የዛሬውን የአውሮፕላን ጠለፋ በትክክል ጠለፋ ለማለት ያስቸግራል። በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ በበረራ ዓለም የማይጠረጠር ( እና መጠርጠርም የማይገባው) ቦታ ላይ የደህንነት ስጋት ሊፈጥር የሚችል ክፍተት አመላክቷል።
ከዚህ ክፍተት ጋር በተያያዘ ወደፊት የሚወሰድ ርምጃ ያስቸግራል። በአብራሪዎቹ ላይ የሆነ አይነት ጫና ሊፈጥር ስለሚችል ፤ እና ያ ደሞ ተመልሶ የመንገደኞችን ደህንነት ዋስትና በሆነ መልኩ መልሶ ስጋት ላይ የሚጥል አይነት ስለሆነ።
ከዚያ መልስ ድርጊቱ የተወሳሰበ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ገጽታ አለው። ሁለቱም ደሞ የሚናቅ እና የሚተው አይደለም ፤ ለኢትዮጵያውያን አስፈላጊ ነውና።
በኢኮኖሚ አንጻር ስናየው የበረራ ንግድ (ቢዝነዝ) በዓለማችን እጂግ ውድድር የበዛባቸው ከሚባሉ የንግድ መስኮች በዋነኛነት ሊጠቀስ የሚችል ነው። ከዓለም ዓቀፍ የፍጆታ ሸቀጦች ዝውውር መስፋፋት እና በእንደዚህ ዓይነት ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች መበራከት ጋር ተያይዞ ፤ ከቱሪዝም መስፋፋት እና መሰል ነገሮች ጋር ተያይዞ የአየር መንገድ ንግድ ብዙ ውድድር አለበት። አየር መንገዶች ለተጠቃሚ አገልግሎት የሚያቀርቡት ዋጋ እና ምቾት( መስተንግዶን ጨምሮ ) የመወዳደሪያ መክሊታቸው እንደሆነ ባይካድም ፤ ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ የደህንነት ሪከርድም ወሳኝ ነው። እንግዲህ መንገደኞች በሚፈልጉበት ሰዐት የሚፈልጉበት ቦታ መድረስ እንዳለባቸው እና እንደሚፈልጉም ሳይረሳ!
በየሃገሮች ከሚደረግ የሁለትዮሽ ስምምነት (በንግድ እና መሰል ጉዳዮች) ሌላ ዓለም አቀፍ በረራን የሚገራ ዓለም ዓቀፋዊ ህግ ቢኖርም ፤ እንደ በረራ ባለ ውድድር በሚበዛበት የንግድ መስክ ሸፍጥ እና ተንኮል ሊኖርም ይችላል። በበኩሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው በአሩሻ ያጋጠመው ጉዳይ መንስኤው እስካሁን ግልጽ አይደለም። ወራት በማይባል ጊዜ ውስጥ ዛሬ ደሞ የጠለፋ ዜና ተሰማ። እንዲህ አይነት ዜናዎች በኢንተርኔት ከመለቀቃቸው ጋር ተያይዞ ፤ መንገደኞች (ቱሪስቶችም ይሁኑ ነጋዴዎች ወይ በሌላ ስራ ምክንያት የሚንቀሳቀሱ) የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከመስተጓጎል እና መዘግየት ጋር ከዚያም አልፈው ከደህንነት ስጋት ጋር አያይዘው ሊያዮ ይችላሉ። ዛሬ የተፈጠረውን ክስተት በብርሃን ፍጥነት ዓለም ዓቀፍ ሜዲያዎች እያራገቡት ነው። ነገሩ በትክክል ምን እንደሆነ እንኳን የማጣራት እድል ሳይሰጥ። ከሚራገበው ወሬ ጋር አብሮ ለተጠቃሚዎችም ጭምር የሚዘዋወረው የአየር መንገዱ ገጽታ አሉታዊ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። ያ ደሞ በሂደት የአየር መንገዱን ስም (ሬፒዮቴሽን) ይጎዳዋል። አየር መንገዱ እየተምዘገዘገ ወደ ታች መውረድ ከጀመረ በስተመጨረሻ የምትጎዳው ኢትዮጵያ ነች። ስለዚህ በኢኮኖሚ አንጻር አሉታዊ ገጽታ ያለው ክስተት ነው።
በፖለቲካ መነጸር ሲታይ ምን ያህል ስኬታማ ነው የሚለውን ጥያቄ ዘለን (በዚህ ቅጽበት እሱን መመዘን ስለማይቻል) በፖለቲካ ትርጉሙ ላይ መነጋገር ይቻል ይመስለኛል።
የድርጊቱ ዋነኛ ተዋናይ ረዳት አብራሪው ነው። በምንም መለኪያ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ሰዎች የሚመደበብ አይመስለኝም ፤ ስለሆነም በግል ህይወቱ በኢኮኖሚ ቋፍ ላይ የነበረ አይደለም።
ከተገኘው አጭር የኦዲዮ ንግግር መሰረት ረዳት አብራሪው ጥገኝነት ጠይቋል። ድርጊቱ በአጠቃላይ የፖለቲካ መልዕክት ለማስተላለፍ የዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የተደረገ ይመስላል። በእርግጥ ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ በህወሓት መንግስት ስላለው አፈና አስረግጦ የሚናገር ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፓይለት ሆኖ ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የመብት ጥሰት እና አፈና እያወራ መቀጠል እንደማይችል ግልጽ ነው፤ ስራውን ያጣል። አየር መንገዱ የሕወሓት የግል ንብረት እስከመምሰል እየደረሰ ነዋ! ምን አልባት አብራሪው በትክክል የተሰማው ነገር ይሄው ሊሆን ይችላል። የሚሰራውን ነገር ለማየት ቅርበት አለውና።
ከዚያ ውጭም ቢታይም መሰረታዊ ነጥብ አለ። ፓይለቶችም (ሌሎች በመንግስት ሰራተኛነት ሂሳብ የህወሃት መንግስት ተቀጣሪ ለመሆን የተገደዱም) ዜጎች ናቸው። እንደ ዜጋ የሚሰማቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ በስራቸው የመፍረድ ስሜት እንዲሰማቸው ለምን ተፈለገ?!በመንግስት ሰራተኛነት የሚሰሩትን ስራ በችሎታቸው እና በዜግነታቸው ያገኙት ሳይሆን ፤ ለሕወሓት አለቅነት እውቅና በመስጠት፤ ህወሓት እንደሚፈልገው በፍርሃት መንፈስ እንዲኖሩ የሚደረግበት ምክንያት ምንድን ነው? ሕወሃት ኢትዮጵያዊ የሆነ አጀንዳ እና ማህበራዊ አስተሳሰብ ቢኖረው እንኳ ልክ ባይሆንም እኔን ምሰሉ ቢባል ትንሽ፤ እንደው ትንሽ ስሜት ይሰጥ ነበር።
ኑሮውን በዚህ ያደረገ በቅርቡ ከኢትዮጵያ የመጣ ሰው አገኘሁ። አንዱ ዋነኛ ጥያቄየ “የህዝቡ መንፈስ እንዴት ነው” ነበር። የነገረኝ በጣም ያሳዝናል። የነገረኝን መረጃ ስተረጉመው ልክ ቅኝ የተገዙ ህዝቦች የሚያንጸባርቁትን ዓይነት ሆነብኝ። ቆይቶ ሲቃ ያዘኝ። እንግሊዞች (ዛሬ እንዴህ የሌለ አይነት የመብት ተሟጋች ነን ሊሉ) ኬኒያ ውስጥ ጭቃ እንዳይነካቸው ሰው (ኬኒያውያንን) እያነጠፉ በሰው ላይ ተረማምደዋል ይባላል። የስነ ልቦና ጠባሳው ዛሬ ድረስ ሙሉ ለሙሉ የዳነ አይመስለኝም። እንደዛ ከተረገጠ ትውልድ የተገኘ ሌላ ትውልድ ያንን የመንፈስ ስብራት ሰብሮ ለመውጣት ብዙ ሞክሯል። የእንግሊዝ ጥላ ግን ዛሬም የጠፋ አይመስለኝም።
ድህነት ለኢትዮጵያ በፍጹም አዲስ አይደለም። በባዶ እግሩም እየሄደ ምርታማ ያልሆነ መሬት እያረሰ ልጆቹን እየመገበ ፤ በእምነት ብቻ ሆዱ ዱጭ ሳይል መንፈሱ ጢም እንዳለ ኖሯል ኢትዮጵያዊ!
ዛሬ የሰውነት መንፈስንም ፤የኢትዮጵያዊነት መንፈስንም በስትራቴጂ የመስበር ዘመቻ እየተጧጧፈ በከተማ የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ ቅጥ ካጣ ጨቋኝ ጋር አብሮ ቢራ እየገለበጠ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ የሚሆን አለ። እንኳን ሌላው የሚሰማውን ለመረዳት ራሱ ምን እንደሚሰማው እንኳን የማያውቅ አለ። ልጅ ፤ ቤተሰብ ያለው ለልጂ ነው ይባል ወጣት ሆኖ እንዲህ ከባርነት ጋር ተስማምቶ የሚኖርብት ምክንያት ምንድን ነው? ረዳት ፓይለቱ በግል በኑሮው ባይጎድልበትም የሚያየው አፈና እና የመንፈስ ስብራት ረብሾት ከሆነስ? ለመሆኑ የኬኒያ ፓይለት ፤ የደቡብ አፍሪካ ፓይለት የተለየ ፓለቲካ አስተሳሰብ ከያዘ በስራው ላይ የመፍረድ ስሜት የሚሰማው ይመስላችኋል?? የመንግስት ሰራተኛነት የሚፈልገው ነጻነት እና የገለልተኛ (ኒዮትራል) ስሜት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለውም ይሄው ነው። አማራጭ ስለሌለ አውሮፕላን እስከመጥለፍ ተደረሰ -መልዕክት ለማስተላለፍ!የዜግነት ክብር ማለት ምን ማለት ነው? ጥያቄው ለህወሓት ደጋፊዎች ነው::
ከድሜጥሮስ ብርቁ