Tuesday, December 5, 2023
HomeEthiopian Newsየአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት ገጭቶ በመግደል ተጠርጥረው ተያዙ

የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት ገጭቶ በመግደል ተጠርጥረው ተያዙ

Photo: Ethiopianreporter
Photo: Ethiopianreporter

የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው ባለፈው ሰኞ ምሽት በተሽከርካሪ ገጭቶ መግደልና ማምለጥ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

አቶ ፀሐይ በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቧሬ አካባቢ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ በተሽከርካሪ ተገጭቶ በመገደሉ ምክንያት፣ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ገጭቶ አምልጧል ያሉትን ተሽከርካሪ በላዳ ተከታትለው በማስያዛቸው መሆኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር ውለው ማክሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ፀሐይ ለምርመራ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው፣ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ ፀሐይ ሰኞ ምሽት ሦስት ሰዓት አካባቢ ከጅምናዚየም ወጥተው ወደቤታቸው በማምራት ላይ ሳሉ በድንገት ቪ8 የተሰኘው ተሽከርካሪያቸው በላዳ ታክሲ መንገዱ ተዘግቶበት መያዙን የገለጹት ምንጮች፣ በእሳቸው ተሽከርካሪ ላይ የግጭት ምልክት አለመታየቱን አስረድተዋል፡፡

ለጊዜው ማንነቱ በውል ያልታወቀ ግለሰብ በተሽከርካሪ ተገጭቶ መገደሉ ቢረጋገጥም፣ በአካባቢው የነበሩ ግለሰቦች ግለሰቡን የገጨው ተሽከርካሪ አቶ ፀሐይ ከያዙት ተሽከርካሪ ጋር ተመሳሳይ ነው ቢሉም፣ ፖሊስ በጥርጣሬ እሳቸውን በመመርመር ላይ ቢሆንም፣ አቶ ፀሐይ ግጭቱን አለመፈጸማቸውን መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

ምንጮች እንደሚሉት፣ በግጭቱ ወቅት በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በተመሳሳይ ተሽከርካሪ ግለሰብ ተገጭቷል በማለታቸው ምክንያት ፖሊስ ምርመራውን እያካሄደ ነው ይላሉ፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ እንዲሰጥ ፖሊስ ጥያቄ ቢቀርብለትም ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በግጭቱ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈው ግለሰብ ማንነት ለጊዜው አልታወቀም፡፡ በአደጋው ወቅት ሕይወቱ ያለፈው ወንድ ነው የሚሉ ሲኖሩ፣ በሌላ በኩል ሴት መሆኗን የሚገልጹ አሉ፡፡ ፖሊስ ይኼንንም ለማረጋገጥ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ግለሰቡ ከተገጨ በኋላ በላዳ ታክሲ የተከታተሉት ሰዎች አቋራጭ መንገድ ተጠቅመው የአቶ ፀሐይን ተሽከርካሪ ቢያሲዙም፣ በእርግጠኝነት የእሳቸው ስለመሆኑና አለመሆኑ መናገር አለመቻላቸው ተሰምቷል፡፡

ይህንን ድንገተኛ ሁኔታ በማጣራት የገዳይን ማንነት ለማወቅ ሲባል አቶ ፀሐይ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ታስረው በመመርመር ላይ ናቸው፡፡ ፖሊስ ምርመራውን ከጨረሰ በኋላ ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሰጥ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here