ኢትዮጵያ ሁለት የኦጋዴን ነጻ አውጪ ከፍተኛ አመራር አባላቶቸን ከናይሮቢ ጠለፈች

(ቦርከና) የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ትላንት በድረ ገጹ ይፋ ባደረገው መግለጫ የ ኢትዮጵያ የደህነነት ሃይሎች ሁለት ከፍተኛ አመራሮቼን ከናይሮቢ ጠለፉብኝ ብሏል።

እንደመግለጫው ሱሉብ አህመድ እና አሊ ሁሴን የተባሉት አመራሮች የተጠለፉት ትላንት ከሰዓት በኋላ ነው። አመራሮቹ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ለሶስተኛ ጊዜ ሊደረግ ታስቦት ለነበረው ድርርድ ያዘጋጀው ቡድን አባላት ነበሩ።

መግለጫው እንዲህ አይነት ጠለፋ ሲደረግ የመጀመሪያ ጊዜ እንዳልሆነ እና እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1998 የኢትዮጵያ ወታደሮች ያላቸው ሶስት የኦጋዴን ነጻ አውጭ ልዑካን አባላትን እንደገደሉ፤ ሁለት እንደጠለፉ እና ከሁለት ዓመት በፊትም አንድ ሌላ ከፍተኛ የግንባሩ አመራር አባል በቅጥር ነብሰ ገዳዮች እንደተገደለ ጠቁሟል።

እንዲህ ያለው ድርጊት ቀጣይ ንግግር ለማድረግ እንቅፋት እንደሚሆን መግለጫው ጨምሮ ገልጾአል። የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ንግግሩን ለማካሄድ ገለልተኛ የሆነ መደራደሪያ መድረክ ለመስጠት ኃላፊነት የወሰደውን የኬንያን መንግስት ጠለፋውን በተሟላ ሁኔታ አጣርቶ ተጠላፊዎቹን እንዲያስለቅቅ ጠይቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.