Tuesday, March 21, 2023
HomeEthiopian News" ትዳር ለሁሉም "

” ትዳር ለሁሉም ”

“ትዳር ለሁሉም”

በፈረንሳይ የስምንት መቶ ሃምሳ አመት እድሜ እንዳለው የሚነገርለት የኖተር ዳም ካቴድራል ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ሚያዚያ ወር አስገራሚ እና አስደንጋጭ ክስተት አስተናግዷል። ዶሚኒኩ ቨኔ የሚባል የ78 ዓመት ዕድሜ ያለው የፈረንሳይ የታሪክ ምሁር እና የፖለቲካ አክቲቪስት በዝግታ እና በተረጋጋ ሁኔታ ወደ ቤተክርስቲያኑ መሰዊያው (ኦልታር) በመሄድ በጽሁፍ ያዘጋጀውን መልዕክት በመሰዊያው ላይ ካስቀመጠ በኋላ ሽጉጡን አውጥቶ ወደ ማንም ሳይቃጣ እንደተረጋጋ ወደ ጭንቅላቱ አስጠግቶ ራሱን ሰውቷል።

ለምን?

የፈረንሳይን ማህበረሰብ ማህበራዊ እሴት ይጎዳል ያለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ከብዙ ውዝግብ እና የተቃውሞ ሰልፍ በኋላ ፤ በብዙ አጀብ ጉልበት አግኝቶ ስሙን አሳምሮ “ትዳር ለሁሉም” በሚል አንቀጽ ስር የፈረንሳይ ህገ-መንግስት አካል በመሆን ጸደቀ።

በዶሚኒኩ ዓይነት እድሜ ላለ ፤ ማህበራዊ እሴቱ ግድ ለሚለው ለረዢም ዘመን የነበረው ማህበራዊ አስተሳሰብ በአንድ አስር ዓመት በማይሞላ በሆያ ሆየ ህግ እንደቡልዶዘር ሆኖ (ማለት ነው!) ሲያፈረሰው ማየት እና ማህበራዊ ህጉ ከፈረሰ በኋላ ያለችውን ፈረንሳይን ላለማየት ብቻ የወሰደው ርምጃ በቂ ምክንያት ብቻ ሊሆን ይችላል። ልክ ለፍቅረኛ እንደመሞት ያለ። ነውረኛ ራስ ወዳዶች ፍቅረኛቸውን ነው የሚገሉት። ዶሚኒኩ ራሱን በመሰዊያው አጠገብ የሰዋው ለመልዕክቱ አጽኦት ለመስጠትም ይመስላል። ሃሳቡን ለሚቃወሙት ብቻ ሳይሆን ፤ በዋነኛነት የሱን ህሳብ ለሚደግፉትም የተላለፈ የማበረታቻ መልዕክት ይመስላል።

በእርግጥ ተቃዋሚዎቹ የነገሩን ጭብጥ እና ጉዳዮን ወደጎን በማድረግ የዶሚኒኩን ታሪክ እንደ ሹራብ ክር ተርትረዋል ፤የእስልምናን ተስፋፊነት ይቃወማል ፤ የአሜሪካ እና የአውሮፓን ግንኙነት ይቃወማል ፤ ልቅ የሆነ ስደተኛን የሚያስገባ ህግ ይቃወማል ፤ በቅኝ ግዛት ዘመን ፈረንሳይ በአልጀሪያ ላይ ባደረገችው አስከፊ ጦርነት ተሳታፊ ነበር ፤ የሚሉና ሌሎችም በግልጽ ምክንያቱን በጽሁፍ አስፍሮ ራሱን ካጠፋበት ምክንያት ጋር የማይገናኙ ጉዳዮችን በመጎልጎል የፕሮፌሰሩን መልዕክት “በወግ አጥባቂነት” ፕሮፓጋንዳ ለመሸፈን ተሞከረ።

አንድ ግምት መውሰድ ይቻላል- ከወሰደው ርምጃ በመነሳት። የዶሚኒኩ ችግር ግብረሰዶማውያን በየጓዳቸው የሚያደርጉት ነገር አይመስልም። ነገር ግን አደባባይ የወጣው እና በህግ ከለላ ተሰጥቶት ሊያራምዱ ያሰቡት የአስፋፊነት ወይንም የተስፋፊነት አዝማሚያ በእርግጥ አሳሳቢ ነው። በዚህ “ትዳር ለሁሉም” በሚለው አንቀጽ ግብረሰዶማዊ ትዳርን ( ሴት ከሴት ፤ወንድ ከወንድ ) ህጋዊ እውቅና ከመስጠትም በላይ ግብረሰዶማውያኑ ( የክብር ስሙ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ይሉታል) የማደጎ ልጂ የማሳደግ መብታቸውንም አብሮ እውቅና ተሰጥቶታል።

ጉዳዮ የ”ሰውነት” ተፈጥሮን የማይጻረር እና እንዲያውም በአስተሳሰቡ የመጠቀ እና ራሱን የ”ተቀበለ” ( “የማንነት ጥያቄ ማለት ይሆን” ለነገሩ ከተፈጥሮ ጋር የሚያያዝ ነገር ነው እንዳይባል ልጆች ከወለዱ በኋላ በቀዶ ጥገና ሴት የሚሆኑ ወንዶች አሉ? ለሰሚው ግራ ነው። ሊገባ አይችልም) ሰው የሚያደርገው ድርጊት ፤ ፍጹም ሰብአዊ ልማድ አድርጎ የማቅረቡ ዘመቻ ሳያንስ ፤ ህጻናትን ጭምር በማደጎ እንዲያሳድጉ መፍቀድ የሰብዓዊ መብት ጭምር ተደርጎ ተወሰደ።

የህግ እውቀቱ ባይኖረኝም በብዙ ሃገሮች እድሜው 18 ዓመት ያልደረሰ ወጣት ለሙሉ እድሜ የደረሰ ሰው በሚዳኝበት ሁኔታ በወንጀል ችሎት የሚዳኝ አይመስለኝም። ሌላው ቀርቶ አገልግሎቶችን እና ሸቀጦችን በመጠቀም ረገድ ከህጻንነት እድሜ ጋር በተያያዘ ድንጋጌ የሚያደርጉ ሃገሮች አሉ። እዚህ ካናዳ ከክፍለ ሃገር ክፍለ ሃገር ቢለያይም አንድ ልጂ የመንጃ ፈቃድ የሚያወጣበት እድሜ ተደንግጓል። ሲጋራ መግዛት እና ማጨስ የሚችልበት እድሜ ተደንግጓል። መጠጥ መግዛት እና መጠጣት የሚችልበት እድሜ ተደንግጓል። ከነዚህ ድንጋጌዎች በስከጀርባ ያለው መሰረታዊ አስተሳሰብ ለሙሉ እድሜ ያልደረሱ ልጆችን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር እንደሆነ ብዙ አያሻማም። የማመዛዘን ፤ የማስተዋል እና ውሳኔ የመስጠት አቅም መሰለኝ ግምት ውስጥ የገባው። ያ ከሆነ ለማሰብ እና ለማመዛዘን ያልደረሱ ልጆች ስለተቸገሩ ብቻ በግብረሰዶማውያን ቤት እንዲያድጉ መፍቀድ አግባብ አይሆንም። ልጆቹ ይዘው በሚያድጉት ስነ-ልቦና እና በወደፊት አኗኗራቸው ተጸዕኖ አያሳድርም ማለት አይቻልምና። ቤት ውስጥ ምን እያዮ ነው የሚያድጉት?!

“የግለሰብ መብት” በሚል ሂሳብ ሊደግፉት እንደሚችሉ ብገምትም ፤ የኢትዮጵያ “አክቲቪስቶች” ጉዳዮን በአሜሪካውያኑ እና አውሮፓውኖቹ ፍጥነት አንስትው አጀንዳ ያደርጉታል የሚል ግምት አልነበረኝም። የዛሬ ሳምንት አካባቢ ፌስ ቡክ በዚህ ርዕስ ላይ ተቀውጦ ነበር። እንዴት በዚህ ሰዓት በአጀንዳነት እንደቀረበ አላውቅም። ገለልተኛ መስለው ነገሩን ያቀረቡ አሉ። የመብት አጋፋሪ መስለው የግብረሰዶምን መብት ያራገቡ አሉ። ምንም ያላሉ አሉ። ካነበብኳቸው ውስጥ በግልጽ ተቃሟቸውን ያንጸባረቁ አሉ (ሕይወት እና አሌክስ ረዘም ያለ “ስታተስ አፕዴት” አካፍለዋል) ።

“ወግ አጥባቂ” ከሚባሉት በላይ በጉዳዮ ላይ ወግ አጥባቂ ሆነው ብቅ ያሉት “የግለሰብ ነጻነት” አቀንቃኞች ናቸው። ግብረ ሰዶማዊነትን መቃወም እንዳላዋቂነት እና ድንቁርና ሁሉ አድርጎ መሳል ተፈልጓል ። በቅኝ ግዛት እና ለሎች ጉዳዮች ጋር በተያይዘ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሊበራል አስተሳሰብ እንደፈረንሳይ ማህበረሰብ የገባው ያለ አይመስለኝም። የፈረንሳይ አብዮት ታሪክ ከሚያረጋግጣቸው ነገሮች አንዱ ከነጻነት ጋር በተያያዘ መልኩ ፈረንሳዮች ከነጻነት ጋር የሚጋጭ የሚመስላቸውን የቆየ አስተሳሰብ አሽቀንጥረው ሲጥሉ ምንም ስስት አላሳዮም። የኋላ ኋላ እስከ ናፖሊዮን ዘመን ድረስ መመሰቃቀል ቢፈጠርም ከነጻነት አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ የማህበረሰቡን አደረጃጀት እና አስተሳሰብ አፈራርሰው የንጉሳቸውን አንገት ቀርጥፈው እስከመግደል የደረሱ ናቸው። የነሩሶ ዘመን ድካም ያለውጤት አልቀረም። የዛ ዘመን ማህበራዊ እሳቤ በዛሬው የፈረንሳይ ማህበረሰብ ላይ አሻራውን አላሳረፈም ማለትም አይቻልም።

በቅርቡ እንኳ አውሮፓ በኒዎ ሊበራል ሃሳብ በሚናጥበት ፤ በሚበጠበጥበት ጊዜም ቁርጠኛ አቋም በመውሰድ ለሶሻሊስት መንግስት ድምጽ የሰጠ ነው የፈረንሳይ ማህበረሰብ – ምንም እንኳን የኋላ ኋላ ኦላንዴ ያልታወቀበት ኒዎ ሊበራል እየመሰለ ቢመጣም።

ቁም ነገሩ በፈረንሳይ ለግብረሰዶማዊ ጋብቻ የነበረው ተቃውሞ ስለ ሰው ልጂ መብት አላዋቂነት ስለነበረ አይደለም። የግለሰብ መብት እና የማህበረሰብ ህልውና በሚጣረሱበት ጊዜ ማህበረሰቡ በግለሰቦች ቆዳ እንደማይቀበር ወይንም መቀበር እንደሌለበት ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል። ግለሰብ በነጻነቱ ማህበረሰብን አልነካም የሚባልውስ ምን ሲሆን ነው? የህብረተሰብ ዓይኑ መዛቅ አለበት እንደተነካ ለማረጋገጥ?

የማህበረሰባዊ ህግን ከማፈራረስም ባሻገር አሁን ያለው የኒዎሊበራል ስርዓት የሚያደርገው አዳዲስ ማህበረሰባዊ አደረጃጀቶች ድንበር ውስጥም ሆነ ድንበር ተሻግሮ የሚደረግን የብዝበዛ መዋቅር የሚያግዝ ሆኖ ሲገኝ ይመስላል። እንደዛ ባይሆን ኖሮ የግብረሰዶማውያኖች መብት የፓለቲካ እና የኢኮኖሚ ኃይል ባላቸው ወገኖች ጥበቃ እና ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሁን የደረሰበት ደርጃ ሊደርስ አይችልም ነበር። አፍሪካ አሁን ባለው ልፍስፍስነቷ እና ድህነቷ ላይ ኒዎ ሊበራሎቹ ( የ”ሚስጥር ማህበር አባላት የሚባሉ”) በየሃገሮቹ የመለመሏቸውን “የመብት ተሟጋቾች” ተጠቅመው ይሄንን ልማድ በህጻናት ላይ ጭምር ለማስፋፋት የሚደረገው ዘመቻ የተልፈሰፈሰ እና የተከፋፈለ ማህበረሰብ በመፍጠር የበለጠ ያዳክም እንደሆነ ነው እንጂ ለአፍሪካ ማህበረሰቦች የሚጠቅመው ነገር ያለው አይመስለኝም። ለአፍሪካ ስንት አንገብጋቢ ጉዳይ እያለ ይሄ ጉዳይ እንዴት በአጀንዳነት እንደሚገፋ ራሱ ግራ ያጋባል።
አሁን ያለው የብዝበዛ ስርዓት ለብዝበዛው ስርዓት ጋሬጣ ሊሆን የሚችልን ምንም አይነት ጉዳይ እንደማይምሩ ፤ የጥላቻ ስም እየለጠፉ ጦር እስከመስበቅ የሚደርሱትን ያህል ፤ ለመበዝበዣነት እና ለመከፋፈያነት የሚጠቅማቸውን አስተሳሰብ እና ሁኔታ ደሞ እያሞካሹ ፍጹም ተራማጂ አስተሳሰብ እያደረጉ ማቅረብ ተያይዘውታል። የሚመለምሏቸው “ኤሊቶችም” ስራቸው በየማህበረሰባቸው ፊታውራሪ ሆነው እንዲህ ያለውን ጉዳይ ማራገብ ነው።

ትልቁ ጥያቂ ስለሚመጣው ትውልድ ነው! ለምንድን ነው ልማዱን በህጻናት ጭምር ለማስፋፋት የተፈለገው?!

ስለ ዶሚኒኩ ቨኔ ከታች ያለውን ቪዲዮ ይመልከቱ

ድሜጥሮስ

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here