-ታጥረው የተቀመጡ የሚድሮክ ቦታዎችን የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቋመ
(ሪፖርተር) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ለዓመታት ታጥረው በተቀመጡ ቦታዎች ላይ ስለሚወስደው ዕርምጃ፣ የጠቅላይ ሚንስቴር ጽሕፈት ቤት እንዲያማክራቸው መጠየቃቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡
ለዓመታት ታጥረው በተቀመጡ ቦታዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያካሂደውን ማጣራት የቀጠለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በሚድሮክ ኩባንያዎች የተያዙ 11 ቦታዎችን የሚመረምር ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደሩ በልደታ ክፍለ ከተማ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ ለዓመታት ታጥሮ የተቀመጠውን በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር የሚገኘው ሁዳ ሪል ስቴት የተያዘ መሬት ጉዳይ ቀደም ሲል እንዲነጠቅ ባሳለፈው ውሳኔ ፀንቷል፡፡ አስተዳደሩ መሬቱ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬቱ ካርታ እንዲመክን ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁዳ ሪል ስቴት ቅሬታውን ለአስተዳደሩ በማቅረቡ ቦታው ለረዥም ጊዜ ታጥሮ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ የኩባንያውን ቅሬታ ባለመቀበሉ የልደታ ክፍለ ከተማ መሬቱን ነጥቆ መሬት ባንክ ማስገባቱ ታውቋል፡፡
ከዚህ በመቀጠል አስተዳደሩ በሚድሮክ ኩባንያ ተይዘው ለዓመታት ግንባታ ሳይካሄድባቸው የቆዩ ቦታዎችን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ጥናት ማካሄድ ጀምሯል፡፡
ቦታዎቹም ፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት የሚገኘው አንድ ትልቅ ቦታ ካዛንቺስ በኢሲኤ ጀርባ በተካሄደው መልሶ ማልማት ክልል ውስጥ የሚገኙ ሦስት ቦታዎች፣ ጉርድ ሾላ አካባቢ የሚገኙ ሁለት ቦታዎችና የሸራተን ማስፋፊያ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ እነዚህ ቦታዎች ላይ ጥናት ከተካሄደ በኋላ ለውሳኔ ለአስተዳደሩ ካቤኔ ይቀርባል ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ባካሄደው ጥናት 109 ቦታዎች ለዓመታት ግንባታ ሳይካሄድባቸው ታጥረው ተቀምጠዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 56 ቦታዎች ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው የውሳኔ ሐሳብ ቢቀርብም፣ ጥናቱ ሌሎች ርዕሶችን ጨምሮ እንዲካሄድ በመወሰኑ በአሁኑ ወቅት ጥናቱ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ከንቲባ ድሪባ ኩማ ይህ ጥናት ባይጠናቀቅም በሚወሰደው ዕርምጃ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ምክር መጠየቃቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ሪፓርተር