Wednesday, February 28, 2024
HomeSliderደሴ ፤ ጥምቀት እና ክልላዊነት

ደሴ ፤ ጥምቀት እና ክልላዊነት

ደሴ ውስጥ የሃይማኖት እምነት ጠንካራ የመሆኑን ያህል ሃይማኖት ፈጽሞ ፖለቲካ አልነበረም። በሸኪዎች ይቀለድ ነበር። በቄሶችም ይቀለድ ነበር – እምነታቸውን ከማጣጣል አንጻር አይደለም። የፍቅር እና የጨዋታ ዓይነት ቀልድ ነበር ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወጥቸ ያደርኩት የፋሲካ ለት ነበር። አብረን ስንጫወት አምሽተን ሶስት ሆነን በአንድ አልጋ ላይ ጓደኛችን ቤት ነበር ያደርነው። በፋሲካው ቀን ከእኛ ጋር አምሽቶ ያደረው አንደኛው ጓደኛችን ሙስሊም ነበር ( እንዋር ፌስ ቡኬ ላይ አለ)። ይሄ የሶስት ጓደኛሞች ታሪክ አይደለም። ደሴ የተለመደ ነገር ነው። የጥምቀቱም ማህበራዊ እና ባህላዊ ገጽታ እንዲሁ የክርስርስቲያኑ ብቻ ነው ማለት ያስቸግራል። “ደሴ የፍቅር ሃገር” ሲባል ለማያውቅ ሰው ተረት ይመስላል።

ክልላዊነት

የደሴ ጥምቀት አደባባይ የሚያወጣው ሌላ ትርኢት ጎሳዊ ያልሆነ ክልላዊነት ነው። የየጁ ፤ የራያ ፤ የቦረና የደላንታ ጭፈራዎች የሚገርሙ ትዕይንቶች ናቸው። ድካም የሚባል ነገር የሚያውቁ አይመስልም። አቧራ ይጨሳል። ሁሉም ተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆኑም አማራነት ብሎ “ሴንቲመንት” አልነበረም። ጥምቀት በጉርምስና ዘመናቸው ድንጋይ እስከሚፈናጠር የተራመዱበት ፤ በልጂነት ፍቅር ዓለም ያዮበት ፤ የተጋደሉበትም የልጂነት መንደራቸውን ( “ሀገራቸውን”) የሚያስታውሱበት ፤ ስለ ”ሃገራቸው“ በፍቅር የሚዘፍኑበት ቀን ነው። የቋንቋ መልክ የሌለው ክልላዊ ፉክክሩ ጎልቶ ይታያል። መፎካከሪያው ጀግነነት፤ የጁ እኔ ነኝ ወንዱ! ቦረና እንደዚያው እኔ ነኝ ወንዱ። ራያም እንዲሁ እኔ ነኝ ወንዱ! የሚጨፍሩበት “ፓሽን” ወልደው ትልልቅ ልጆች ላደረሱ አባወራወች ትንሽ ይበዛል ሊባል የሚችል ነው። ፉክክሩ አልፎ አልፎ ወደ አደገኛ የዱላ ጠብ የሚያመራበት ጊዜ ነበረ።

ከነበሩት አካባቢያዊ ጭፈራዎች ለየት ባለ ሁኔታ ይጨፍሩ የነበሩት የትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። የትኛው አድዋ ፤ የትኛው ተምቤን ፤ የትኛው አዲ ግራት እንደሆነ አይታወቅም። ሰፊ ክብ ሰርተው አንድ ላይ ነው የሚዘሉት። እንደማስታውሰው በትግሪኛ የሚጨፍሩት ቀኑን ሙሉ አልነበረም። መጀመሪያ ታቦት ያስገቡና ቤት ደርሰው ምግብ በልተው ተመልሰው ወደ ማታ ላይ በቀጠሮ ቁልፍ የሆነ ቦታ ይዘው ነው የሚጨፍሩት። ከዚያ በኋላ ጨለማ ነው የሚበትናቸው። ሌላው ቀኑን ሙሉ ነው ሲጨፍር የሚውለው።

ጎሳዊ ያልሆነ ክልላዊነት በከተማ ልጆችም የሚንጸባረቅበት መልክ ነበረው። በከተሞች በሰፈር ላይ የተመሰረተ የቡድን ስሜት በባህላችን የነበረው ጠንካራ ክልላዊነት ነጸብራቅ ሊሆን ይችል ይሆናል( ጥናት የሚጠይቅ ነገር ነው)። ይሄኛው ከሌሎቹም የተሻለ ጥሩ የሚመስል ጎን ነበረው፤ ለጎሳም ለአካባቢያዊም ብድናዊ ስሜት ቦታ አይሰጥም። ወላጆቻቸው ከየጁም ይምጡ ከቦረና ወይንም ከትግራይ አንድ ሰፈር እስከሆኑ ድረስ የቡድኑ ማንነት ሰፈራቸው እንጂ ወላጆቻቸው የመጡበት ቦታ ወይንም ወላጆቻቸው የሚናገሩት ቋንቋ አይደለም። ይሄ በሌሎች ከተሞችም የነበረ ነገር ነው። አዲሳባም ፤ ናዝሬትም ፤ ሃረርም ሌላም ቦታ ይኖር ይሆናል።

ደሴ ሶስት ያህል ተፎካካሪ የሰፈር ግሩፖች ነበሩ። አገር ግዛት ፤ አራዳ ፤ ሮቢት። በኋላ ሌሎችም ሰፈሮች በዚሁ መልክ ተደራጂተው ቁጥሩ ጨመረ። ዜሮ ሁለት (ይሄ የነ ፈያራ የነበረው ነው) ፤ ሁለት አራት ፤ ሰኞ ገበያ የቡድን ስሜት ፈጥረው ነበር። ጥምቀት እነኝህ የሰፈር ቡድኖች የሃይል ሚዛናቸውን የሚፈታተሹበትም ነበር። “የለመደው ደም የለመደው” በሚል ጭፈራ ይጀመር እና ማሳረጊያው ፍርክስ ነው።

በተለይ የሚካኤል ታቦት በሚሸኝበት ቀን ጠቡ ያለ ፓሊስ እና ተኩስ ሩምታ እንዲህ በዋዛ አይበርድም ነበር። “የሚካኤል ታቦት ሃይለኛ ነው ደም ካላየ አይገባም” ቀላል በማይባል ሁኔታ የናኘ “ሚት” ነበር። ሚካኤል ሰበብ ተደረገ እንጂ የግሩፕ ጠብ ምክንያቱ የሚንቀለቀል የወጣትነት ወኔ ጋር የተቀላቀለ የባህል ተጽዕኖ ይመስል ነበር። ከክልላዊነት ስሜትም ባሻገር የግሩፕ መሪዎች ፍቅረኛቸውን “ኢምፕረስ” የሚያደርጉበት መንገድ የሚመስልም ነገር ነበረው። በደርግ ጊዜ ጥይት ተተኩሶ ራሱ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ሰው በመንግስት የተገደለበትን ጊዜ አላስታውስም። ወያኔ ሲመጣ የጂል ብትር እንዲሉ (የነሱ የጂልነት ብቻ ሳይሆን ጥላቻም ስላለበት ነው) ልጆች መግደል ጀመሩ።

የደሴ ጥምቀት ከጠብ መልስ ለሶስት ቀን በሚዘልቅ ለዛ ያለው ጭፈራ ፤ በሲሲ ፓራራ ሰበብ በሚፈጠር“ጃም ቡሌ” አይነት ዳንስ ከሚፈጠር ቁርኝትም በተጨማሪ ፤ ደሴ በሞቀ ማህበራዊ ፍቅር የገነባችውን ሞቅ ያለ ማህበራዊ ትስስር ለናሙና አውጥታ ከምታሳይባቸው በዓላት ጥምቀት በርግጠኝነት አንዱ ነው። እርግጥ ከላይ እንዳልኩት የጉርምስና ጠብም ነበር። የጥላቻ እና ሜንጫ የሚያስመኝ ግን አልነበረም። ድንቅ ነበር የደሴ ጥምቀት። ምን ያህል ተለውጧል በእውነቱ የማውቀው ነገር የለኝም።

ድሜጥሮስ ብርቁ

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here