Friday, June 14, 2024
HomeEthiopian Newsግብፅ በሳዑዲ ዓረቢያ አማካይነት ኢትዮጵያን ወደ ስምምነት ለማምጣት አስባለች

ግብፅ በሳዑዲ ዓረቢያ አማካይነት ኢትዮጵያን ወደ ስምምነት ለማምጣት አስባለች

ተጻፈ በ ዮሐንስ አንበርብር

ታላቁን የህዳሴ ግድበ በተመለከተ ግብፅ የተፈጠረባትን ሥጋት ለመቅረፍ በሳዑዲ ዓረቢያ መሪነት የባህረ ሰላጤው አገሮች ኢትዮጵያን ወደ ስምምነት እንዲያመጡላት ፍላጐቷ መሆኑን ከወደ ግብፅ ተሰማ፡፡

አል ሞኒተር የተባለው የአገሪቱ ሚዲያ የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ናቸው ያላቸውን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ግብፅ ተሰሚነታቸው ይጠቅመኛል ብላ ያመነቻቸውን የዓረብ አገሮች በሳዑዲ ዓረቢያ አማካይነት በማስተባበር፣ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ትፈልጋለች፡፡

‹‹የግድቡ አገነባብ ዝርዝር መረጃ፣ ግድቡ ስለሚኖረው የውኃ መያዝ አቅም፣ እንዲሁም በየወቅቱ ከግድቡ ሊለቀቅ የሚገባው የውኃ መጠን የግብፅን የቆየ የውኃ ድርሻ የሚቀንስ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ስምምነት ኢትዮጵያ ልትፈርም ይገባል የሚል ይዘት ያለው ሰነድ በግብፅ በኩል እየተዘጋጀ ነው፤›› በማለት አል ሞኒተር ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን መናገራቸው በዘገባው ተጠቁሟል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ በሕዝብ ተቃውሞና በወታደራዊ ተፅዕኖ እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2013 ከተወገዱ በኋላ፣ ግብፅ ከዓረብ አገሮች (ከኳታር በስተቀር) ጋር ያላት ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን ዘገባው ያስረዳል፡፡

የፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲ አገዛዝ መውደቅን ተከትሎ የሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥታት ለግብፅ ከፍተኛ የገንዘብ ዕርዳታ ለማድረግ የቀደማቸው አለመኖሩን የሚያስረዳው ዘገባው 10.7 ቢሊዮን ዶላር በስድስት ወራት ውስጥ ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ገልጿል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታን እያፋጠነች ትገኛለች፡፡ እኛ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር በድጋሚ ወደ ድርድር ለመግባት ተቸግረናል፡፡ ስለዚህ የዓረብ አገሮች ጣልቃ ገብነት ወሳኝ ነው፡፡ ቢያንስ የግድቡ ግንባታ ፍጥነት እንዲቀዘቅዝና ጊዜ እንድንገዛ ዕድል ይሰጠናል፤›› በማለት አንድ የግብፅ ባለሥልጣን ለአል ሞኒተር መናገራቸውን ዘገባው ያስረዳል፡፡

የግብፅ መንግሥት ይህንን ጣልቃ ገብነት የፈለገውና ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው፣ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከሌሎች የዓረብ አገሮች ይሁንታን ካገኘ በኋላ መሆኑን ዘገባው ያስረዳል፡፡

አቡ ዘይድ የተባሉ የዓረብ የውኃ ምክር ቤት ሰብሳቢ፣ ‹‹ኢትዮጵያና ግብፅን ለማግባባት የዓረብ አገሮች ቢጥሩ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የሁለቱን አገሮች ይሁንታ ካላገኘ ተግባራዊነቱ አጠራጣሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በቅርቡ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንን ከአገሩ ቢያስወጣም፣ እዚህ ያሉ ኢንቨስትመንቶችን ከመደገፉ ባሻገር የሳዑዲ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ መሆኑን፣ የኩዌት ዴቨሎፕመንት ፈንድ፣ የዓረብ ባንክ ፎር ዴቨሎፕመንት ፈንድ፣ እንዲሁም የነዳጅ አምራች የሆኑ የዓረብ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዳላቸው ዘገባው ይገልጻል፡፡

‹‹በመሆኑም ይህ ኢኮኖሚያዊ ትብብርና የገንዘብ ድጋፍ በተወሰነ መጠን የሚቀንስ መሆኑን ማሳየት ማለት፣ ኢትዮጵያን ወደ ስምምነት እንድትመጣ ማስገደድ ነው፤›› በማለት አንድ የግብፅ ዲፕሎማት መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 2013 የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርትን በመጥቀስ የዓረብ አገሮች ሊገጥማቸው የሚችልን የውኃ እጥረት ለመቅረፍ 200 ቢሊዮን ዶላር በጀት ለቀጣዮቹ አሥር ዓመታት መበጀት ይገባቸዋል በማለት፣ የውኃ ችግር የሁሉም ዓረብ አገሮች ነው በማለት ዘገባው ያስተሳስረዋል፡፡

አል ሞኒተር ያወጣውን ዘገባ በድረ ገጽ ላይ ያነበቡ ኢትዮጵያውያን ግብፅና ኢትዮጵያ ወደ ድርድር ቢገቡ ምርጫቸው ቢሆንም፣ በዘገባው ላይ እንደተመለከተው የሳዑዲ ዓረቢያን ጣልቃ ገብነት ግን ሙሉ በሙሉ አውግዘዋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በቅርቡ በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰውን ጉዳት የሚጠቅሱት እነዚሁ አስተያየት ሰጪ ኢትዮጵያውያን፣ የሳዑዲ መንግሥት ለኢትዮጵያ ያለውን አመለካከት በፈጸመው ተግባር ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ግብፅ ለራሷ ኢፍትሐዊ የሆነ ጥቅም ስትል ሳዑዲ ዓረቢያና ሌሎች የዓረብ አገሮችን ለማስተባበር እየጣረች በመሆኑ ኢትዮጵያም አሁን እንዴት መሄድ እንዳለባት ገብቷታል፡፡ ለዚህም ነው ከአፍሪካ አገሮች ጋር ጥብቅ ትስስርን የመሠረተችው፡፡ በመሆኑም የግብፅ ማንኛውም አፍራሽ እንቅስቃሴ ውጤት ከመላው የአፍሪካ አኅጉር ጋር መላተም ነው፤›› በማለት ተችተዋል፡፡

ምንጭ-ሪፖርተር

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here