Friday, June 21, 2024
HomeAmharicአንድነት ነባር አመራሩን በወጣቶች ተካ

አንድነት ነባር አመራሩን በወጣቶች ተካ

በዘሪሁን ሙሉጌታ

 

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሦስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ካካሄደ በኋላ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውን በፕሬዝደንትነት ቢመርጥም በቀረው የፓርቲው አመራር ቦታ ላይ አዳዲስና ወጣት አመራሮችን በነባሮቹ ተክቷል።

ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ ቪው ሆቴል በተካሄደ ሥነስርዓት ላይ በፓርቲው ሕገ-ደንብ መሠረት በጠቅላላ ጉባኤው የተመረጡት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ለ13ቱን ቋሚ ኮሚቴዎች የሚመሩ 13 የካቢኔ አባላትን ለብሔራዊ ም/ቤቱ አቅርበው አፅድቀዋል። ሁለት ቀሪ የካቤኔ አባላትን በይደር ለሌላ ጊዜ አስተላልፈዋል።

በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ፓርቲውን በስራ አስፈፃሚነት (ካቢኔ አባልነት) የሚመሩ ተቀዳሚ ም/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌ በቀለ፣ አቶ በላይ ፈቃዱ ም/ል ሊቀመንበር፣ አቶ ስዩም መንገሻ ዋና ፀሐፊ፣ አቶ ዳንኤል ተፈራ የድርጅት ጉዳይ፣ አቶ ሃብታሙ አያሌው ህዝብ ግንኙነት፣ አቶ ሰሎሞን ስዩም የፖለቲካ ዘርፍ አላፊ፣ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ዳዊት አስራደ የኢኮኖሚ ጉዳይ ኃላፊ። አቶ አለነ ማዕጠንቱ የማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ አስቻለው ከተማ የፋይናንስ ጉደይ ኃላፊ፣ ወ/ሮ የትናየት ቱጂ የሕግና ሰብአዊ መብት ኃላፊ፣ አቶ ትዕግስቱ አወሉ የአዲስ አበባ ሰብሳቢ በመሆን የስራ አስፈፃሚ አባል ሆነው ተመርጠዋል። በቀጣይም የወጣቶችና የሴቶች ጉዳይ ኃላፊዎች የሚመረጡ ይሆናል።

አዲሱ ካቢኔው በዕድሜ ከ28 እስከ 35 የሚሆኑት ከአጠቃላይ የስራ አስፈፃሚ አባላት 60 በመቶ ሲሆኑ፤ ዕድሜአቸው ከ40 እስከ 45 የሚሆኑ 26 ናቸው የተቀሩት ከ50 እስከ 65 የሚሆኑ ደግሞ 13.3 በመቶ እንደሆኑ ተገልጿል። በትምህርት ዝግጅት ረገድ ከአጠቃላይ የስራ አስፈፃሚ አባላቱ 7ቱ የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፤ 4ቱ የመጀመሪያና ሁለቱ ዲፕሎማ መሆናቸውም ተገልጿል። የሥራ አስፈፃሚ አባላቱ የተመረጡት ከ44 የብሔራዊ ም/ቤት አባላት የ39ኙን ድጋፍ ሲያገኙ የአንድ ተቃውሞና በሦስት ድምፀ-ተአቅቦ ነው የተመረጡት።

በአሁኑ የሥራ አስፈኀሚ አባላት ምርጫ የብሔር ተዋፅኦ ትኩረት እንዳልተሰጠው ተገልጿል። በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው ፓርቲው በብሔረሰብ እኩልነት እንጂ ስልጣንን በብሔር በማከፋፈል አያምንም፣ ነገር ግን ፓርቲው ሥልጣን በብቃትና ችሎታ ስለሚያምን ለብሔር ተዋፅኦ ትኩረት አለማድረጉን አስረድተዋል። በሀገሪቱ ከ80 በላይ ብሔረሰቦች ቢኖሩም በ13 ሥራ አስፈፃሚዎች ውስጥ ሁሉንም ብሔረሰብ መወከል አይቻልም ብለዋል። ያም ሆኖ እንደ አጋጣሚ ቢሆን በሀገሪቱ ያሉ አብዛኛዎቹ ብሔረሰቦች የተካተቱበት ሥራ አስፈኀሚ መመስረቱ ተገልጿል። በሴቶች ተሳትፎ ረገድ ቀደም ሲል የነበረው የሥራ አስፈፃሚ አንድም ሴት ባይኖረውም በአሁኑ ግን አንድ ሴት ማሳተፉን አቶ ሐብታሙ በጥሩ ጎኑ ሊታይ እንደሚችል ተናግረዋል። የሴቶች ተሳትፎ ችግር የአንድነት ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱም ችግር እንደሆነ ጠቅሰው ገዢው ፓርቲ እንኳ ከ60 በላይ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች ቢኖሩትም የሴቶች ተሳትፎ በቁጥር ከስድስት አይበልጥም ብለዋል።

በቀጣይ አዲሱ የሥራ አስፈፃሚ በርካታ ተግዳሮቶች ከፊቱ መቆማቸው እየተገለፀ ነው። በተለይ የ2007 ምርጫ መቃረብና የፓርቲዎች የውህደት ጥያቄ ቀዳሚ ጉዳይ ነው። አዲሱ የስራ አስፈፃሚ ከፓርቲዎች ጋር መዋሃድን ቀዳሚ አድርጎ እንደሚሰራና ከማይዋሃዳቸው ፓርቲዎች ጋር መዋቅራዊ ባልሆነ ሁኔታ በትብብር ለመስራት መዘጋጀቱን ከአቶ ሀብታሙ ገለፃ መረዳት ተችሏል። በተጨማሪም ኢህአዴግ ከያዘው አምባገነናዊ አውራ ፓርቲ ግትር አቋም ሀገሪቷን ወደ ቀውስ እያመራ በመሆኑ ወደ ድርድር እንዲመጣ ሥራ አስፈፃሚው የበኩልን ጥረት ያደርጋል ያሉት አቶ ሐብታሙ፤ ድርድር ሲባል ስልጣን መከፋፈል አለመሆኑ ታውቆ በምትኩ በሀገሪቱ ነፃ የዴሞክራሲ ተቋማት ለማረጋገጥ፣ ከሕግ የበላይነት ጋር በተያያዙ ጥያቄዎች ላይ፣ የታሰሩ ፖለቲከኞች ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጓቾች ጉዳይ ለመወያየትና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠርም ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

ከመድረክ ጋር ስላለው ግንኙነት በተመለከተ በጉባኤው በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት በሦስት ወር እልባት እንደሚሰጠው የጠቀሱት ህዝብ ግንኙነቱ ከመድረክ ጋር የሚኖረው ግንኙነት በውህደት ሊፈታ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅትም የመድረክ አባል የውህደት ድርድሮችን እያደረጉ መሆኑንም አስረድተዋል። ከመድረክ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችም ቢሆኑ አንድ ግዙፍ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ አንድነት ግፊት ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል።

ምንጭ – ሰንደቅ

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here