Thursday, May 30, 2024
HomeEthiopian Newsየአቶ አሥራት ጣሴ እስር የኢህአዴግ የጉልበት ፖለቲካ ማሳያ ነው!

የአቶ አሥራት ጣሴ እስር የኢህአዴግ የጉልበት ፖለቲካ ማሳያ ነው!

(ፍኖተ ነጻነት) ፓርቲያችን አንድነት በተደጋጋሚ ከገዥው ፓርቲ ህግን ከለላ በማድረግ እና የመንግስትን ሥልጣን በመጠቀም የሚደርስበትን ከፍተኛ አፈና ተቋቁሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ ትግሉን አጠናክሮ መቀጠሉ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

በተለይም ፓርቲያችን በመላው የሀገራችን ክፍል የዘረጋውን መዋቅር በህዝባዊ አቅም ወደ ተሻለ ደረጃ በማሸጋገር በአምስት ዓመት ስትራተጂክ ዕቅዱ መሰረት እያከናወነ ያለው ህዝባዊ ንቅናቄ እና በተሳካ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዶ ዴሞክራሲያዊ የአመራር ሽግግር ማድረጉ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ተስፋ ያሳደረ ቢሆንም ገዥውን ፓርቲ በአንጻሩ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደከተተው ይስተዋላል፡፡

ኢህአዴግ ቀደም ሲል የፓርቲያችንን እንቅስቃሴ በመከታተል ከከፍተኛ አመራሮች መካከል አቶ አንዱዓለም አራጌ፤ ናትናዔል መኮንን እና ሌሎች በርካታ አባላትን የተለያየ ምክንያት ፈጥሮ እየወነጀለ ለእስር መዳረጉ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህም በድንገት የተደረገ ሳይሆን የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር እና የኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ በግልጽ በፓርላማ ተገኝተው ‹‹አንድነት ፓርቲ እግር ሲያወጣ እግሩን እንቆርጣለን›› ባሉት መሰረት የፈጸሙት ነበር፡፡

አሁንም የራዕያቸው አስቀጣይ ነን የሚሉ የገዥው ኃይሎች ፈለጋቸውን ተከትለው የአውራ ፓርቲ (የአንድ ፓርቲ ስርዓት) ለመገንባት አንድነትን በጉልበት ፖለቲካ ማጥፋት እንደ ብቸኛ መንገድ ወስደው እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ በመላው የሀገራችን ክፍል በርካታ አባሎቻችን ከስራ ተፈናቅለዋል፤ በግፍ ከሀገራቸው እንዲሰደዱ ተደርገዋል፤ ታስረዋል፤ ተደብድበዋል፡፡ ይህም በየጊዜው በፓርቲያችን ልሳን በመረጃ ተደግፎ ለህዝብ ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በፓርቲያችን አመራር እና አባላት ላይ የተፈጸመውን የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት ባመላከትንበት ሪፖርትም ተካተቶ ለህዝብ ይፋ ተደርጓል፡፡

በተለይም የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል የተካሄደውን ህዝባዊ ንቅናቄ ተከትሎ ፓርቲያችን በተንቀሳቀሰባቸው አሥራ አንድ የሀገራችን ከተሞች ጉልህ ሚና የተጫወቱ እና በህዝብ ተቀባይነት ያላቸውን አባላት ምክንያት እየፈጠሩ እና የፍትህ ስርዓቱን የፖለቲካ መሳሪያ እያደረጉ ለእስር እና ለእንግልት መዳረጉን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

ኢህአዴግ ገና በጊዜ የጀመረው የ2007 ዓ.ም የምርጫ ዘመቻ የተለመደውን የጉልበት ፖለቲካ የተከተለ ሲሆን በቅርቡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ለንሴቦ ወረዳ አቶ አለማየሁ ለሬቦ የተባሉ የሲተዳማ ዞን የአንድነት ስራ አስፈጻሚ በአዲስ አበባ ተገኝተው የፓርቲ ጉባኤ ተሳትፈው ሲመለሱ በቁጥጥር ስር ውለው ለ22 ቀናት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር ቤት ከተሰቃዩ በኋላ መንግስትን ሰድበዋል የሚል ክስ ተመስርቶባቸው በዋስ ተለቀዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ በየካቲት 30 ቀን የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር (የብሄራዊ ምክር ቤት አባል) የሆኑት አቶ አስራት ጣሴ ፍርድ ቤትን ዘልፈዋል ተብለው ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ሌሎች አራት ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች ሊታሰሩ ሴራ እየተሸረበባቸው መሆኑን ምንጮች ለፓርቲያችን እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡

የፍትህ ስርዓቱን ዋነኛ የፖለቲካ መሳሪያ ያደረገው የኢህአዴግ መንግስት አቶ አስራት ጣሴን ለማሰር እንደ ምክንያት የተጠቀመው በአዲስ ጉዳይ መጽሄት 197 ቅፅ 7 ያወጡትን ጽሑፍ ሲሆን አጠቃላይ መልዕክቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ የሌለ መሆኑን፤ ህጎች አፋኝ መሆናቸውን፤ ኢ.ቲቪ የሰራቸው አኬልዳማ፤ ጀሃዳዊ ሃረካትና ሌሎች ለፖለቲካ ጥቃት ማድረሻ የተቀነባበሩ ድራማዎች ህገ ወጥ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ ይህ የፍትህ ጥያቄ ደግሞ አቶ አስራት ጣሴ ገና በጠዋት ለትግል የወጡበት፤ ከመሰሎቻቸው ጋር ሆነው አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍት ፓርቲ እንዲመሰረት በርካታ መስዋዕትነት የከፈሉበት የፖለቲካ አላማቸው እና የፓርቲ አቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡

‹‹የኢህአዴግ መንግስት ከሚመራቸው ፍርድ ቤቶች ፍትህ ይገኛል ብለን ሳይሆን ለታሪክ እንዲመዘገብ ወደ ፍርድ ቤት እንሄዳለን›› ሲሉም የግል ሃሳባቸው ብቻ ሳይሆን በብዙ አንቀጽ የተጠቀሰ የፓርቲያቸው አቋም ስለመሆኑም ማሳያ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ኪሊማንጃሮ የተባለው ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር በመንግስት ተቋማት ላይ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በህዝብ ከማይታመኑ ተቋማት መካከል ፍርድ ቤቶች በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ናቸው፡፡

ከነዚህ በህዝብ ከማይታመኑ ተቋማት ፍትህ አይገኝም ብሎ ማመን እና እምነትን መንገርም ሆነ መጻፍ ህገ መንግስታዊ መብት መሆኑ እየታወቀ በአካል ባልተገኙበት ችሎት በአካል ተገኝቶ ችሎትን ያወከ ወይም የዘለፈ በሚቀጣበት ፍታብሔር አንቀጽ 480 ቀርበው እንዲያስረዱ ከተጠሩ በኋላ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተጠሩበት የፍታብሔር አንቀጽ የሚያዘው ጥፋታኛ ሆነው የተገኙ ቢሆን እንኳ በአነስተኛ የገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ እንጂ ለእስር የሚያበቃ አልነበረም፡፡

ኢህአዴግ ይህንን እያደረገ ያለው ቀናቶች ወደ 2007 ዓ.ም ምርጫ እየገሰገሱ እና ፓርቲያችንም በህዝባዊ አቅሙ እየጎለበተ በመምጣቱ ካለቃቸው እንደተማሩት እግር ያወጣ ፓርቲያችንን እግር በመቁረጥ፤ አመራሩን ህግን ከለላ አድርገው ለእስር በመዳረግ፤ እንዳይጽፍ፤ እንዳይነገር እና በፍርሃት ቆፈን ተይዞ አንገቱን እንዲደፋ በማድረግ በምርጫ ሜዳው ከጀሌዎቻቸው ጋር ሩጠው አሸንፈናል ብሎ ለማወጅ የሚደረግ አስነዋሪ ዘመቻ ነው፡፡

ነገር ግን እንዲህ ያለው አምባገነናዊ ተግባር ትግላችንን የበለጠ አጠናክረን በመግፋት ሰላማዊ ትግሉ የሚጠይቀንን መስዋዕትነት ለመክፈል የሚያበረታን እንጂ ወደኋላ የማይመልሰን መሆኑን ዛሬም እንደ ትላንቱ ለመላው ህዝባችን እናረጋግጣለን፡፡

የፍትህ ስርዓቱም ከአንድ ፓርቲ ወገንተኝነት እንዲወጣ እና በግፍ የታሰሩ አመራሮቻችንንም በነጻ እንዲያሰናብት እንጠይቃለን !!!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
የካቲት 1 ቀን 2006ዓ.ም

ስለመግለጫው የበለጠ ለማወቅ እዚህ ይጫኑ

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here