Tuesday, March 21, 2023
HomeEthiopian Newsፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከብዝበዛ በማዳን ታሪክ እንዲሠሩ ተጠየቁ

ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከብዝበዛ በማዳን ታሪክ እንዲሠሩ ተጠየቁ

  • ‹‹ዐይናችን፣ ጆሯችንና ልባችን የቤተ ክርስቲያናችንን ህልውና በሚወስነው የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ተግባራዊነት ላይ ነው፤ የቤተ ክርስቲያናችን ትንሣኤ ደርሷል ብለን እናምናለን፡፡›› /ምእመናን/
  • ‹‹ከእውነተኛ የቤተ ክርስቲያኒቷ ጥቅም ወዲያና ወዲህ አልልም፤ አትጠራጠሩ! ሕጉ የጠራ ኾኖ በትክክሉ ይወጣል፤ ቤተ ክርስቲያናችን ወደቀደመ ክብሯ ትመለሳለች፡፡›› /ፓትርያርኩ/

(ሰንደቅ ጋዜጣ፤ 9ኛ ዓመት ቁጥር 436፤ ጥር 07 2006 ዓ.ም.)

በጋዜጣው ሪፖርተር

‹‹የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ከመሠረታዊው ተልእኮው ጋራ ያልተቀናጀ ከመኾኑም በላይ በወገንተኝነትና በሙስና የሚፈጸሙ የተለያዩ የሥነ ምግባር ብልሽቶች በስፋት የሚንጸባረቁበት ኾኖ ይስተዋላል፡፡ ይህን ከቤተ ክርስቲያኒቷ ክብርና ቅድስና ጋራ የማይጣጣም ሒደት ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይ ርምጃ ሊወስድበት ይገባል፡፡ አስፈላጊው እርማት በወቅቱ ሳይደረግ በመቅረቱ፣ ምእመናኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ላይ እምነት ማጣትን እያሳደረ ኹኔታውም እየተባባሰ ሲሔድ ይታያል፡፡ ስለዚህ ታሪክ እንዳይፈርድብን ካህናቱንና ምእመናኑን በማስተባበር አስቸኳይ የእርምት ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ይኾናል፡፡››

ይህ ጥቅስ አቡነ ማትያስ ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኾነው ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያቸውን የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሁለተኛ ዓመታዊ ስብሰባ ግንቦት 22 ቀን 2005 ዓ.ም. በንግግር ሲከፍቱ ካሰሙት ቃል የተወሰደ ነው፡፡

ፓትርያርኩ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም ለመጠበቅና የቀደመ ክብሯን ለመመለስ›› ሥር ነቀል የለውጥ ርምጃዎች እንደሚወስዱ ባስታወቁበት በዚያ የመክፈቻ ንግግራቸው÷ የቅ/ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ብልሹ አሠራርን ለማረምና ለማስወገድ፣ አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ለማዋቀርና ለፋይናንስ አያያዙ ዘመናዊነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አደረጃጀት ለመዘርጋት የሚያስችሉ ሦስት መሠረታዊ ርምጃዎችን እንደሚወስድ አመልክተው ነበር፡፡

አቡነ ማትያስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጤናማ ሒደት የሚወስኑ ናቸው ካሏቸው ሦስቱ መሠረታዊ ርምጃዎች ጋራ በተለይም ልዩ ሀገረ ስብከታቸው በኾነው በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት እየገዘፈና እየተመሰቃቀለ የመጣውን የመልካም አስተዳደር ዕጦትም በአደረጃጀቱና አሠራር ለውጥ ማስተካከል አስፈላጊ መኾኑን አሥምረውበት ነበር፡፡

ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ግልጽ የአስተዳደር ሥርዐት የሚሰፍንበትን የለውጥ መሠረት በአስቸኳይ ማስቀመጥና አቅጣጫውን መቀየስ ‹‹በእግዚአብሔር፣ በታሪክና በመጪው ትውልድ ፊት›› ኹልጊዜ በሚዛን እየተመዘነ እንደሚኖር መዘንጋት እንደሌለበት ፓትርያርኩ ያሳሰቡት ለቅ/ሲኖዶሱ አባላት ጭምር ነበር፡፡  የበለጠ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here