Saturday, April 20, 2024
HomeEthiopian Newsየቆመ የመሰለው ህወሓት...

የቆመ የመሰለው ህወሓት…

የህወሓትን መንግስት ግብር ፈጽሞ በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ጽንሰ ሃሳብ መስፈር እንደማይቻል ህወሓት በተደጋጋሚ ከወሰዳቸው ትርጉም አልባ አፈናዎች፣ ከሚከተላቸው ጥላቻ ፈጣሪ ፓሊሲዎች እና በሚያሳየው ቅጥ ያጣ የጉልበተኛነት ፍላጎቶች በግልጽ መረዳት ይቻላል። ከህወሓት መንግስት ጋር በተያያዘ ስለ መንግስት ተቋማት ፋይዳ ፣ስለዜጎች መብት ፣ በመንግስት እና በቢሮክራሲ መካክለ ሊኖር ስለሚገባው ከፓለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ ግንኙነት( neutrality principle)፣ ስለ ህግ የበላይነት፣ ስለ ህገ መንግስታዊ አስተዳደር ማሰብ አይቻልም። የሚገርመው ነገር የህወሓትን መንግስት በነዚህ ዲሞክራሲያዊ ተቋማዊ የመንግስት መስተዳድር ገጽታዎች መስፈር አለመቻሉ ሳይሆን ፤ አምባገንነት የነገሰባቸው ፈላጭ ቆራጫዊ በሚባሉ መስተዳደሮች እንኳ መስፈር አለመቻሉ ነው። ህወሓት ከማንስም በታች ወረደ።

የመንግስት ስልጣን በያዙ ማግስት ዋና ዋና የሚባሉት የህዋሓት  አመራሮች በአንድ በኩል ከአውሮፓ ዪኒቨርሲቲዎች የተልዕኮ ትምህርት እያሯሯጡ በሌላ በኩል የፖለቲካ ስልጣን አደረጃጀት እና ከህዝብ ሊገጥማቸው የሚችለውን ፈተና እንዴት እንደሚወጡት የሚያስጠኗቸው (political tutor/mentor) የውጭ ወዳጆች እንደነበራቸው የሚጠቁሙ ሁኔታዎች አለ። በተመሳሳይ ሁኔታ ህወሓት እንደ አሰራር የ”ቡድን አመራር” የሚል ልምድ ስለነበረው ክላሽ ያነገተው የህወሓት “ተጋዳላይ” ሁሉ የመንግስትነት ስሜት ይሰማው ነበር። በህወሓት ‘ታጋዮች’ ደረጃ ይንጸባረቅ የነበረው የመንግስትነት ስሜት የርዮተ-ዓለም እይታውን እና የፖለቲካ ትምህርቱን የወሰደው ከህወሓት አመራሮች እንደመሆኑ(በካድሬዎች በኩል ቢሆንም) ፣ ህወሓት የሚሽከረከርበት  የፖለቲካ ምህዋር – “ትግሬነት” እና “ታጋይነት”-  በአንድ በኩል ታግለን አሸነፍነው የሚሉት “ጨቋኝነት እና ነፍጠኝነት” እና የጠላትነት ስሜት በሌላ በኩል ስለነበረ ከታች ያሉት “ታጋዮች” ጭምር ብዙ ቁም ነገር ሊሰጠው የማይችልን ጉዳይ በጥይት የሚዳኙበት ሁኔታም ነበር።  የህወሓት አመራሮች ትምህርታቸውን እና የተሰጣቸን የፖለቲካ ገለጻ ጨርሰውም ሀገር በስርዐት እና በተቋማት ሳይሆን በህገ-ህወሓት ልቦና መገዛት ቀጠሉበት።

ለብዙ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ የሆነ ፣ከታሪካችን ጋር ትስስር ያለው እና ብዙ ኢትዮጵያዊ የተሰዋለት ሃሳብ በነፍጠኛነት ስለተፈረጀ  ያንን ያነገበ እንግልት እና ዘለፋ እንዲደርስበት ተደረገ። ከታች የነበሩ ‘ታጋዮች’ ጭምር በዚህ መንፈስ ነበር ሰው እንዳዋዛ በጥይት የሚገድሉት፤የሚያንገላቱት። ፕሮፌሰር አስራትን ወደ እስር የወረወራቸው የህወሓት መንግስት ነው። እታች በእስር ቤት ደረጃ ደሞ ኢትዮጵያዊነትን በጥፊ የመታ መስሎት ፕሮፌሰር አስራትን በዛ እድሜያቸው ተንጠራርቶ በጥፊ የመታውም የህወሓት ታጋይ በራሱ ቤት እሱም መንግስት ነበር።  እንደገና ከብዙ ዓመት በኋላ ብርቱካን ሚዴቅሳ ስትታሰር ፕሮፌስር መስፍን (ወደ ሰማኒያ ይጠጋ ነበር እድሚያቸው ያኔ) በሰደፍ የተመቱበት ሁኔታ አሁንም  ዓላማው ሽማግሌን መታገል ሳይሆን ፕሮፌሰር መስፍን በጊዜው ለህወሓቱ ታጋይ ያሳዮትን ኢትዮጵያዊነት መምታታቸው ነበር -በነሱ ቤት።

ትላንትናም እንዲሁ ለግራዚያኒ የሚታነጸውን መታሰቢያ ለመቃወም የወጡ ኢትዮጵያውያኖች በህወሓት መንግስት ከታሰሩ በኋላ ፕሮፌሰር መስፍን የታሰሩትን አድራሻ  ለማጣራት አንድ ፖሊስ ጣቢያ ሲጠይቁ የተሰጣቸው መልስ “ምናባክ አውቅልሃለሁ፣ ግባና ጠይቅ” (ሰማኒያ ስድስት ዓመታቸው እንደሆነ እንዳይረሳ) ዓላማው ፕሮፌሰርን ማሳነስ ሳይሆን ፕሮፌሰሩ ሳያስነኩ ሳይሸጡ ሳይለውጡ ይዘውት የኖሩትን ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ለማሳነስ ነበር። በእነ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምም ላይ ተመሳሳይ ሊባል የሚችል አይነት ወከባ እንደደረሰ ከፍኖተ ነጻነት ዘገባ ግምት መውሰድ ይቻላል።

ከሃያ ዓመት በፊት የነበረው የህወሓት አስተሳሰብ ይሄው ነው። ከሃያ አመት በኋላም እየተንጸባረቀ ያለው አስተሳሰብ ይሄው ነው። የህወሓትን “በትግሬነት” ዙሪያ የሚያጠነጥን የሚመስል ነገር ግን በባህሪው “ጸረ-ትግሬነት”ም የሆነ ፓለቲካ በማህበራዊ ማለሳለስ እና ማድበስበስ የበላይነት ግንባታ ቢቀጥልም ከመጠነሰፊው የፕሮፓጋንዳ ሽፋን አቅም በላይ ሆነው እንዲህ እያፈተለኩ ወደ አደባባይ የሚወጡ ህወሓት ለኢትዮጵያውያን እና  ኢትዮጵያዊነትን ከውስጥም ከውጭም ለብሰው ለሚኖሩ ያለውን ንቀት እና ጥላቻ የሚያሳዮ ነገሮች ይስተዋላሉ።  የመብት ጥሰቱም ሊቆም ያልቻለው ህወሃት ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት ባለመቻሉ ነው።ይሄንን በግልጽ ለመረዳት የነማን መብት ተደጋጋሚ የመብት ጥሰት ደረሰበት የሚለውን መጠየቅ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።

መንግስታዊ ተቋም፣መንግስታዊ አስተዳደር ፣ህግ እና የህግ የበላይነት የሚባል ነገር አሁንም ጭላንጭሉ የለም። ከአምባገነንም የተቃዋሚ ሃሳብ ባያከሩ እንኳ ራሳቸውን የሚያከብሩ አይጠፉም። በሽምግልና እድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን ጭምር በተቋም ድረጃ እያሰሩ ማንገላታት ካስሩ በኋላ “ይቅርታ ጠይቁኝ” የሚል አምባገነን ስርዐት እና መንግስት አሁንም በወንበዴነት እና አልባሌነት ከመታየት ያለፈ አንድምታ አይፈጥርም።

ባለፈው ዓመት ይመስለኛል ትግራይ ላይ በትግራይ ያለውን የህወሓት አስተዳደር የሚቃወም ሰልፍ እንደተደረገ በዜና ማሰራጫዎች ሰምተናል። አሁንም ገፍቶ ሰልፍ አድርጋለሁ ብሉ የሚመጣ ካለ ትግራይ ላይ ያለው የህወሃት አመራር ያስራል የሚል ግምት የለኝም፡፡ አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ ሲከለከል እና ሰልፈኛ ሲታሰር – ያውም ለግፈኛ የጣሊያን ጀኔራል የሚሰጥ ክብርን በመቃወም የተደረገን ሰልፍ- ነገሩን ሙሉ ለሙሉ ከአምባገነነት ባህሪ የመነጨ ርምጃ ለማለት ያስቸግራል። የትግራይ ህዝብ “በተሰው” 60,000 ልጆቹ ስም የሚከበረውን ያህል ሌላውም ኢትዮጵያዊ  በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተሰው ጀግኖቹን እንዳሉት አምኖ ማክበር ባይቻል እንኳን የሚያከብሩትን ማጣጣል እና ለማሳነስ መሞከር ለማሳነስ እየሞከረ ያለውን እካል የሃልዮም የገቢርም ትንሽነት የሚጠቁም ርምጃ ሊሆን ይችላል።

እንነጋገር ከተባለ እነዛ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖች በክብር በፍቅር የተሰውት ለጎጥ አይደለም። ለአማራነት አይደለም። ለኦሮሞነት አይደለም። ከጉራጌኔት አይደለም። የተሰውት ለኢትዮጵያዊነት ነው። ህወሓትም ሃያ አንድ ዓመት ሙሉ ሲቀጠቅጠው ኖሮ ኢትዮጵያዊነት ንቅንቅ ያላለበት ምክንያት ይሄው ነው። በመጨረሻ ህወሓት የመስዋዕትነት መታሰቢያ የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶችን በልማት ስም አፈርሳለሁ የሚልበትም ምክንያት ለጸረ-ኢትዮጵያዊነቱ ተጨማሪ ማሳያ ከመሆን ያለፈ ሊሆን አይችልም።

የቆመ የመሰለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ እንዲሁ ህወሓት “ጉልበቴ እንዳለ ነው እልተነካም” የሚል አንድምታ ለመፍጠር እየወሰደ ላለው ወደ እብደት እየተቀየረ ላለ ጎጠኛ ርምጃ ለከት ቢያበጂለት ጥሩ ነው። “ባለ-ራዕዮ” የህወሓትም መሪ እንዲህ አለሁ አለሁ ሲሉ ነው በድንገት የሌሉት። እየሌሉም ህወሓት ምን ያህል ጊዜ አሉ እያለ ያሰበው? መንግስታዊ ስርዐት ሳይፈጥሩ፣  የሚሰሩ እና ተዓማኒነት ያላቸው የመንግስት ተቋማት ሳይፈጥሩ የወንበዴ አይነት ባይሪ እያሳዮ በፖሊስ እና በፖሊስ ጣቢያ ብርታት እየዘረፉኩ እና እየረገጥኩ እቀጥላለሁ የሚል ቡድን የተደላደለ መንግስት አለኝ ብሎ የሚያስብ ከሆነ “የባለ ራዕዮ” መሪ ታሪክ ሊደገም ይችላል። ህወሓትም የህወሓትም ደጋፊዎች ማስታወስ ያለባቸው ጉዳይ ይሄንን ነው።

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here