Thursday, July 18, 2024
HomeAmharicአፈንዲ ፣ ጃዋር መሐመድ እና የቴዲ አፍሮ ጉዳይ

አፈንዲ ፣ ጃዋር መሐመድ እና የቴዲ አፍሮ ጉዳይ

የሰሞኑ የነ ጃዋር ሲራጅ ግርግር ለኛም ስም አትርፏል፡፡ እንደፈቀደው ይሁን፡፡ እኛ ጉዳያችን ሞልቶልናል፡፡ የታቀደው የቴዲ ኮንሰርት በመሰረዙ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ በኮንሰርቱ ታክኮ ሊከሰት የሚችለው የህዝብ መተላለቅ በመቅረቱ እሰየው ነው፡፡ ብርና ዝና ብቻ እያሰቡ የህዝብ መጨራረስን ሊጋብዙ የነበሩ ሰዎች ተንኮላቸው ስለከሸፈባቸው አላህን በጣም ነው የምናመሰግነው፡፡

ታዲያ ያስገረመኝ ነገር ስሜት እውነትን ለመሸፈን ምን ያህል ጉልበት እንዳለው መረዳቴ ነው፡፡ አጃኢብ ነው! ግጭትና ትርምስ ሲሰበክ የነበረው በውሸት የተፈጠረውን ወሬ እንደ ሰበብ በማድረግ ነው፡፡ ውሸቱን ለማዳመቅ በግርግሩ ውስጥ የገቡ ሀይሎች አበዛዝም ያስገርማል፡፡ ከአሜሪካ እስከ ኖርዌይ፣ ከለንደን እስከ ሸገር እየተጠራሩ ሽብሩን ለማጋጋል የተደረገው ጥረት አስደናቂ ነበር፡፡ ለወትሮው በአንድ ብሄር ላይ የሚደረግ ዘረኛ ቅስቀሳን እንቃወማለን ሲሉ የነበሩ አንዳንድ ምሁራን ደግሞ ከኛ ጋር ተባብረው ግጭት እንዳይከሰት ጥረት ያደርጋሉ ብለን ስንጠብቅ የኛ ተቃራኒ መሆናቸው አስገርሞናል፡፡ ለምሳሌ እነ ዳንኤል ብርሃኔ “ቀኝ አክራሪዎች እንዲህ አደረጉ” እያሉ ሲጽፉት የነበረው ነገር በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ነገሮችን በስሜት በመቀበል እውነትን ከውሸት ለመለየት ጥረት አለማድረጋቸው አስቂኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ ሆኖ ነው ያለፈው፡፡ ለምሳሌ በግርግሩ መጀመሪያ ሰሞን “መጽሔቱ ቃለ-ምልልሱን አትሞ አውጥቶታል” ሲባል ከርሞ “ሁለት ዓይነት መጽሔት ነው የታተመው” የሚል ነጠላ ዜማ ተለቀቀ፡፡ ከዚያ ለጥቆም “መጽሔቱ አከራካሪውን ቃለ-ምልልስ ቆርጦ አስቀርቶታል” ተብሎ ተወራ፡፡ “የተቆረጠው ክፍልም ይኸውላችሁ” ተብሎ በአንዳንድ ዌብሳይቶች ላይ ተለጠፈ፡፡ በመጨረሻው ላይ ጭራሽ የቴዲ አፍሮ ቃለ-ምልልስ በኦዲዮ ተቀርጾ በእጃችን ገብቷል የሚል ማስመሰያ ተፈጠረ፡፡ ይህ ሁሉ የውሸት ወሬ ነው፡፡ በግርግሩ የተሳተፉት ግን አንዱንም ለማጣራት አልሞከሩም፡፡ “ጀዋር የተናገረው ነገር ምንጊዜም እውነት ነው” የሚል መመሪያ ያላቸው ነው የሚመስለው፡፡ (ያሳቀኝ ነገር ቴዲ አፍሮ ራሱ መጽሔቱ “ቅዱስ ጦርነት” በሚለው ርዕስ አለመታተሙን ያላወቀ መሆኑ ነው፤ እንደዚያ ዓይነት ርዕስ ያለው መጽሔት በጭራሽ አልታተመም)፡፡

እኛ ለቴዲ አፍሮ አልነበረም የተከራከርነው፡፡ ቴዲ ተናገረ የተባለው ቃል ትክክል ነው ያለ ሰው የለም፡፡ በደሌ መጠጣትን አቁሙ መባሉንም የተቃወመ ሰው የለም (እኛ እንዲያውም አስካሪ መጠጥ የተባለ በሙሉ ቢወገድ ነው የምንፈልገው)፡፡ እኛ ያልነው በሀሰተኛ ወሬ ሰውን ለማጨራረስ አትሞክሩ ነው፡፡ ይህንን ሀሰተኛ ወሬ የሚያራግቡ ሀይሎች ድብቅ አጀንዳ አላቸው ነው ያልነው፡፡ ይኸው ነው መልዕክታችን፡፡

ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ቴዲ አፍሮ በትክክል “ቅዱስ ጦርነት” የሚለውን ቃል ተናግሮ ቢሆን እንኳ መደረግ የነበረበት በፍትሕ መንገድ መፋረድ ነው፡፡ ሆኖም የግርግሩ አድማቂዎች በቀጥታ ወደ ዘረኝነት ቅሰቀሳ ነው የገቡት፡፡ ያሳዝናል! የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ወግ ይህ አልነበረም፡፡ የህዝቡ ትግልም ከስርዓቶች ጋር ነው እንጂ ከሰፊው የአማራ ህዝብ ጋር አይደለም፡፡

በኔ በኩል የምችለውን አድርጌአለሁ፡፡ በአላህ እርዳታ የምፈልገውን ውጤት አግኝቼበታለሁ፡፡ ህዝቦቻችን አልተገዳደሉም፡፡ አልተፋጁም፡፡ እነርሱ እንደተመኙት አልተጨራረሱም፡፡ ስለዚህ ባደረግኩት ነገር ደስተኛ ነኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ቅንጣት ታክል ጸጸት አይሰማኝም፡፡ ወደፊትም እንዲሁ ማድረጌን እቀጥላለሁ፡፡

===መነሻው===

ይህንን ሁሉ ትርምስምስ በአጋፋሪነት የመሩትን እናውቃቸዋለን፡፡ ሁሉም በውጪ ሀገር ተቀማጭ ሆነው ነበር እሳቱን ሲያጋግሉት የነበረው፡፡ ዓላማቸው ሰሞኑን የፈጠሩት የሰንበቴ ማህበር ግዙፍ ስኬት እያስመዘገበ እንደሆነ እንደ መጠቆሚያ አድርጎ መጠቀም ነው፡፡ ህዝብ ቢጨራረስ ባይጨራረስ ጉዳያቸው አይደለም፡፡

የግርግሩ ዋና አቀናባሪ ማን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እንደ ቃል አቀባይ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ግን ጀዋር መሐመድ ነው፡፡ ጀዋር በቅድሚያ ስለጉዳዩ በኔ ኢንቦክስ ሲነግረኝ “የእንቁ መጽሔት ባለቤቶች ጎል ሊያስገቡን የውሸት ሽፋን በፎቶሾፕ ሰርተው በትነዋል” ነው ያለኝ፡፡ እናም “ይህንን መጽሔት መበቀል አለብን” በማለት ሊቀሰቅሰኝ ሞከረ፡፡ “እንቁ ማለት የማይታወቅ መጽሔት ነው፤ ነገሩን ባናጋግለው ይሻላል” አልኩት፡፡ እርሱ ግን “አይደለም! በጣም ግዙፍ የሆኑ ነፍጠኞች ናቸው በገንዘብ የሚደጉሙት” ብሎ ሊያነሳሳኝ ሞከረ፡፡ እኔ በበኩሌ የሰውዬው አጉል ብልጠት ስለሚደብረኝ ግድ አልሰጠሁትም (እርሱ የሚያወራውን ነገር ሁልጊዜ በጥርጣሬ ነው የማየው)፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱን ላለመገናኘት ስሸሸው ቆየሁ፡፡ በዚህ መሀል ቴዲ ሰጠ ስለተባለው ቃለ-ምልልስ ሐቁን ለማወቅ ጥረት አድርጌ ነበር፡፡ እናም ውሸት መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡

ታህሳስ 14/2006 ከጀዋር ጋር በሌላ ጉዳይ ስንገናኝ ግን ቀደም ሲል ውሸት ነው ሲለው የነበረውን ነገር “እውነት ነው! የኦዲዮ ማስረጃ ጭምር አለን፤ የመጽሔቱ አዘጋጅ ማረጋገጫ ሰጥቶኛል” የሚል ማሻሻያ ሰጥቶት ከርሱ ጋር እንድሳተፍበት ይጨቀጭቀኝ ጀመር፡፡ ነገሩ ውሸት ነው ሳልለው “ይህንን ነገር ከማጋጋል መቆጠቡ ይመረጣል” ብዬ ላቀዘቅዝ ሞከርኩ፡፡ እርሱ ግን “እምቢ! ቴዲን አፈር አባቱን ሳናበላው አንተወውም፤ አንተ ደስ ካለህ እንደ ፈለግክ ሁን” እያለ ይፎክርብኝ ገባ፡፡ ለፉከራው ግድ ባይኖረኝም ለራሱ ዝና ሲል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሞ ወጣቶች ዘንድ ያገኘውን ተቀባይነት በመጠቀም ስለሜንጫው የፎከረውን ቃል ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል ብዬ ፈራሁ፡፡ እና የርሱን እንቅስቃሴ የሚያኮላሽ እርምጃ መውሰድ አለብኝ በማለት ወሰንኩኝ (በወቅቱ እኔም እንደርሱ በቢራ የምንቦጫረቅ መስሎት “በደሌ መጠጣት አቁም” ሲለኝ ለጥቂት ነበር ከመሳደብ ራሴን የተቆጣጠርኩት!)፡፡
***** ***** *****
ይህ ሰው በጣም አጭበርባሪ ነው፡፡ የውሸት ወሬ መፈብረክ ይችልበታል፡፡ ደግነቱ የሚፈበርካቸውን ወሬዎች ሀሠትነት ለማረጋገጥ ረጅም ጊዜ አይፈጅም፡፡ የዚህ ሰው ሌላኛው ባህሪ ደግሞ ለሁሉም የፖለቲካ ቡድኖችና ፓርቲዎች የሚሰራ መሆኑ ነው፡፡ ሰውዬው ከላይ ሲታይ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ይመስላል፡፡ ሆኖም አብዛኛው ሰው እንደሚያውቀው ከኦፒዲኦ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋርም የጠበቀ ግንኙነት አለው፡፡ አንድ ቀን ሳያስበው ይህንን ግንኙነቱን ግልጽ ያደረገበትን ጥያቄ ጠየቀኝ፡፡ እኔ በሰጠሁት ምላሽ ሳስደነግጠው ትንሽ እንደማፈር ብሎ ዘጋው (በወቅቱ የጠየቀኝን ጥያቄ ሌላ ጊዜ ብነግራችሁ ይሻላል)፡፡ በርሱ ቤት ነገሩን የማላውቅ መስሎታል፡፡ ይሁንና በፌስቡክም ጭምር በሰፊው ሲባል የነበረ ነገር በመሆኑ ብዙም አልደነቀኝም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሰው ከኦነግ-ቀመስ ቡድኖችም ጋር በትክክል እንደሚሰራ መረጃው አለን፡፡ ከሻዕቢያ ጋር እንደሚሰራም ውስጥ ውስጡን ይወራል፡፡ እነዚህ ግንኙነቶቹ ቀደም ብዬ የሰማኋቸው በመሆኑ ብዙም አላስገረሙኝም፡፡ በጣም የተደነቅኩት ግን “ነፍጠኛ” እያለ ቀን ከሌሊት ከሚሰድባቸው ቡድኖችም ጋር የሚሰራ መሆኑን እራሱ በነገረኝ ጊዜ ነው፡፡ የዚያን ቀን በጣም ነበር የደነገጥኩት (ዕለቱ ህዳር 7/2006 ነው)፡፡ “ይህ ሰው ጥቅም ካገኘ ለሰይጣንም ይሰራል ማለት ነው ለካ!” በማለት ተደመምኩበት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከዚህ ሰው ጋር የማደርገውን የመልዕክት ግንኙነት ገታ ማድረግ ጀመርኩ (እንግዲህ ለዚህ ሁሉ ማስረጃው በእጄ ነው ያለው)፡፡

ሰውዬው ከነዚህ ሁሉ ቡድኖች ጋር የሚሰራበት ዓላማ ገንዘብና ዝና ማግኘት ይመስለኛል፡፡ በየሀገሩ እየዞረ ብር እንደሚለቅምም ይታወቃል፡፡ እኔ በበኩሌ በግርግሩና በጉዞው ብር ቢያገኝበት ጉዳይ የለኝም፡፡ ብር አገኝበታለሁ ብሎ የማይገባ ድራማ ሲጫወት ግን ዝም ብዬ ላልፈው አልፈቀድኩም፡፡ የጸረ-በደሌውን ዘመቻ በጎን በኩል የተጋፈጥኩት በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ አስቡት እስቲ! የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት ለመታደም ድሬዳዋ ስቴድየም በተገኘው ህዝብና እርሱን በሚቃወመው ህዝብ መካከል ግጭት ቢፈጠር ውጤቱ ምን ሊሆን ነው? በዚያ ውጤትስ ተጠቃሚ የሚሆነው ማን ነው? አማራው ነው? ኦሮሞው ነው? ወይንስ ማን ነው? እስኪ እናንተው መልሱት፡፡ … የጃዋር የፖለቲካ ተንታኝነት ይህ ነው እንግዲህ!…(እንኳንም ኮንሰርቱ ቀረ! እሰይ!)

ከዚህ ሰው ጋር የተዋወቅኩት በኢንተርኔት ነው፡፡ የምጽፋቸውን ጽሑፎች በዌብሳይቱ ለመጠቀም በፈለገበት ጊዜ ሲያነጋግረኝ ነው ያወቅኩት፡፡ ከዚያ ውጪ ሌላ ትውውቅ የለንም፡፡ ለአንድም ቀን አይቼው አላውቅም፡፡ እኔ የጻፍኳቸውን ጽሑፎች ከኔ የፌስቡክ ፔጅ ላይ እየወሰደ ዌብሳይቱ ላይ ይለጥፋል፡፡ በቃ ይኸው ነው፡፡ ባለፈው ክረምት ደግሞ “ያንተን መጽሐፍ እናሳትማለን” የሚል ቃል ሰጠኝ፡፡ በጥቅምት ወር መጨረሻ ገደማ ግን የመጽሐፉ ጉዳይ ቀረና መጽሔት እንጀምራለን ብሎ መጣ፡፡ የመጽሐፉ ጉዳይ መቅረቱ ሆዴን እየበላኝ ብቸገርም እስቲ ትንሽ ልመርምረው ብዬ አብሬው ሰነበትኩ፡፡ ይሁንና ከህዳር ወር 10/2006 ወዲህ የመጽሔቱም ነገር የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ (የማያደርገውን ነገር በስሜት የሚያወራው እንዲህ ዓይነቱ ቀጣፊ ሰው በድሬዳዋ ልጆች ቋንቋ “ሐጂ ቅደደው” ወይንም “ሐጂ ቦንባ” ነው የሚባለው)፡፡

የሆነ ሆኖ የአሁኑ ግርግር ከዚህ ጉዳይ ጋር አይገናኝም፡፡ መጽሔት እናዘጋጃለን ብዬ የለፋሁበትን ድካም መና ስላስቀረብኝ ቂም ቋጥሬ አይደለም ልጋፈጠው የወሰንኩት፡፡ እርሱ ያመጣው ሎጂክ እጅግ አደገኛና ህዝቦችን የሚያጨራርስ በመሆኑ ነው ዝም ማለቱን ትቼ በቀጥታ የገባሁበት (መጽሔቱን በራሴ ወጪ ይፋ አደርገዋለሁ)፡፡ (ወደ ሚቀጥለው ገጽ ዞሯል)

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here