Saturday, June 22, 2024
HomeEthiopian Newsትግራይ እና ሕወሓት ምንና ምን ናቸው?

ትግራይ እና ሕወሓት ምንና ምን ናቸው?

 በበፍቃዱ ኃይሉ

“An event has happened, upon which it is difficult to speak, and impossible to be silent.’ ~ Edmund Burke.

ሴቶች!

ሴቶች ፀጉራቸውን ያሳድጋሉ፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር በስህተት የተደነቀረ አይደለም፤ በምሳሌነት የቀረበ ነው፡፡ 1ኛ. ፀጉራቸውን የማያሳድጉ ሴቶች አሉ፤ 2ኛ. ፀጉራቸውን የሚያሳድጉ ወንዶችም አሉ፡፡ ቢሆንም ግን ዓረፍተ ነገሩ ውሸት/ስህተት ነው ሊባል አይችልም፤ ምክንያቱም የተለዩት (exceptionals) አጠቃላዩን አይገልፁም፡፡ በዚህ ርዕስ ስር የምናወራው ፍፁም እውነት ስለሆነ ነገር አይደለም፤ በአብዛኛው እውነት ስለሆነ ነገር ነው፡፡

ሕወሓት!

የትግራይ ተወላጆች ሕወሓት ይደግፋሉ፡፡ የዚህ ዓረፍተ ነገር እውነትነት ልክ ‹‹ሴቶች ፀጉራቸውን ያሳድጋሉ፡፡›› እንደሚለው ዓረፍተ ነገር ነው፡፡

በቁጥር ውዥንብር (illusion) ውስጥ ካልገባን በቀር (ኢሕአዴግ የደጋፊዎቼ ቁጥር እያለ የሚናገረው የ‹‹እውነተኛ›› ደጋፊዎቹ ቁጥር ነው ብለን ነባራዊውን እውነታ ማገናዘብ ካልተሳነን በቀር) የሕወሓት/ኢሕአዴግ ደጋፊዎች ቁጥር ከትግራይ ተወላጆች ቁጥር ጋር እኩል ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ ትክክልም/ስህተትም አይደለም/ነውም፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብም ሆነ ማንኛውም ሰው የፈለገውን በሙሉ ወይም በጎዶሎ ድምፅ መደገፍ ይችላል፡፡ ስህተቱ ግን ምክንያቱ ላይ ነው – ወደእዚህ እንመለስበታለን፡፡

ሌላ እውነት፤ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ደጋፊዎች ቁጥር ከትግራይ ተወላጆች ቁጥርጋ እኩል ከሆነ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሓትን ወይ ይቃወማል አሊያም አይደግፍም ማለት ነው፡፡ ይኼም ትክክልም ስህተትም አይደለም/ነውም፡፡

በመጀመሪያ የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ለምን ሕወሓትን አይደግፉም ወይም ይቃወማሉ? (ለምን ‹ሕወሓት› አልኩኝ? በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የምናወራው ወረቀት ላይ የሰፈረውን ማደናገሪያ ሳይሆን በተግባር ላይ ያለውን እውነታ ነው፤ ስለዚህ የመንግሥት ስልጣን ያለው በኢሕአዴግ እጅ ሳይሆን በሕወሓት እጅ መሆኑን ማስታወስ ይበልጥ ያግባባናል፡፡) ለጥያቄው መልስ ስንሰጥ፡-

1ኛ. ሕወሓት በትጥቅ ትግል ከመጣ በኋላ በምርጫ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣኑን የመልቀቅ አዝማሚያ አላሳየም፣

2ኛ. አብዛኛው እና ወሳኙ የመንግሥት ሥራ ኃላፊነት ቦታ በሕወሓት ሰዎች ተይዟል፤

እነዚህ ሁለት ነጥቦች ሌላውን/ቀሪውን ሰው በማስከፋቱ በይፋ በማይወጣ ቃል (ሕወሓትን እና የትግራይ ተወላጆችን እንደ አንድ በማየት) ብዙኃኑ የውስጥ ለውስጥ ቅሬታውን የትግራይ ተወላጆች በሌሉበት እርስ በእርሱ እንዲቀባበል አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ የትግራይ ተወላጆችን በጥርጣሬ፣ በፍርሐትና አልፎ አልፎም በጥላቻ የመመልከቱ እና የማግለሉ አባዜ ደግሞ የትግራይ ተወላጆችን ወደሕወሓት ይበልጥ አየገፋ እና ታማኝ እንዲሆኑለት እያደረጋቸው መጣ፡፡ ብዙዎቹ ለሕወሓት በታመኑ ቁጥር ደግሞ በሌላው ወገን ያሉት ብዙዎቹ በትግራይ ተወላጆች ላይ ሁሉ (ያለልዩነት) ጥርጣሬ እና አልፎ፣ አልፎም ጥላቻ ጭምር እያዳበሩ መጡ፡፡ በዚህ መሐል ሁለት ዓይነት ማኅበረሰብ ተፈጠረ፡-

1ኛ. የትግራይ ተወላጆችን ሁሉ በጥርጣሬ የሚመለከት፣

2ኛ. ሕወሓትን የሚደግፍ/የተደገፈ የትግራይ ተወላጅ፣

ቀሪው – አሁንም ፀጉራቸውን እንደማያሳድጉት ሴቶች ወይም እንደሚያሳድጉት ወንዶች ቁጥሩ እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡

አረና!

አረና ከሕወሓት ተገንጥለው የወጡ የትግራይ ተወላጆች ፓርቲ ነው፡፡ የአረና ተቀባይነትን ከሁለት ወገን ማየት ይቻላል፡፡ 1ኛ. ከትግራይ ተወላጆች ወገን እና 2ኛ. የትግራይ ተወላጅ ካልሆኑ ቀሪ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወገን፡፡

አረና ከሁለቱም ወገን ልባዊ፣ ሰፊ ተቀባይነትን ማግኘት አልቻለም ብዬ አምናለሁ፡፡ ከትግራይ ተወላጆች ወገን በሕወሓት ቅሬታም ቢኖራቸው ‹ከሌላውጋ ባለመስማማትም ቢሆን ጥቅማችንን የሚያስጠብቀው ሕወሓት ነው› የሚል እምነት አላቸው፡፡ አረና ያንን አያደርግም የሚለውን ተፅዕኖ ደግሞ የፈጠረባቸው በመድረክ ጥላ ከተሰባሰቡ ሌሎች ተቃዋሚዎችጋ መተባበሩ ነው፡፡ ይህ ከእርሱ በቀር ለትግራይ አሳቢ እንደሌለ በውጤታማ መንገድ መስበክ በተቻለው የሕወሓት አስተምህሮ መሠረት ሀጢያት ነው፡፡ ስለዚህ የትግራይ ተወላጆች አረናን የሕወሓትን ያክል ለመቀበል ሲቸግራቸው ይታያል፡

በሌላ በኩል ደግሞ አረናን ቀሪዎቹም በጥርጣሬ እንዲመለከቱት ሆኗል፤ ይህንን ያደረገው ደግሞ ቀድሞ የጠቀስኩት የትግራይ ተወላጆችን ሁሉ ሕወሓትን አይቃወሙም/ይደግፋሉ የሚል ጥርጣሬ/እምነት አባዜ ነው፡፡ (ምናልባት አባባሌ ግልጽ የመሆን አቅም ካጠረው – አረና በትግራ ተወላጆች (ያውም ከሕወሓት የወጡ ሰዎች ስብስብ በመሆኑ) የምር ሕወሓትን ይቃወማል፣ የምር አማራጭ ሐሳብ ያመጣል የሚል እምነት በብዙዎች ውስጥ አጣለሁ፡፡ እንዲያውም፣ ሕወሓት በቀሪው ሕዝብ ውስጥ ያጣውን ተቀባይነት ለማግኘት የፈጠረው የሴራ ቡድን ነው የሚል ፍሬ አልባ ክርክር አድምጬ አውቃለሁ፡፡)

እነዚህን ነጥቦች የዚህኛውን ወይም የዚያኛውን ቡድን (አለመሆን ከታሪካችን አንፃር እንደሚከብደን ቢታወቅም፣) አይደለንም ብለን እናስብ እና መፍትሔ እንፈልግላቸው፡፡ እኔ የአረናን ዝርዝር ማኔፌስቶ ማወቅም መዘርዘርም ሳያስፈልገኝ በፖለቲካ ጦስ ትግሬ እና ትግሬ ያልሆነ በሚል በጥርጣሬ መስመር የተከፈለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአረና መንገድ መልሶ ማስታረቅ ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም መሠረታዊው ‹እኔ የእኛ ስብስብ አባል መሆኑን› (“I” is a subset of “We”) አምኖ መጀመር አለበት በሚል መርሕ አረና የሚወክለው የትግራይን ሕዝብ ቢሆንም ትግራይን የሚወክለው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን አምኖ መቀበል አለበት ነው፤ (ተቀብሏል የሚልም እምነት አለኝ) – አባባሌ ከሕወሓት የመከፋፈል አገዛዝ በተቃራኒ የአረና አካሄድ አብሮ መኖር ላይ የተመሠረተ ነው… ነው፡፡ ለዚህ እንደምስክር የምጠራው አረና በመድረክ ስም (መድረክ ጠንካራም ይሁን ደካማ) የተሰባሰቡ ፓርቲዎች አባል ለመሆን መድፈሩን ነው፡፡ መድረክ ውስጥ ሕብረብሔራውያን እና ብሔር ተኮር የሆኑ ፓርቲዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ፓርቲዎች በአንድ ያሰባሰባቸው የማኒፌስቷቸው አንድነት አይደለም፤ ተቃዋሚነታቸው ብቻም አይደለም፡፡ የራሳቸውን ሕልውና (መኖር) ከሌሎቹ ሕልውና ለይተው ማየት ባለመቻላቸው ነው፡፡ ሕወሓት ከመድረክጋ ኅብረት ሊፈጥር ቀርቶ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመደራደር እንኳን እንደማይፈቅድ እናውቃለን፤ ምክንያቱን ብንጠይቅ የመድረክን ሕልውና እና የሕልውናውን አስፈላጊነት አምኖ መቀበል ስለማይፈልግ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ አረና በመድረክ አባልነቱ ብቻ በአንድ መዳፍ ላይ እንዳሉ ጣቶች የትግራይ እና ቀሪ ኢትዮጵያን አብሮነትን እንደሚቀበል እንቸገራለን ቢባል እንኳን የጽሑፉ ቁምነገር ስላልሆነ በፓርቲው (የአረና መንገድ በማለት) የመሰልነውን ‹‹ሌላውን በማጥፋት መኖር ሳይሆን ሌላውን በማኖር አብሮ መኖር›› የተባለ መርሕ መዝዘን ውይይታችንን እንቀጥል፡፡

ሕወሓት ‹‹እውነትም መንገድም›› እራሱ እና እራሱ ብቻ እንደሆነ ያምናል፡፡ ከእርሱ (እና የራሱ ርዕዮተ ዓለም) ውጪ ትግራይም/ኢትዮጵያም እንደማይኖሩ ያምናል፡፡ ይህ እምነት በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች አዕምሮ ሰርፁዋል ለማለት እደፍራለሁ፡፡ የብዙዎቹ የትግራይ ተወላጆች ሕወሓት ደጋፊነት እና የሙጢኝ ባይነትም የሚፈጠረው ከዚሁ የተሳሳተ ግንዛቤ እና ድምዳሜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሕወሓት እና የትግራይ ተወላጆች (ሴት ወንድ፣ ወጣት አዋቂ፣ ምሁር መሐይም ሳይል) አንድነት ትግራይን ከቀሪው ሕዝብጋ በቀጭን የጥርጣሬ መስመር ለኹለት እየከፈላቸው ነው፡፡ ለነዚህ አንድ ነገር ግን በጥርጣሬ ድንበር ለኹለት የተከፈሉ ሕዝቦች መልሶ አንድ መሆን የሁላችንም ሚና ወሳኝ ነው፡፡ በሁለቱም ምናባዊ መስመሮች ክፍያ ውስጥ ያሉ ዜጎች የኹለቱም ሕልውና (የአንዱ በሌላው ላይ የተመረኮዘ) መሆኑን ለማስታወስ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ስሜትን አቁሞ እውነቱን መጋፈጥ ያስፈልጋል፡፡

ምንም እንኳን ዘመናዊ ፖለቲካ በጂኦግራፊያዊ ካርታ ቢከፍላቸውም ሕዝቦቹ ግን እነዚህን የፖለቲካ መስመሮች አቋርጠው አብረው ሲኖሩ፣ የነበሩበትን ታሪክ ለማስቀጠል አንዱ የሌላውን ሕልውና ማክበር አለባቸው፡፡ የመብት ክብር፣ የሥልጣንም ሆነ የሀብት ክፍፍል ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ችሎታ እና አግባብ ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የኹለት ብሔሮች (ትግሬ እና ሌሎች /ያውም ክህሎት እና ዕውቀትን መሠረት ባላደረገ የአንዱ መሪነት እና የሌላኛው ተመሪነት/) ሳይሆን የሁሉም እኩል አገር የምትሆንበት ሥርዓት መዘርጋት ወይም በጊዜ ሒደት የሚዘረጋበት መንገድ መመቻቸት አለበት፡፡ ይህንን ልዩነት እየተንከባከብን ወደማይፈለግ አቅጣጫ ገፍተን አገሪቱን ገደል ከመስደዳችን በፊት በግልጽ እናውራበት፣ የትግራይም ይሁን ሌሎች ምሁራን በጉዳዩ ላይ አንደበታቸውን ይፍቱ፣ተቃዋሚ ፓርቲዎች ችግሩን እንደሌለ በዝምታ ከሚያልፉት እንዴት እንደሚቀርፉት ይንገሩን፡፡ ይኼው ነው የጽሑፉ ዓላማ!

የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል

 

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here