው እንደተላለፈ ጠቅሰው “እገዳው ትክክል አይደለም፤ አንሱትና ባቀረብነው የውህደት ጥያቄ መሰረት አብረን እንስራ ብለናቸዋል” ብለዋል፡፡
“መድረክ ከአንድነት የተሻለ ጥንካሬ እንደሌለው ገምግመናል” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ውህደቱን አንፈልግም ቢሉም እንኳን በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በቅንነት አብረን ልንሰራ እንደምንችል ነግረናቸዋል ብለዋል፡፡ ሙሉውን አዲስ አድማስ ላይ ለማንበብ ይሄንን ይጫኑ