ይሄኛው ጽሁፍ ትላንትና ‘ፌስ ቡክ’ ላይ ላጋራሁት ሃሳብ ትችት ለሰነዘረ የ ‘ፌስ ቡክ ጓደኛ” የሰጠሁት መልስ ነው።
ግልጽ ለማድረግ ያህል በእስራኤል ሃገር የ”ቁንጂና ውድድር” አሽናፊ የሆነችውን ትውልደ ኢትዮጷዊ ወጣት የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ከባራክ ኦባማ ጋር ራት ስለጋበዛት አንድ የእንግዚዝ ጋዜጣ የሰራውን ዜና ብዙ ኢትዮጵያዊ በመደነቅ ሲቀባበሉት ሳይ ግነቱን እና አንድምታውን ግምት ውስጥ በማስገባት ፌስ ቡክ ላይ ለሰነዘርኩት ሃሳብ የተሰጠውን ትችት መልስ ለመስጠት ያህል ነው። አስተያየቱ እንዲህ ይላል ፡-
“ድሜጥሮስ ደሞ ታበዛዋለህ እንኳን እሷ ልደቱ አያሌው እድሉን ቢያገኝ ጥሩንባውን አንችለውም:: ምነው አንተ critical thinker ብለህ ያልካቸው እንኳን እንደ ግብዳ ስኬት እንደዚህ አይነት ፎቶ ሲለጥፉ አልነበር By the way ain’t it a big deal for a 21 years old girl won a pageant and invited to have a dinner with the head of states of US?”
የኔ መልስ ፡-
ወደ ቁንጂና ውድድር አሽናፊዋ ጉዳይ ስለመለስ- ልጂቱ ከእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ሽሞን ፔሬዝ ቤት (ወይንም ቢሮ እርግጠኛ እይደለሁም) ተደውሎላት በሰውየው መኖሪያ ቤት ከኦባማ ጋር እራት እንድትበላ ስትጋበዝ እሽ በማለቷ ወይንም ጉዳዩን በማስመልከት ምናልባት ላናገሯት የእግሊዝ የሜዲያ አሰተያየት መስጠቷ ምንም ችግር የለውም።(በነገራችን ላይ ፕሬዝዳንት ባይሆን ኖሮ የማያቃት ሰው ደውሎ እቤቴ ራት ብይ ቢላት ትሄድ ነበር? እንደዛ ካደረገችማ ኢትዮጵያዊ እይደለችማ። ጎንደሬነቷስ የታለ ማስባሉ አይቀርም። ሃሃ)። ችግሩ በሃገር ውስጥ እና በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ (ያውም ተማረ የሚባለው)ዜናውን እንደትንግርት አይቶ እንደ ዱላ ቅብብል እየተቀባበለ ላይክ ሲያደርገው ማየት ስለ ፖለቲካ ብስለታችን እና ስለ ነጻነት ስላለን ግንዛቤ እንድጠይቅ ያስገድዳል። ነጻነት የእሳቤ ብቻ ሳይሆን የእኗኗር ዘየም ውጤት ነው። ነጻ ለመሆን የሚፈልግ ትውልድ እና ሕዝብ ዓለምን እና ህይወትን ሳናውቀው እንደዋዛ ነጻነታችንን እንድናጣ ቀላል የማይባል አስተዋጾ ባበረከቱ አደንዛዥ ማህበራዊ ልማዶች እና አስተሳሰቦች ብሎም እያዋዙ እያስመሰሉ ሲያስፈልግ ደሞ በጉልበት በሚገዙን ሰዎች የዓለም እይታ ዓለምን የሚያይ ከሆነ ነጻ የሆን እድሉ የመነመነ ነው። የነጻነት ጥንስሱ የለማ። ነጻነት ከንቃት ህሊና ለንቃተ ኅሊናው ጋር መሳ ለመሳ ከሚሄድ የአኗኗር ዘየ የሚወለድ ጉዳይ ነው።
ሲጀመር የ”ቁንጂና ውድድር” የሚባለውን ሃሳብ ከቁምነገር የማልጽፈው ጉዳይ ነው። የ”ቁንጂና ወድድር” ውጤት ደሞ እንዲህ የፓለቲካ ሰዎችን ግምት(በድንገት ሳይታሰብ የሆነ ነገር እይመስለኝም) አግኝቶ የዜና ሽፋን እንዲሰጠው ሆኖ ሲቀርብ መታየት ያለበት እንዲህ ባለ ፕሮፕጋንዳ ማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ምንድን ነው? በመጀመሪያ ይሄ ታሪክ ስለ ‘ኤሊቲዝም’ ነው ስለ ‘ህዝባዊነት’ የሚተርከው? ኮንፎርሚስቶች ( መስሎ አዳሪዎች) ዲዛይንድ’ በሆነ “ሶሻል ሞቢሊቲ” – ለ’ልሂቃኑ’ ቅርበት እንዲኖራቸው ሲደረግ የሚዳነቀውን ያህል ስርዐቱን ያልተቀበሉት (“ዲሴንት የሚያደርጉት”) በየቦታው በተቸከሉ ማህበራዊ ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችካሎች ጋር እንዳይንቀሳቀሱ ተደረገው የታሰሩ ሚሊየኖችም አይታወሱም። አይዘከሩም። ስደተኞች ላይ ያለው ትርፍ ከጉልበት ዋጋ (“ከሌበር ቫሊዮ”) ጋር የተሳሰረ ብቻ አይደለም። “አይዲዮሎጂካል” ቫሊዮም እንዲኖራቸው ይፈለጋል። ምናልባት የምዕራቡን ዓለም አስራር አይተኽው ይሆናል።
ዜና ፣ ዶክመንታሪ፣ቃለ መጠየቅ ወይንም ሌላ ታሪክ ሲስራ በውስጡ የርዮተ-ዓለም ትርፍ እንዲኖረው ተደርጎ በብልጠት ስለሚሰራ ለማያቅ ሰው እውነቱን ከውሸት ፣ ግነቱን ከሚዛናዊ ዜና ለመለየት ያስቸግር ይሆናል። እንዲህ እንድልጂቱ ባለው ታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ስዎችን (ያውም የዓለም መሪዎች የሚባሉትን) ትኩረት አግኝቶ ሲሰራ – ልጂቱ ብታውቀውም ባታውቀውም ማውራት የተፈለገው ስለ “ስኬት” እና “ዕድል” ብቻ አይደለም። ታሪኩ የ”ኮንፎርሚቲ ‘(መስሎ እንዳረጉት ሆⶈ የማደር) ታሪክ ነው ወይንስ የጥረት እና የትግል? “ኮኦፐሬቲቭ” የመሆን ታሪክ ነው? ፌስ ቡክ ላይ እንዳልኩት ከእስራል በኢትዮጵያውያን አይሁዶች ላይ ስለሚደረሰው የሚንሰማው ነገር የተለየ ነው፡፡ ጭራሽ በቅርቡ ኢትዮጵያውያኖቹ እንዳይዋለዱ ያለ ዕውቀታቸው የማምከኛ ክትባት ይከተቡ እንደነበር ሰምተናል። የእስራኤልም ባለስልጣናት ጉዳዮን አምነው በይፋ ይቅርታ ጠየቁበት የተባለ ጉዳይ ነው። ልጂቱ ተሳካላት የሚባለው እንግዲህ እንዲህ ባለ ማህበረሰብ ውስጥ ነው። ከዚህ የ”ስኬት” ዜና ጀርባ እና ከተሰጠው የዜና ሽፋን ከዚህ በፊት ከነበረው ተሞክሮ በመነሳት መውሰድ ያለብን ግምት አለ።
ለልጂቱ በልጂነት አቅሟ ደረሰብኝ ያለችውን ነገር አስባ፤ የተደረገላት ጥሪ እንዲፈጥር የታሰበውን አንድምታ ገብቷት ያንን ግምት ውስጥ አስገብታ ግብዣውን ባትቀበል እና አለመቀበሏ ዜና ቢሆን ኖሮ ታሪኩ ከ ‘ኢሊቲዝም’ የበለጠ የህዝባዊነት ታሪክ ይሆን ነበር። የተለመደ እና የሚጠበቅ (ኦርዲናሪ) ከመሆን ይልቅ ያልተለመደ እና አስተማሪ ሊሆን ይችል ነበር። እንዳልኩት በልጂቱ ለመፍረድ እይደለም። ንቃተ ህሊና ከዕድሜ ጋር ብቻ የሚመጣ ሳይሆን ማህበረሰባዊም መሰረት አለው። (ለነገሩ ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም ከልጂቱ ብዙ በማይርቅ ዕድሜ ክልል ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነጻነት እያነሱ የሚጥሉ እና ክህዝባዊ ሃሳብ ጋር የሚኖሩ እንዳሉ ፍንጮች የሚታዮ ይመስለኛል። እንዳናደናግራቸው እንጂ)። ማህበራዊ ንቃት ህሊና ቢርኖ፣ጠንካራ የነጻነት ስሜት እና ነጻነት ለማግኘት ትጋት ቢኖር ልጂቱ ያለችበት ዕድሜ ብርቱ የለውጥ ፈላጊነት እና የአርበኝነት ስሜት የሚስተዋልበት ዕድሜ ነው። ነገሮችን ለማገናዘብ የሚያንስ ዐድሜ አይደለም። በታሪክ የምናውቃቸው የታላላቅ አብዮቶች ሞተር የሆኑት በዚህ የዕድሜ ክልል ያሉ ዜጎች ናቸው። የሆነ ሆኖ እንዳልኩት ልጂቱን ነጥሎ ለመተቸት ወይንም አገኘሁ የምትለውን ‘ስኬት’ ለማሳነስ ወይ ለማጣጣል ሳይሆን የኔ ጉዳይ በማህበረሰብ ድረጃ ዜናውን እየተቀባበልን የተረዳንበትን መንገድ ለመተቸት ነው። ነጻነት ፈላጊዎችም የነጻነት ትርጉም እና ፋይዳ የገባቸውም ሰውችም አያስመስለንም። የምንጋራቸው እና የምናጋራቸው ሃሳቦች ለንቃተ ህሊና መዳበር እና ለነጻነት ለሚደረገውን ትግል ያላቸውንም ሚና ግምት ውስጥ ማስገባ የሚያስፈልግ ስለሚመስለኝ ነው።
በመጨረሻ እኔ የማደንቃቸው “critical thinker” እነማን ናቸው? እሱን እብራራ እና እመለስበት ይሆናል እንደሁኔታው።