Sunday, December 3, 2023
HomeEthiopian Newsአማራ የለም

አማራ የለም

ህወሃት የመንግስት ስልጣን የያዘ ሰሞን በፕሮፌሰር መስፍን ፤ ዶ/ር መኮንን ቢሻው ፤ መለስ ዜናዊ እና ጓደኟው መካከል የተደረገ ውይይት ቪዲዮ ክሊፕ ባለፈው ሁለት ቀን እንደ አዲስ እየተዘዋወረ የመለስ ዜናዊ ሃሳብ እየተንቆጳጰሰ ነው።

መጀመሪያ ነገር ቪዲዮው የተቆረጠ ይመስላል። ለመለስ ዜናዊ የተሰጠው ሪባታል አልተካተተም። ሪባታል ያልነበረ ከነበረ ውይይቱ ሙሉ አልነበረም ማለት ነው።

ቪዲዮው ላይ በተገኘው መረጃ ልክ ስንመዝነው ራሱ መለስ ዜናዊ ከሌንጮ ይሁን ከሌላ የውጭ ጸሃፊ ዘግኖ (ዘጋኝ ነው መቸም!) ያኘከው ሃሳብ የተወለጋገደ እንደነበረ ለማሳየት አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል::

ተቆርጦ የቀረበው ሃሳብ ትኩረቱ በአማራ ማንነት ጋር የተያያዘ ነው። ለመድገም ሳይሆን ፊት ለፊት ለማየት እንዲመች ያህል የፕሮፌሰር መስፍንንም የዜናዊንም ሃሳብ እዚህ ላቅርበው::

ፕሮፌሰር መስፍን

”የአማራው ብሄር አልተወከለም ስለሚባው ነገር…ለውክልና አስቸጋሪ ነው የሌለ ነገር መወከል አይቻልም። የለም አማራ የሚባል ነገር ። …ሀገሩ የት ነው ሲባል ሃገሬ አማራ ነው የሚል ሰው የለም። … ማንነቱን የሚገልጸው በመሬቱ ነው። ባካባቢው ነው። …ምሳሌ ጥራ ብባል እኔ የማውቀው አንድ ነገር ብቻ ነው:: በጣሊያን ጊዜ በአምስቱ አመት፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲከፋፍል በጌምድርን፤ ወሎን ፤ጎጃምን ሰሜን ሸዋን አንድ ላይ አደረገ እና አማራ አለው። ያ ብቻ ነው።[ዜናዊ ገብቶት ይሆን?!] እንጂ እነዛ ሰወች ራሳቸው እዚህ ውስጥ ያሉ ሰዎች ‘እኛ አማሮች ነን’። ‘የአማራነት ስሜት አለኝ’ የሚል የለም። በብዙ ነገር ስመለከተው የሌለ ነገር ነው። እዚህ ሃገር የለም። አለመኖሩ ደሞ ለኔ ጥሩ ነገር ነው። ለኢትዮጵያ ጥሩ ነገር ነው። አሜሪካን ሃገር እየተፈጠረ ነው። ያ እንደማይጋባብን ተስፋ አለኝ…”

መለስ ዜናዊ

“በፕሮፌሰር መስፍን ከተሄደ ለሁሉም የሚሰራ ነው። ኦሮሞም የሚባል ነገር የለም። ትግራይም የሚባል የለም። ነገር ግን ከዚህ በላይ ደሞ ትግራይን ትግራይ የሚያደርግ ኮንሴፕት አለ። ቋንቋ አለ፤ ባህል አለ፤ ስነ አእምሮ አለ፤ እነኝህን ግምት ውስጥ በማስገባት ከባቢያዊ የሆኑ ልዮነቶች እንዳሉ የታወቀ ሆኖ ፤ አንድ ትግራይ የሚባል ነገር አለ፤ አንድ ኦሮሞ የሚባል ነገር አለ ፤ አንድ አማራ የሚባል ነገር አለ ።ይሄን ስል ጎጃሜው እና ጎንደሬው እና ሸዋው ከታሪክም ጋር የተያያዘ ነገር አለ ፤ ፕሮፌሰም ያመጡት ሃሳብ አለ ምናልባት ወደ ትግራይ ድንበር ያለው ጎንደሬ ከትግራይ ጋር ይበልጥ ይጋባ ይሆናል።ያም ሆኖ አማራ የሚባል ህዝብ አለ ህዝቡን እንደዚህ እንትን ማለቱም ትክክል መስሎ አይታየኝም። የአማርኛ ቋንቋ አለ። የወሎ ያነሱት ለየት ያለ ነገር ነው። … እስላም ነኝ የሚለው ቀደም ሲል ኦሮሞ የነበረ ነው። ቋንቋው እየጠፋ የሌላ ቋንቋ [ አማርኛ ማለቱ ነው] እየወሰደ የመጣው ነገር [ ይሄ ጀዋር የቋመጠለትም አይነት ነገር ይመስላል] …አማራ የሚባል ህዝብ አለ ፤ታሪክ አለ ፤ቋንቋ አለ “

የእኔ ጥያቄ

ከመለስ ዜናዊ ትንተና ምሳሌ ብነሳ – ከቋንቋ ውጭ በእርግጥ “ትግራይን ትግራይ” የሚያደርግ የተለየ ኮንሴብት አለ? እንዳሁኑ ሳይፈራርስ የኢትዮጵያ ባህል ባብዛኛው ከእምነት (ከሃይማኖት እስልምናም ይሁን ክርስትና) የተሰራ ነው የሚመስለው። የትግራይን ህዝብ ከሌላው ህዝብ የሚለይ በልዮነት ሂሳብ የሚያዝ መሰረታዊ የባህል ልዮነት አለው?! ተምቤን እና ወልቃይት ምን አይነት የባህል እና የታሪክ ልዮነት ሊኖራቸው ይችላል? በሌላው አካባቢ ያለው የአካባቢያዊነት ( ፕሮፌሰር እንዳሉት ከመሬት ጋር የተሳሰረ) ትግራይ ውስጥ የለም?

ትግራይን አንድ የሚያደርግ ስነ አእምሮ ምንድን ነው? ለምን ተምቤን የአርበኛ መፈልፈያ ሆነ ? ለምን አድዋ ከኤርትራ አስካሪዎች የተዋለዱ ባንዳዎች ተፈጠሩባት?ዘመንን ከዘመን እያገናኘን ሃሳቡን ብንመዝነውም እንዲሁ የተለያየ ስነ አእምሮ ልናገኝ እንችላለን። አጼ ዮሃንስ “ኢትዮጵያ የተባለችው ምሽትህ ፤ልጂህ እናትህ ናት“ በሚል ብዙ ሰራዊት ያሰለፉበት እና አንገት የሰጡበትን ማንነት አሁን ከዚያው አጼ ዮሃንስ ከወደበቀሉበት ኢትዮጵያዊ ማንነት ብሎ ነገር የለም የሚሉ ብቅ አላሉም እንዴ እንዴት የሁለቱ ስነ አእምሮ አንድ ሊሆን ይችላል? ሌላው ቀርቶ በጣሊያን ብዙ አስካሪ ከመለመለበት ኤርትራ ለኢትዮጰያ የሞቱ ጣሊያንን የወጉ ሞልተዋል።

“አማራነት” የማንነት መግለጫ ከሆነ እንደተባለው ራሱን እንደ አማራ የሚቆጥር አልነበረም። ራስን በትውልድ ቦታ እና አካባቢ የመግለጡ ዝንባሌ የበለጠ ጠንካራ ነበር። ”ተስፋ ገብረስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ“ ለምን ዘብሄረ ”አማራ” አልተባለም?! ”ብርቁ ጀመረ ዘብሄረ የጁ“ ለምን ዘብሄረ “አማራ” አልተባለም?በታሪክ የነበረውም ጦርነት አካባቢያዊ ገጽታ እንደነበረው ምንም አንድ እና ሁለት የለውም። የታንጉት ሚስጥሩን ትተን አጼ ቴዎድሮስን በጎንደሬነት ብንይዛቸው ሸዋን ለምን ወጉት? በዛብህ “አማራ” አይደለምን? ሸዋ እና ጎጃም ለምን ተዋጋ? ሸዋ እና ወሎ ለምን ተዋጋ? አሁን በሚባለው አይነት ሁሉም “አማራ“ ናቸው? አማራነት ስላልነበረ እና አካባቢያዊነት ይጠነክር ስለነበር ይመስለኛል።

መለስ ዜናዊ ስነ አእምሮ ባለውም ነገር ብናየው የጎጃም ስነ አእምሮ እና የሸዋ ስነ አእምሮ አንድ ሊሆን አይችልም። የሸዋ እና የጎንደር ስነ አእምሮ አንድ ከትግራይ በተለየ ሁኔታ አንድ ሊሆን አይችልም። የጎጃምም ባህል ቢሆን (የራሱ የሆነ ካለው) ከአዲስ አበባው ጋር ተመሳስሎ ከትግራዮ ጋር መሰረታዊ ልዮነት እስከሚፈጥር ድረስ የተለያየ አይነት ሊሆን አይችልም። ስሜት አይሰጥም። የሸዋ ስነ አእምሮ የኦሮሞን ስነ አእምሮ አልቀላቀለም ብሎ ማለትስ ይቻላል?

ነገርየዋን የዘሯት ጥልያኖች እና ሌሎች የውጭ ሰዎች ናቸው።

ሰለሞን ደሬሳ ዘበት እልፊት በሚል ”ወለሎታት“ በ”የነብሯ ወተት“ ርዕስ ከተደረደሩ ስንኞች (ምንም ለሌላ ጉዳይ ቢጻፍም) በአምሳለ ኢትዮጵያዊ ለተከሰቱት ጥልያኖች (ጉማጆች) የምትሆን መስሎ ተሰማኝ :-

መራር የነብር ጡት በመጥባቴ
ተደናብሮ
ድንጉጥ ኖሮ ሞቴ
ተረስቶት ያለ ስም መጥራቴ
ለጊዜው ጥሎኝ በተጓዘ ሞቴ
ፋሽስት ተነቀለ ብየ
ስቸ መሳሳቴ!

አመጣጡ

ተመሳሽነቱን እንዴት እንዲህ ሳትነው
ማናከሱን ሰውን ከሰው
እድገት ብሎ ሊመጣ እያላበው
እርጉዝ አስወርዶ አራስ የሚሰልበው

መልኩ

እትብቱን ጥሬ በልቶ ሊሸሽ በደም ተለውሶ
ሊያመልጥ እንደገና የሌለንን አግበስብሶ
መጣ ተመልሶ የኔኑ ፊት ለብሶ

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here