Tuesday, July 23, 2024
HomeEthiopian Newsሁላችንም ሰክረን ነበር፡፡

ሁላችንም ሰክረን ነበር፡፡

ፋክት መጽሄት

ድርጊቱ የተፈፀመው በ1983 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ነው፡፡ ያኔ ወያኔ ወያኔ እያለ፣ ጎንደርና ባህርዳርን እንጂ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ህዝቡ በኢህአዴግነቱ እውቅና ሳይሰጠው፡፡ ያኔ ጎንደርና አካባቢው ከደርግ ሰራዊት ነፃ ወጥቶ በወያኔ እንደተያዘ፣ ያኔ እኔ ከማስተምርበት በጣና ሀይቅ ዳር ከምትገኘው የጎርጎራ መንደር ወደ አዲስ አበባ መጥቼ፣ ንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስተማር እንደጀመርኩ – በመጋቢት 1983 ዓ.ም፡፡ ያን ጊዜ አንድ ጓደኛዬን ለመጎብኘት አዋሳ አካባቢ ወደምትገኝ ለኩ የምትባል አነስተኛ ከተማ ሄድኩ፡፡ ጓደኛዬ ብዙ ጓደኞች ነበሩት፡፡ ወዲያው የእኔም ጓደኞች ሆኑ፡፡ የጓደኛዬ ጓደኞች አብዛኞቹ መምህራን ነበሩ፡፡ ከሁለቱ የግብርና ሰራተኞች በስተቀር ማለቴ ነው፡፡ ከሳምንት ቆይታ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ልመለስ ስል በዋዜማው ጓደኞቼ (አሁን ሁሉም የጓደኛዬ ጓደኞች የእኔም ጓደኞች ሆነዋል) ተሰብስበው ጋበዙኝ፡፡ ቀን ተቀምጠን፣ ማታ ባንኮኒ ተደግፈን ተጨዋወትን፡፡

ማታ ላይ አብረን ስላሳለፍነው እጅግ አጭር ሳምንት ዋንጫችንን ደጋግመን አነሳን፡፡ በፍቅራችን ቅናት ይሁን በመለያየታችን ሀዘን ተፈጥሮ ጭምር አዘነች፡፡ የለኩ አድባር ጣራ ሰማይዋን በነጎድጓድ ጥፋሯ እያረሰች፣ ዳመና አይኗን ጨምቃ ዝናብ እንባዋን አፈሰሰች፡፡ እኩለ ለሊት ሆኖ ድንገተኛው የመጋቢት ዝናብ እስኪያባራ ጠጣን፡፡ ዝናቡ አባርቶ ከመጠጥ ቤቱ ስንወጣ እኩለ ለሊት አልፎ ነበር፡፡ ከዝናቡ የተጠራቀመው ጎርፍ በመንገዱ ግራና ቀኝ ይወርዳል፡፡ በዚህ መሀል አንዱ የግብርና ሰራተኛ፣ ‹‹በጣም ስለምወድህ ለመጨረሻ ጊዜ ልጋብዝህ እፈልጋለሁ፡›› አለኝ፡፡ ሌላው ጓደኛችን ቀጠለ፤ በርግጥ እንዳለው በጣም የሚወድህ ከሆነ ግብዣውን ልቀበለው ይገባል፣ ነገር ግን እሱ ለአንተ ያለው መውደድ ከሌሎቻችን በተለየ ከፍ ያለ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፣ በማለት ሃሳብ ሰጠ፡፡ ቀጠለና ሌላው ለዚህ ማረጋገጫ ያለውን ሃሳብ እንዲህ በማለት አቀረበ፡፡ ‹‹እውነት ከእኛ የተለየ የምትወደው ከሆነ በመንገዱ ግራና ቀኝ በሚወርደው ጎርፍ ውስጥ ግባና በደረትህ ተኛለት፡፡ ይህን ካደረግክ በእርግጥም ለእንግዳው የተለየ መውደድ አለህና ትጋብዘዋለህ፡፡›› ጓደኛችን ንግግሩን ሲጨርስና ጋባዡ ጎርፍ ውስጥ ሲነጠፍ አንድ ሆነ፡፡ ሁላችንም የጋባዡን የተለየና የላቀ መውደድ አረጋገጥን፡፡ ተደነቅን፡፡ ተገረምን፡፡ እንደዚያ ያለ የመውደድ ምጥቀት ከዚህ ቀደም ከመሀከላችን ተመልክቻለሁ የሚል አልተገኘም፡፡ ጓደኛችንን ከጎርፍ ውሃ ውስጥ ጎትተን አወጣነው፡፡ ፈተናውን በማለፉ ግብዣው ተፈቀደለት፡፡ አንድ መጠጥ ቤት አስከፍተን ገባን፡፡ ጋባዥ በጎርፍ የተነከረ ልብሱን እየጨመቀ ጋበዘን፤ ከለሊቱ ስምንት ሰአት ሲሆን ደግሞ በጎርፍ የራሱ ብሮችን ጨምቆ ከፈለና ግብዣው አበቃ፡፡

ያን እለት ምሽት የነበርነው ስድስት ጓደኛሞች ነበርን፡፡ ባይገርምም ሁላችንም ሰክረን ነበር፡፡ የሰከረው ጋባዥ፣ ግብዣ ለማድረግ የተለየ የጓደኝነት ፍቅርን ምክንያት አድርጎ ሲያቀርብ አምስታችንም ተቀበልነው፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም ሰክረን ነበር፡፡ ትልቁ ፈተና ግን ያን የላቀ ፍቅር ማረጋገጥ ሆነብን፡፡ ሌላው ጓደኛችን ለዚህ ማረጋገጫ የሚገርም ‹ምሁራዊ› መፍትሄ ያለውን የጎርፍ ውሃ ጥምቀት ሲያቀርብ በአድናቆት ተቀበልነው፡፡ እንዲያውም ይህች ሀገር መቼም ቢሆን፣ ከአዲስ አበባ ርቆ ጠረፍ ቢኬድም የሚታደጋት ጠቢብ ምሁር እንደማታጣ አረጋገጥን፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም ሰክረን ነበር፡፡ በመጨረሻም ስለዚህ ጓደኛችን እንግዳ ተቀባይነትና ታላቅ የመውደድ ጥበብ ዋንጫችንን አነሳን፡፡ የሆነው ሁሉ በታላቅ መገረምና መደነቅ፣ ተጠየቃዊ ውይይት ተደርጎበት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም ሰክረን ነበር፡፡ ግን ያቺ ስካራችን ከእንቅልፍዋ የቀሰቀሳት፣ ባንኮኒ ውስጥ ቆማ ዋንጫችንን አረቄ የምትሞላዋ አስተናጋጅ አልሰከረችም፡፡ በስካር ሚዛኑን ያጣው ህሊናችን በሚያፈልቀው ቧልት እየገፈፈች፣ አንዳንዴም እየተንከተከተች ስካራቸንን ለማሳበቅ፣ ለማጋለጥ ትሞክር ነበር፡፡ ግን ማንም ከቁምነገር የቆጠራት የለም፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም ሰክረን ነበር፡፡

እነሆ ዛሬ ከሃያ ሶስት አመታት በኋላ ሀገሬ ኢትዮጵያ ተጠየቃዊ ተጨባጭነት ያልተከተሉ ድርጊቶች በጠራራ ፀሐይ የሚፈፀምባት ሆነች፡፡ ዜጎቿም የእነዚህን በህሊና ተጠየቃዊነት መዛባት የተውሸለሸሉ ተግባራት ፈፃሚና አጽዳቂ ሆኑ፡፡ እነሆ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ሰከረ፡፡ ሀገሬ በሚዛናዊ ህሊና፣ ተጠየቃዊ ቅብብሎሽ ሊተነተኑ የማይችሉ ተግባራት በሚፈፅሙና ይህን ድርጊት በሚያጸድቁ ዜጎች ተሞላች፡፡

ያልሰከረ የለም! ጎዳና ተዳዳሪው፣ የቀን ሰራተኛው፣ ወያላው… ድሀው በጠኔ ሰከረ፡፡ የጠኔ ስካር ደግሞ አንጀት ገብቶ ወስፋት እያስጮኸ ስለሆድ ያሳስባል እንጂ፣ ከፍ ብሎ ራስ ላይ አይወጣም፡፡ የወስፋት ጩኽት ክፋቱ የህሊናን ጩኸት አለማሰማቱ ነው፡፡ በመሆኑም አብዛኛው ድሀ ‹‹እዬዬም ሲዳላ ነው›ን ተረቶ፣ የህሊናውን ጩኸት ችላ አለው፡፡ ስለሚጮህ ወስፋቱ ቢጮህ ባልከፋ፡፡ ስለሚጮህ ወስፋቱ ለጥ-ፀጥ አለ፡፡ ማን ከርሱ ውስጥ ስለሚጮህ፣ ስለሚፈራገጥ ወስፋቱ ለስላሳና ዝምተኛ ይሆናል! ሰክሮ የህሊናውን ሚዛን የሳተ ካልሆነ በቀር!

የቤት ኪራይ ከፋዩ፣ ለኮንዶሚኒየም ቆጣቢው፣ ከእጁ ላይ ለአፉ የማያጣው፣… በጠኔ ከሰከረው ሙልጭ ድሀ ትንሽ ከፍ ያለው… ከላይኛው እጅግ ወርዶ፣ ከታችኛው ስንዝር ርቆ ‹መሀል› ላይ ያለው ዜጋም በምናገባኝና በራስ ወዳድነት ሰክሯል፡፡ ለዚህኛው ዜጋ ቁም ነገሩ በልቶ ማደሩ ነው፡፡ ወር ባይደርስ፣ ደሞዙ ቢቀነስ አያገባውም፡፡ ሊያገባ ያጫል፤ የሚወልደው ልጅ የሚማርበት ት/ቤትና ስርዓተ ትምህርት አያስጨንቀውም፡፡ ምክንያቱም በምናገባኝ ሰክሯል፡፡ ስለሱና ስለጎጆው፣ ስለ ልጁ አስተዳደግና ትምህርት የሚያገባቸው ደሞዝ የሚከፍለውና ስርአተ ትምህርት የሚቀርጽለት፣ ጎዳና የሚዘረጋለት መንግስትና የግል ትምህርት ቤት የከፈቱለት ባለሀብቶች ናቸው፡፡ የነዚህኞቹ ስካር ህሊናቸው ከጉበናቸው አልፎ እንዳያስብ አድርጎታል፡፡ ከጉበናቸው ውጪ በሀገራቸው ስለሚደረገው ማድረግ የሚገባቸው ልማታዊ ዜና ማዳመጥ፣ የምርጫ ካርድ ማውጣትና በአምስት አመት አንዴ ለኢህአዴግ ድምጽ መስጠት፣ በፀረ-ልማት ሀይሎችና በአሸባሪዎች ላይ አዋጅ ሲነገር ሰልፍ መውጣት ነው፡፡ ይህም ሆኖ የዜናው፣ የአዋጁና የመመሪያው ይዘት አያገባቸውም፡፡ የሚያገባቸው ማዳመጡ፣ መምረጡና ሰልፍ መውጣቱ ነው፡፡ የእነዚህኞቹ ስካር ከድሀው ከፍ የሚለው ፍርሀትንም ስለሚጭንባቸው ነው፡፡

ሀብታሞች፣ ባለሀብት ዜጎቻችንም ሰክረዋል፡፡ እነዚህኞቹን አናታቸው ላይ ወጥቶ ያሰከራቸው በየእለቱ ከጮማ ጋር የሚቆርጡት፣ ከውስኪ ጋር የሚጠጡት ኢትዮጵያን በገንዘባቸው ገዝተው የግላቸው የማድረግ ፍላጎታቸው ነው፡፡ ከዚህ ስካር ባንነው ወደ ህሊናቸው ሚዛን መመለስ አይፈልጉም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ መግዛት ሲያልሙ ከስራቸው ያለውን በጠኔና በምናገባኝ የሰከረ ድሀ የሚያደርሱበት ይቸገራሉ፡፡ እናም ስካራቸው በድሀ ወገናቸው ጥላቻና ኢትዮጵያን የግል ሀብት በማድረግ ፍላጎት ተቃርኖ ሲወዘውዛቸው ውሎ ያድራል፡፡

በየመስሪያ ቤቱ የተሾሙ ባለስልጣኖቻቸውም ሰክረዋል፡፡ እነዚህን ያስከራቸው ደግሞ የስልጣን ጥማትና ስግብግብነት ነው፡፡ ባለስልጣኖቻቸውም ኢህአዴግ ገና ሲሾማቸው ከስልጣን ጥማት ጥንስሱ ጉሹን ይግታቸዋል መሰል ስለስልጣናቸው ጽናት የሚያደርጉት ድርጊት እንኳን የታወቀ ወሰን፣ የአይን ማረፊያ አድማስ አይገኝለትም፡፡ በአንድ በኩል ለስልጣን ያበቃቸውን ኢህአዴግን ለማስደሰት አኩርፎታል ያሉትን ሰድበው፣ ተቀይሞታል ያሉትን አስረው፣ ጠልቶታል ያሉትን አፍርሰው፣ ወዶታል ያሉትን ሾመው የልብ አውቃነታቸውን ለማሳየት እንቅልፍ ያጣሉ፡፡ በሌላ በኩል ስግብግብነታቸውን ለማስታገስ ታደጉት የተባሉትን ዜጋ ያድጉበታል፡፡ ጉቦ ሲቀበሉ፣ ቀረጥና ግብር ሲያጭበረብሩ፣ የዜጎችን ሀብትና ንብረት ሲወርሱ ህሊናቸውን አይሸነቁጣቸውም፡፡ ምክንያቱም ሰክረዋል፡፡ የሰከረ ህሊና ትልቅ ተግባሩ የሚጋልበው ሰካራም ለሚያደርገው ሁሉ ማጨብጨብ ነው፡፡

በየመንግስት መዋቅሩ የተዋቀሩ ኮሚቴዎቻችንም ሰክረዋል፡፡ እዚህ ነጥብ ላይ ተግባራዊ ምሳሌ ልጠቅስ እወዳለሁ፡፡ የዛሬ ሶስት ሳምንት በኮንትነታል ሆቴል በተዘጋጀ በሚዲያና ልማታዊ መንግስት ላይ ሊመክር በተቀመጠ ጉባኤ፣ የፋና ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ ሃላፊ/ስራ አስኪያጅ ባቀረቡት ንግግር (ጥናት)፣ በ1983 ዓ.ም ለሚዲያው ነፃነትና ዲሞክራሲያዊነት ትልቁ ማነቆ የሰለጠነ ሙያተኛ (ጋዜጠኛ) አለመኖሩ ነው ካሉ በኋላ፣ ይህ ችግር ዛሬም አልተቀረፈም አሉ፡፡ ሁሉም አድማጭ በአዘኔታ ተዋጠ፡፡ ችግራቸው ታየው፡፡ ሃያ ሶስት አመት ልማታዊም ሆነ ዲሞክራሲያዊ ጋዜጠኛ ለማስተማር በቂ አይደለም ወይ ብለን አልጠየቅንም፡፡ ምክንያቱም የሰከሩት ተናጋሪው ብቻ ሳይሆን እኛ ታዳሚዎቹም ነን፡፡ አብዛኛው የጉባኤው ታዳሚ በስልጣን ጥሞና ተስፋ፣ ጥቂቱ በምናገባኝ የሰከርረ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ያህል ለቡድን ስካር ማሳያ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ አይገኝም፡፡ ፌዴሬሽኑ በማንአለብኝነትና ተአብዮት ጥንብዝ ብሎ ሰክሮ፣ ቆሞ መራመድ አቅቶታል፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ የሰላሳ አንድ አመት ዳዴው እየተመለሰ ነው፡፡ ዋልያዎቹ ያስቆጠሩት እያንዳንዱ ጎል የአሰልጣኙና የፌዴሬሽኑ አናት ላይ ወጥቷል፡፡ በዚህም የተነሳ እጃቸውን የሚሰነዝረውን ልሳናቸው የሚናገረውን አያውቁም፡፡ አስራ አራት ሚሊዮን ብር በሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ አንድ ጎል ብቻ ላገባ ቡድን፣ በአንድ ውድድር ላይ እንኳን ለሩብ ፍፃሜ ቡድኑን ላላደረሰ አሰልጣኝ፣ እውነት በስካር ህሊናው የደነዘዘበት ካልሆነ በቀር ማን የሸልማል! በቻን የአፍሪካ ዋንጫ አፍረን ያሳፈርናችሁ በፌስቡክና በሚዲያ ስታብጠለጥሉን ሞራላችን ተነክቶ ነው ይሉናል፡፡ ይህ እውን በስካር ከደነዘ ስንኩል ተጠየቅ በቀር ከየት ይመነጫል! እኛስ እውን በጠኔ፣ በምናገባኝ፣ በስልጣን፣ በሀብት የሰከርን ዜጎች ባንሆን ይህን እንቀበላለን! እውን ያልሰከረ ፌዴሬሽን፣ ያልሰከረ ባለስልጣን፣ ያልሰከረ መንግስት፣ እኛም ያልሰከርን ዜጎች ብንሆን ቡድኑ ድሮም ከሚታወቅበት ኳስ ማማሰልና አብዝቶ መቀባበል እምብዛም የጎላ ለውጥ ያላመጡትን፣ በቻን ላይ በሶስት ውድድሮች የሚያደርጉት ጠፍቷቸው እንደተቆጡት ህፃን ከወንበራቸው ሳይነሱ ሽንፈትን ያላመጡትን (የዋጡት አይመስለኝም) አሰልጣኝ በአሰልጣኝነት እንዲቀጥሉ እንፈቅድ ነበር! ግን እሳቸው ማንያህሎኝነትና እራስን ካለመመርመር የመነጨ ተአብዮት አስክሯቸዋልና በፈቃዳቸው ስራቸውን አለቀቁም፡፡ እኛም ሰክረናልና ይበቃዎታል አላልንም፡፡ ሁላችንም ሰክረናል፡፡ ሀገሬ የሰካራም ሀገር ሆናለች፡፡

ችግሩ ያኔ ከሃያ ሶስት አመት በፊት ስድስት ሆነን የሰከርን እለት፣ ፊት ለፊታችን አንዲት ያልሰከረች ኮማሪት ነበረች፡፡ በትዝብቷም ይሁን በሳቋ ስካራችንን ታጋልጥ ነበር፤ ሰሚ ባይኖርም፡፡ ዛሬ ሀገሬ ያልሰከረ ዜጋ የላትም፡፡ እንደዚያች ኮማሪት በትዝብቱም ይሁን በምፀቱ ስካራችንን አጋልጦ ወደ ልቦናችን የሚመልሰን ወገን የለም፡፡ ሁላችንም ሰክረናል፡፡ ሀገሬ የሰካራም ሀገር ሆናለች፡፡ ፈጣሪ ብሎ ስካሩ ቢያልፍ አንጎበሩ እንዴት ያደርት ይሆን!? ምስኪን ኢትዮጵያ!

_____________

ይሄ ጽሁፍ የተወሰደው ከዶ/ር በድሉ ዋቅጂራ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ነው፤ ቀደም ሲል ጽሁፉ በፋክት መጽሄት እንደወጣ ግን ተጠቁሟል

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here