በስሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረብያ በኢትዮጵያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በመቃወም ጠንከር ያለ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። እያደረጉም ነው። ሌላው ቀርቶ ጥቃቱ እየደረሰ ባለበት በሳውዲ እንኳን ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው በጎዳናዎች ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ኢትዮጵያውያን ግን በገዛ ሃገራቸው በሳውዲ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘግናኝ ድርጊት መቃወም አልቻሉም። በጀግናው የወያኔ መንግስት ጥቃት ደርሶባቸዋል። ምናልባት አዲስ አበባ ጥቃት የደረሰባቸው በሳውዲ እየተዋከቡ ያሉ ኢትዮጵያውያኖች እህት ፤ ወንድም ፤ ጓደኛ፤ እናት ፤ አባት ሊሆኑም ይችላሉ።
ሰልፉን ማንም ይጥራው ማን ያነገበው ዓላማ ግልጽ ነበር። እንደውም ወያኔ ወያኔ ባይሆን ኖሮ እንደመንግስትነቱ የሳውዲ መንግስት ለሚያደርሰው ህገወጥ ጥቃት መስጠት ላለበት ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ እንደግብዓት ሊጠቀምበት የሚገባ ርምጃም ነበር። ተነሳሽነቱን ወስደው ድምጸቸውን ለማሰማት በወጡ ኢትዮጵያውያን ላይ ጭራሽ ጥቃት ማድረስ የወያኔን ፖለቲካዊ ማንነት እና ግብ ጠንቅቆ ለሚያውቀው ኢትዮጵያዊ ባያስገርምም ፤ ከወያኔ ጋር ተሰልፈው እየሰሩ ላሉ ወገኖች ጥያቄ ማስነሳት አለበት።
ወያኔ አሁንም ደደቢታዊ መንፈሱን ነው እየኖረ ያለው። በሰፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለመሽፈን ቢሞክርም ከኢትዮጵያዊ መንፈስ ጋር ሊታረቅ አልቻለም። ዛሬም ኢትዮጵያዊነት ጋር ሰላም ሊያወርድ አልቻለም። ደደቢታዊ መንፈስ የጽንፈኚነት መንፈስ ነው። ደደቢታዊነትን ቀፋፊ የሚያደርገው በጎሰኛነት ላይ የተመሰረተ እና ሌሎችን ኢትዮጵያውያንን እንደሌላ ማየቱ ብቻ አይደለም። የበለጠ ቀፋፊ እና ምናልባትም አደገኛ የሚያደረገው የአጥፍቶ መጥፋትም መንፈስ የተጠናወተው መሆኑ ነው። በፓርላማ (ከተባለ) እና ከዚያም ውጭ እየናኘ ያለው የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደዜጋ ያገባኛል በሚል መንፈስ የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን በጽንፈኝነት የመፈረጁ ዋነኛ ምክንያት ወያኔ የራሱን የጽንፈኝነት እና የአጥፍቶ ጠፊነት መንፈስ ለመሽፈንም ይመስላል። ነገሩን ከ”ልማት” ጋር ያለ ጠብ ማስመሰሉም ሌላ አላማ የለውም።
ወያኔያዊ ከሆነ መንገድ ዉጭ እንደዜጋ ስለ ኢትዮጵያ ማሰብ እና መምከር ጽንፈኝነት ከሆነ ፤ ዜጎች ጽንፈኛ ከመሆን ውጭ ኢትዮጵያን ከደደቢታዊ ጎሰኛስነት እና አጥፍቶ ጠፊነት መታደግ የሚቻል አይመስለኝም። ለመሆኑ እዚህ “ፌስ ቡክ” ላይ እንኳን ሃሳባቸውን ሰነዘሩ ብሎ በ “ኢን ቦክስ” መልዕክት ከማስፈራራት አልፈው በአካል ጭምር ጉዳት ለማድረስ (ከነቤተሰባቸው) የሚዛትባቸው እንዳሉ አይታወቅም? ሰልፍ ስለተወጣ ብቻ የተፈጠረ አይደለም። ጥያቄው ኢትዮጵያ እስከ መቸ የጥቂት ደደቢታውያን ትሆናለች?
ደደቢታዉያን ከተቻላቸው ኢትዮጵያን ለዘመናት እየሽጡ፤ እየለወጡ እየፈለጡ፤ እየቆረጡ በስልጣን ላይ ለመኖር ካልተሳካላቸው ከውስጥም ከውጭም ኢትዮጵያን በእሾህ አጥረው ኢትዮጵያ በብዙ ደም ራሷን ስታ እንድትጠፋ ነው ሃሳባቸው። ደደቢታውያን ሳትሆኑ ከደደቢታውያኑ ጋር ተሰልፋችሁ የቀለበት መንገድ እያወራችሁ የደደቢታውያኑን የጥፋት ዕቅድ እንዳታስተውሉ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?