ደሴን ከሚያስታውሱኝ በዓሎች በቀዳሚነት የማስቀምጠው ጥምቀትን ነው። አቧራ ይጨሳል። የጭፈራ አቧራ ይጨሳል፤ የድብድብ አቧራ ይጨሳል፤ የፍቅርም አቧራ ይጨሳል።
ደሞ የፍቅር አቧራ ምንድን ነው? እኔ ራሴ በተመጠነ እና ባልተንዛዛ አማርኛ እንዲህ ነው ልል አልችልም። ሲያዮት ብቻ የሚገባ ነገር አለ መቸስ። እንደዋዛ በ “ሲሲ ፓራራ” አርሞሪካ ጀምረው ወደ ሌላ ዓይነት አርሞሪካ (የፍቅር አቧራው አንድ ገጽታ ነው እንበል) ፤ አልፎም በዚያው ግማሽ በደረሰ ዓመት ወግ ማረግ እስከማየት የሚደርሱ አይጠፉም ነበር።
የፍቅር አቧራ መነሻውም መድረሻውም ፍቅር እንደነበር ከማስታወስ በስተቀር ፤ አሁን የምር ፍቅር “የፋራ” የመሰለበት ዘመን ላይ እንዴት እና በምን ምክንያት እንደደረስን ሊገባኝ አይችልም። ያኔ ሰው ስራ ሳይኖረው የፍቅር ጓደኛ ሊኖረው ይችል ነበር። ግንኙነቱ ራሱ የፍቅር ብቻ አይመስልም ነበር። አጼ ቴዎድሮስ ከእቴጌ ተዋበች ጋር ነበራቸው ወደሚባለው ዓይነት ግንኙነት የሚጠጋ ነበር። በማቴሪያል መላላጥ አለነበረም ያኔ። በዘመኑ ፍቅር ጠንካራ የነበረበት ምክንያት ብዙም ከዘመኑ ልጆች ጋር ላይያያዝ ይችላል። በማህበረሰቡ ውስጥ የነበረው እሴት ሙሉ በሙሉ ስላልወደመ እኛ ያደግንበትን ዘመን በደግ ጎኑ ሳይዋጀው አልቀረም። እንደዛም ሆና ልጆች እያለን ትላልቅ ሰዎች “የዛሬ ልጆች” እያሉ ይማረሩ ነበር፤ ምን ማለታቸው እንደሆነ ዛሬ እንዲህ ሊገባኝ ስለትውልዱ ምርር የሚሉት ነገር አይገባኝም ነበር።
የዛን ዘመን ሰዎች ሳይማሩ እንደፈላስፋ በቀላል የኑሮ ዘየ ለራሳቸውም ፤ ለሰውም፤ ለሃገርም የኖሩ ናቸው። በደስታ ጊዜ ተሰባስበው እንደሚደሰቱት፤ በሃዘን ጊዜም ተሰባስበው ርስበርስ መጽናናት ተክነውበታል (ስብሃት እንዳለው የሃዘን “ቴራፒ” ሊባል የሚችል ነገር ነበረን!)። በሃዘን ጊዜ እንደ “ጠላት” የሚታይ ሰው ሁሉ “ጠላትነቱ” ተረስቶ “በርታ እግዚያብሔር ያጥናህ” ያባት አደር ነው። በአያቴ እድሜ የነበሩ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ሲሉ ሰምቸ አላውቅም፤ አኗኗራቸው ግን ይገልጸው ነበር። የአኗኗር ዘያቸው እና የህይወት ፍልስፍናቸው ኢትዮጵያን ለዘላለም የማኖር ብቃት ነበረው። እንኳን ገጠር እና ደሴ ሰፈር ውስጥ የነበረው ማህበራዊ ትስስር ለየት ያለ ነበር።
በኛ ዘመን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ለነሱ ቀላል ወይንም ምንም ማለት አልነበረም። ገጠር ያለ ዘመድ የመንደሩ ሰዎች ከተማ የሚያስኬድ ጉዳይ ያላቸው ከሆነ ከተማ ያለ ዘመዱ ጋር አምስት ስድስት ሰው ሰብሰቦ ሲልክ ምንም አይመስለውም። ይሉኝታ ከማጣት አልነበረም። የከተማን የኑሮ ጫና ካለመረዳትም አይመስለኝም፤ የሆነ ነገርም አብሮ ይልካላ! ለሰው መቸገርን እግዜር የሚወደው ነገር ነው ከሚል እምነት ሊሆን ይችላል። “ለሰው መድሃኒቱ ሰው ነው” የሚል ማህበራዊ ፍልስፍና እና እምነት ተጽዕኖ ስለነበረ ይሆናል። ለነሱ ሃገር ማለት ሰውም እንደሆነ በውል የገባቸው ይመስላል። “ሃገራቸው” ደሞ የገጠር መንደራቸው። ኢትዮጵያ የሚባል ነገር አያውቁም ለማለት አይደለም። በጭራሽ። ስለ አካባቢያዊነት የሚሰማቸው ጠንካራ ስሜት ለመግለጽ ያህል ነው። (በነገራችን ላይ “አካባቢያዊነት” በልጽገዋል በሚባሉትም ሃገሮች ዛሬም ድረስ ጠንካራ ነው።)
ከተማ ያለው አስተናጋጁ ዘመድ ባብዛኛው የሚያደርገው ነገር ቢኖር አንጥፈው የሚተኙበት ነገር እና የማይለበስ ልብስ ካለ ፈላልጎ መስጠት ነበር። እስቲ በፍልስፍና ዘይቤ እዮት! ማረፊያ የለኝም ለሚል “ያገር” ሰው “የኔ ወንድም አለ። እሱ ጋር ታርፋላችሁ” ብሎ በ”ኮንፊደንስ“ እንደመላክ ነው። ወንድምየውም ተቀብሎ ካላስተናገደ ከወንድሙ ጋር ሊቆራረጥ ሁሉ ይችላል። ማህበራዊ ትስስራቸው “ወገን” የሚለውን ሳያዛንፍ ሊገልጽ የሚችል ነው። አልፎ አልፎ የሚኖረው ግጭት እንደተጠበቀ ሆኖ ግንኙነታቸው ፍቅር እና መረዳዳት ይጫነው እንደነበር ለመረዳት አዋቂ መሆን አይጠይቅም። ለሰው ከሚሰጥ ዋጋ የሚመነጭ ይመስለኛል። በእኛን ዘመን ለምን ዋጋ እንደሚሰጥ የታወቀ ነው። እንደሌላው በአፍ ስለማይሉት እና ስለኖሩት አላስታውቅ ብሎ ይሆናል እንጂ የኖሩት ህይወት ወንጌላዊነት ይንጸባረቅበታል። ሰውን ለመውደድ የሰውነት ትርጉም እና የእምነት ትርጉም ዘልቆ እንዲገባ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። አኗኗራቸው የክርስቶስን ትምህርት ከህይወት እስከሞት ቃል በቃል የወሰደ የኑኖ ዘየ ይመስል ነበር። የነሱ አባቶች አገር አዳኝ አርበኛ የነበሩበትም አንድ ሚስጥር ይሄ ሊሆን ይችላል። ስለ ሰው እና ስለ ሃገር ብዙ ነገር ይሆናሁ። በተቃራኒው የእኛ ትውልድ ስለ “ማቴሪያል” የማንሆነው የለም። እንኳን እምነቱን እና ሀረሩን፤ ራሱን ይሸጣል። ለነገሩ “ራስ” ያለእምነት እና ያለሃገር ምንድን ነው?
ባለንበት ዘመን “የሰብአዊ መብት” ዲስኩር ጆሮ የማደንቆሩን ያህል (በሃገር ውስጥም በዓለም ዓቀፍ ደረጃም)፤ ከመንግስታት ጀምሮ እስከ ግለሰቦች ድረስ ስለ ሰው ልጂ መብት የሚደሰኮረውን ያህል (ያውም እየተመረጠ) በምግባር ደረጃ ግን ተማረ ከሚባለው ሰው ጀምሮ በተጨባጭ የሚደረግ ነገር የለም ። ማድረጉ ቀርቶ አሰቃቂ ግፍ የሚፈጽም አለ፤ ለመፈጸም የሚመኝም አለ። እንደ አሜሪካ ያሉ ሃገሮች በጎን ስለህጻናት መብት ይደሰኩራሉ ፤ በጎን ደሞ እንደ ኢራቅ፤ አፍጋኒስታን ፤ ሊቢያ ያሉ ሃገሮች ላይ በሰበቁት ጦር ምክንያት ሰለጨረሷቸው ህጻናት እንዲወራ እንኳ አይፈልጉም። ስለሴቶች መብት ይደሰኩራሉ ፤ እንደቀላል ነገር በቀጭን ትዕዛዝ በሚያስጀምሩት ጦርነት የሚያልቁ ሴቶች አይቆጠሩም። የሰው አንገትን ለሜንጫ የሚያስጎመጂ አድርጎ የሚደሰኩር ለወትሮው ስለ ሰብዓዊ መብት የሚደሰኩርም ከራሳችን ማህበረሰብ የወጣ (በአካል)ሰምተናል።
የእኛ ዘመን ትልቅ ችግር ከሚመስለኝ አንደኛው ነገር ምንም ወይንም ጥቂት አዋቂ ሆነን ሳለን “እንደበቃ እንደነቃ” ሆነን የፍትህ እና የእውቀት መለኪያ ሚዛን የምንሆንበት አይና ያወጣ ፈጣጣነት ነው። ከተከታይ ጋር ሆኖ ሃገር ማጥፋት የሚመጣው በዚህም መልክ መሰለኝ።
አሁን በዘመቻ መልክ የኦሮምኛና የአማርኛ ተናጋሪዎች እንዳይታረቁ ሆነው እንዲጋጩ ፤ ሃገር እንዲታወክ ለተፈለገበት የሚሰጠው አንደኛ ምክንያት በአዋቂነት መንፈስ የሚሰጥ የታሪክ ትንተና ነው። የሁለቱ ቋንቋ ተናጋሪዎች ግን የሚባለው ዘመን ታሪክ ጠባሳ ሳይገድባቸው ከዛ በኋላ ተጋብተው ተዋልደዋል። ደሴ መድሃኒያለም የአያቴ ማህበር ነበር። ብዙዎቹ የማበሩ አባሎች በውትድርና ሃገራቸውን ያገለገሉ የመሃልም የዳር ሃገር(ድሮ እንደሚባለው) ሰዎችም ነበሩ። ሻምበል ዘለቀ ዝቄ ባልሳሳት (ድንገት ይሄን የሚያነቡ የልጂ ልጆች ካሉ ሊያርሙኝ ይቻላሉ) የወለጋ ሰው ነበሩ ፤ ሻምበል ባሻ ጨዋቃ መልካ እንዲሁ የኦሮምኛ ተናጋሪ ነበሩ። አሁን የማላስታውሳቸው ሌሎችም ነበሩ። በማህበሩ ያሰባሰባቸው ሃማኖት ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ፍቅርም ነበር። የሚጋሩት አብረው የደከሙበት የጋራ የሃገር ጉዳይም ነበር። አሁን የሚነዛው ዓይነት የጥላቻ ስሜት ቢኖር ኖሮ በፍቅር አንድ ማህበር መጠጣት ባልተቻለ ነበር።
በሌላኛው የማህበራዊ ገጽታ ስናይ ደሴ ውስጥ በቀበሌ ደረጃ በሊቀመንበርነት በሌላ መልክ ያገለግሉ የነበሩ ከኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ አካባቢ የመጡ እንደነበሩ አስታውሳለሁ። በህብረተሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበራቸው የሚከበሩ ነበሩ። ኤርትራዊ ተብለው በኋላ ወያኔ እያነቀ እየጫነ ወደ አስመራ የላካቸውም እንዲህ ባሉ ቦታዎች እንዳገለገሉ አውቃለሁ። በደሴ ማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ አክብሮት የነበራቸው ፤ ማህበራዊ ተጽዕኖ የነበራቸው የሚያሸማግሉ ሁሉ ነበሩ። ብርሃኑ ፈይሳ ( በቅጽል ስሙ ፈያራ ይባል ነበር) ከእኛ ተቀራራቢ የሆነ እድሜ ላይ ያለ የደሴ ልጂ ነው። ያለ ልክ እልሀኛ። ያለ ልክ ወኔያም! የተወጋበትን ጩቤ ከተወጋበት ቦታ ነቅሎ የወጋውን አሯሩጦ እንደወጋ ይነገርለታል። ጥሩ ተከላካይም ነበር። ለኢትዮጵያ ብቤራዊ ቡድንም ተጫውቷል። እንደሁላችንም የሱም ዓለም ደሴ ነበረች ለጊዮርጊስ ክለብ ሊጫወት እስከሄደበት ድረስ። የኦሮሞ ጠበቃ ነን በሚል በብልጠት ግጭት እየፈበረኩ ያሉት የሳቱት ታሪካዊ ውል ብቻ አይደለም። በሚሊዮን የሚቆጠር የፈያራ አይነት ታሪክም ነው። የፈያራ አይነት በጎሳ ላይ ተተብትቦ ያልቀረ ማንነት ያላቸው ሰዎች ሞልተዋል። ከጎሳዊ መንደራቸው ሳይወጡ እዚያው ለሚኖሩትም ቢሆን የጎሳ ግጭት እየተደገሰላቸው ለመብታችሁ እየታገልንላችሁ ነው እየተባሉ ሊፌዝባቸው ባልተገባ። (ወደ ሚቀጥለው ገጽ ዞሯል)