Thursday, May 30, 2024
HomeSliderየኢህአዴግ 9ኛ ጉባዔ፡"የልማት ኃይሎች ንቅናቄ"

የኢህአዴግ 9ኛ ጉባዔ፡”የልማት ኃይሎች ንቅናቄ”

ጉባዔው “የመለስ ዜናዊ  አስተሳሰቦቹ እና አስተምህሮዎቹ ይበልጥ የህዝብ ሃብት ሆነው እንዲስፋፉ የማድረግ አቅጣጫ የሚያስይዝ ጉባኤ እንደሚሆን ይጠበቃል” ኃይለማርያም ደሳለኝ 

[Source:www.eprdf.org.et]
March 24,2012 (Borkena) ኢህአዴግ  ለአራት ቀናት ይቆያል የተባለለትን 9ኛውን የድርጂቱን ጉባዔ “በመለስ አስተምህሮት ጠንካራ ድርጂቶች እና  የልማት ኃይሎች ንቅናቂ ለህዳሴያችን” በሚል መሪ  ቃል ትላንት  በባህርዳር ጀመረ። የኢትዮጵያ ቴሌቭዠን እንደዘገበው  9ኛው ጉባዔ 8ኛው ጉባዔ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ምን ያህል ተግባራዊ እንደሆኑ እንደሚገመግም አስታውቋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት ወራቶች በኋላ ውዝግብ በሚመስል ሁኔታ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን የተሰጣቸው ኃይለማርያም ደሳለኝ እስካሁን የተደረጉት የድርጂቱ ጉባዔዎች ሁለት መሰረታዊ ነጥቦችን፡-

  • ድርጂቱ ውስጣዊ ዲሞክራሲያዊ ሁኔታውን የሚፈትሽበት እና ተግባርን ማዕከል አድርጎ በሚካሄድ ፓለቲካዊ እና ሪዮተ-ዓለማዊ  ትግል ድርጂታዊ ጥንካሬ የሚጎለብትበት እንዲሁም በዲሞክራሲያዊ መንገድ አመራሮችን መርጦ የትግሉን ቀጣይነት የሚያረጋግጥበት”
  • ከሕዝቡ የተቀበለውን አገር የመምራት እና የማስተዳደር ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን የሚገመግምበት እና ተገቢውን ትምህርት በመውሰድ ጠንካራ ጎኖቹ ይብልጥ እንዲጎለብቱ እና ደጋማ ጎኖቹ እንዲታረሙ እና ዳግም እንዳይከሰቱ ለትግል የሚዘጋጂበት የተጣመሩ ተልዕኮዎችን መፈጸም

የያዙ እንደነበሩ አስታውሰው 9ኛው ጉባኤ ሲካሄድም “የራሱ የሆኑ ታሪካዊ ገጠመኞችን በመያዝ ነው” በማለት ጠቁመዋል። ታሪካዊ የተባለው የመለስ ዜናዊ በሞት መለየት ሲሆን  ከዚሁ ጋር በተያያዘ 9ኛው ጉባዔ  አንግቦት የተነሳው  ዓላማ
“በመስዋዕቱ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ማዕበል ዳር እንዲደርስ እና በህይወት ዘመኑ ለሃገራችንም ሆነ ለአህጉራችን ከዚያም አልፎ ለዓለም ፍትህ ከድህነት እና ኋላቀርነት ለመላቀቅ የሚታገሉ ህዝቦች ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረከቱ እና  እያበረክቱ ያሉ አስተሳሰቦቹ እና አስተምህሮዎቹ ይበልጥ የህዝብ ሃብት ሆነው እንዲስፋፉ የማድረግ አቅጣጫ የሚያስይዝ ጉባኤ እንደሚሆን ይጠበቃል” ሲሉ ገልጸውታል ።

“በአምስቱ ዓመት የልማት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለሁለት ዓመት ተኩል ዕቅድ አፈጻጸም አመርቂ ውጤት ተገኝቷል” መባሉ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ መታመማቸው ይፋ ከሆነበት ቀን ጀምሮ በሞተ ተለይተው ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን እንዲረከቡ እስከተደረገበት ጊዜ  በብዙ ወራቶች በሚቆጠር እድሜ የፕሮጀት መስተጓጎል ከመኖሩ አንጻር ውጤት ተገኝቷል መባሉ አሳማኝ ባይሆንም፤ “የማስፈጸም አቅም” በጉባዔው ከዋነኛ አጀንዳዎች እንደ አንዱ መነሳቱ “ትራንስፎርሜሽን” ስለተባለው እቅድ መሳካት አጠራጣሪነት የሚሰጠው ፍንጭ አለ። ፕሮጀክት የማስፈጸም አቅም ግምገማ ክፕሮጀክት እቅድ ጋር ሊታይ የሚገባው የፕሮጀክት ቀረጻው አካል እንጂ ፕሮጀክት በማስፈጸፍ ሂደት መሃል ላይ እንደ ኮንትራት ውል ክለሳ ሊነሳ የሚገባ ጉዳይ ሊሆን አይችልም። “የማስፈጸም አቅም በጥልቀት ይፈተሻል” መባሉ ምናልባት ከአስፈጻሚ አካላት መተካካቱ እና ከፋይናንስ አቅም አንጻር ሊታይ የሚችል ነው። የህወሓት መራሹ መንግስት የድህንነት እና የስለላ መዋቅር በአፈናው ልክ የተለጠጠ ስለሆነ ለተነደፉ የልማት ፕሮጀክቶች ሊውሉ የሚችለውን የተወሰነ የፋይናንስ አቅም ሊሻማው እንደሚችል አንድ እና ሁለት የለውም።

ሌላው ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ፓለቲካዊ ግብ ያለው የሚመስል በዋጋ ግሽበት የተመታ ኢኮኖሚ እየመሩ በ”ድንገት” የሞቱ ከመሆናቸውም በላይ ሁለት አስርት ዓመት በዘለቀው በጽንፈኛ የጎሰኝነት ስሜት ላይ የተመስረተ በሚመስል አስተዳደራቸው በወሰደው የመብት ጥሰት እና የኃይል  ርምጃ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸውን እንዳጡ ፣ እስርና እንግልት እንደደረሰባቸው እና ለስደት እንደተዳረጉ እየታወቀ የመለስ ዜናዊ “አስተምህሮቶች…ለዓለም ፍትህ፣ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ አስተዋጾ አበረከቱ” መባሉ ምናልባት በገዢው ፓርቲ  ስር ለተኮለኮሉት ካልሆነ በስተቀር ለሌላው ኢትዮያዊ እንደ ፌዝ ከመታየት ያለፈ ዋጋ እንደማይኖራቸው መገመት አያዳግትም።  ይልቁንም አቶ መለስ ዜናዊ የብሄር ትምክህት የተጠናወታቸው የፓለቲካ ሰው እንደነበሩ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተለያየ ጊዜ ከሰነዘሯቸው ፓለቲካዊ አስተያዮቶች በተጨማሪ በመሩት ስርዓት በተንጸባረቀው( እና አሁን ድረስ ባልተቀየረ) የስልጣን እና የሃብት ክፍፍል በቀላሉ መገመት ይቻላል። አቶ መለስ ለረዢም ጊዜ ከመሩት (እና ‘ከተዋጉለት’) የህወሓት ፓርቲ የተለየ የፖለቲካ እሳቤ እና አመለካከት ያልነበራቸው ሰው እንደመሆናቸው፤ምናልባት 9ኛው ጉባዔ “የመለስን አስተምህሮ ማስፋፋት” በሚል ጠቅላይ ሚኒስተር ዜናዊ ከጊዜ በኋላ በማህበራዊ ማለሳለስ እና በብልጣብልጥነት ሊሸፍኑት የሞከሩትን የህወሓት ራዕይ እና ዓላማ በሌሎች ከህወሃት ጋር በበታችነት በሚሰሩ ድርጂቶች ላይ የመጫኛ ስትራቴጂ ሊሆን የሚችልበትም ሁኒታ ሊኖር ይችላል::

ከዚሁ ጉባዔ ጋር በተያያዘ የኢሃዴግ መንግስት ቻይናን እና ሱዳንን (ሰሜን ሱዳን) ጨምሮ ስላሳ ያህል የውጭ ሃገር መንግስታትን እና ድርጂቶችን በእንግድነት የጋበዘ እንድሆነ ገልጾ የኤርትራ ተቃዋሚዎችም ከውጭ መንግስታት እኩል ግብዣ ተደርጎላቸው በጉባዔው በእንግድነት ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ስለመጋበዛቸው ወይንም ስላለመጋበዛቸው የተጠቆመ ነገር ባይኖርም ከህወሃት መራሹ መንግስት ተሞክሮዎች ተቃዋሚው እንዲህ አይነት ግንዣ እንደማይደረገልት መገመት አያስቸግርም።

 

 

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here