Friday, June 14, 2024
HomeEthiopian Newsየመናገር ነጻነት ዘመቻው ለህወሃት መራሹ መንግስት ምኑ ነው?

የመናገር ነጻነት ዘመቻው ለህወሃት መራሹ መንግስት ምኑ ነው?

ሰሞኑን የዞን 9 አባላት የብሎጋቸውን በኢትዮጵያ መከልከል ተከትሎ ከክፈቱልን ያለፈ ፤ መሰረታዊ ሊባል የሚችል ዘመቻ በማህበራዊ ድህረ ገጾች ጀምረዋል፡፡ በዚህ ደረጃ ምላሽ መስጠቱ እና መጠቀም የሚቻለውን መድረክ ተጠቅሞ የችግሩን ጥልቀት ለማመላከት መሞከር ጥሩ ነው። ነገር ግን የመጻፍ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እየተጠየቁ ያሉትን ቡድኖች(‘ፎርማሊ’ ካወራን መንግስት ናቸው -ያውም ፈላጭ ቆራጪ) ባህሪ  ግምት ውስጥ በማስገባት፤ ዘመቻው እነዚሁ ቡድኖች አምነትውበት በማናለብኝነት የወሰዱትን ርምጃ ከማስቀየር ይልቅ በስነ ልቦናቸው ለተቀረጸው የትምክህት እና የበላይነት አስተሳሰብ ሃሴት የሚሰጥ ሆኖ ስለተሰማኝ ለነሱ ትምክህት ሃሴት ላለማዋጣት ስል በዚህ በዘመቻ አልተሳተፉኩም።
እንኳንስ የመናገር ነጻነት አይደለም ለእምነት ነጻነት ጀርባቸውን ሰጥተው የክስርቲያኑን የእምነት ተቋማት በቁጥጥር ስር አድርገው ሙስሊሙንም እንዲሁ እምነቱን ለመንጠቅ ቤት ለቤት ጭምር አሰሳ የገቡ ሰዎች ናቸው፡፡ የመናገር እና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ጋር በእጂጉ የተቆራኘ  የጋዜጣ ህትመት ማስቆም ሳያንሳቸው ዜጎችን –ያውም ኩሩ ሀገር ወዳድ ዜጎችን በሽብረተኛነት በመክሰስ ፣ብዙ እንግልት በማድረስ እና ክብራቸውን ጭምር ለማዋረድ በመሞከር ሌሌች ዜጎች የዜግነት ክብር እና ነጻነት  ጥያቄ ቅብጠት እና በህይወት መቀለድ እንዲመስላቸው በማድረግ የባርነትን እስተሳሰብ በደህንነት ተቋማት ፣በህግ ተቋማት እንዲሁም የማህበራዊ ድንዝዝነት በሚያስፋፉ ሌሎች ልማዶች የሚስፋፉበትን መንገድ በስውርም በግልጽም በማበረታታት  የባርነትን መስረት ለማጽናት ሌት ከቀን የሚሰሩ ለመሆናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ያለ ብዙ ምርምር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
የህገ-መንግስት ጉዳይ እና የዜጎች መብት ፋይዳ ሳይገባቸው ቀርቶ ነው እንዳይባል፤ ትግል ጀመርንም ጨረስንም የሚሉባቸውን ቀናቶች በብሔራዊ ደረጃ ጭምር እንዲከበርላቸው የሚፈልጉ ናቸው። እንዲያውም ያለባቸውን የስነ-ልቦና ችግር ከሚያመላክቱ ነገሮች  እንደኛው ይሄው ነው። ህወሃት ስልሳ ሺህ  ሰው ሰዋበት የሚሉትን በዓላቸውን የሚያዳንቁትን እና ሰው እንዲያዳንቅላቸው የሚፈልጉትን ያህል ለኢትዮጵያ ነጻነት ከጎጠኝነት በጸዳ በንጹህ የሃገር ፍቅር ስሜት የወደቁ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖች ጉዳይ እንዲነሳም እንዲታወስም እይፈልጉም። ታሪኩ ሲነገር ያሳንሳቸዋላ!

የሃሳብ ነጻነት ወደሚያፈኑበት ጉዳይ ስመለስ -የሚያፍኑበት እና ሃሳብ እንደጦር የሚፈሩበት ጉዳይ ምንድን ነው የተባለ እንደሆነ መሳሪያ እንቆ የተኮፈሰ የፓለቲካ ስብዕናቸውን የሚያኮስስ ስለሚመስላቸው። እደፊኛ የሚነፉትን ፕሮፓጋንዳ የሚያስተነፍስ ስለሚመስላቸው። የሃሳብ ልውውጥ ላይ ያለ ስለት ስለሚያስፈራቸው። አንግበው ለተነሱት የትምክህት እና የበላይነት ግንባታ ዓላማ እንቅፋት እንደሆነ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ይመስለኛል። የእምነት ነጻነትም እስከመንጠቅ የሄዱበት ምክንያት ከፍራቻ ውጭ ሌላ ሊሆን አይችልም። የፍርሃት ገጹ ይለያያል።  የህወሃት መራሹ መንግስት ፍርሃት በአንድ በኩል በጥጋብ እና በማናለብኝነት የተከናነበ ይመስላል በሌላ በኩል ደሞ በልማት ዲስኩር ተከልሎ ከዲስኩሩ በስከጀርባ በምናቡ የሚስላቸውን “ጸረ-ልማት ሃይሎች” (ኢትዮጵያውያኖች እኮ ናቸው የኢትዮጵያ ልማት ጠላቶች?) እንደምክንያት እየተጠቀመ የአፈና የሚጧጡፍበት የሞራል ፈቃድ አብረውት ክሚሰሩት “እህት ድርጂቶች”  ይወስዳል፡፡ በህወሃት “የማይበገር ጀግንነት” ውስጥ ያለው እውነታ (‘ሪያሊቲ’) ሃሳብን በነጻነት የመግልጽ መብትን እስከመፍራት የሚያደርስ ፍርሃት ነው። የደህንነት ተቋማቱም እወቃቀር የሚሰማቸውን የፍርሃት ደረጃ ግምት ውስጥ ያስገባ ይመስላል።

ስለ ህወሃቶች እና ስለገነቡት የማፈኛ ተቋም የራሴም የሰዎችም ተሞክሮ አለኝ። ገና በልጂነት ባደኩባት የደሴ  ከተማ ፓሊስ(ህወሃት ለአፈና ተግባር ካሰለጠናቸው ውስጥ ነበር)   አንዱን ያለ እግባብ እያንገላታ ለማሰር ዱብ እንቅ ሲል (እንደዛ ይደረግ የነበረው ደሞ ለሃገሩ በብሄራዊ ውትድርና ዘምቶ የመጣ ዜጋ ነው-የገባው የሚመስለው የፖለቲካ ሁኔታ እንገቱን ባያስደፋው ኖሮ የዛን ለፍዳዳ ፖሊስ ጥርሱን የሚያራግፍ ጎበዝ ነበር። አውቀዋለሁ ) ነገሩ ከንክኖኝ ከፖሊሱ ጋር “የምን እደረገህ” ያደረገውም ነገር ካለ በስነ-ስርዐት ውሰደው የሚል ሙግት ውስጥ ገባሁ። ከዚያ በኋላ ፖሊሱ ልጁን ትቶ ወደኔ ዞረ። ዱላም ጀመረ። ታሳሪው እኔ ሆንኩ፡፡ እና ሂድ እልሄድም ውዝግብ ተጀመረ።  ጓደኛየ ታደሰ ባየ( ፌስ ቡክ ላይ አለ) በዛ በዝናብ ተንበርክኮ ሁሉ ለመነው ፓሊሱን፡፡ እኔ ደሞ እንኳን ልለምነው እንዴት ድንጋይ እንደሆነ በተጋጋሚ እነግረዋለሁ። የመምታት አቅሙን ተጠቅሞ ያ ሁሉ የፖሊስ ዱላ ወረደብኝ። በመጨረሻ ላለመታሰር ጨለማውን ምክንያት እድርገን ሁለታችንም አመለጥነው። የተመታሁት ብዙ እንደነበረ የገባኝ ግን በነገታው  መሄድ እቅቶኝ ቀኑን አልጋ ላይ ሳሳልፍ ነው።  ያኔ ተናድጄ ስለነበር ምንም አልተሰማኝም።   ሶስት ቀን ያህል ሳያስነክሰኝ አልቀረም።

ኮተቤ እያለሁ ደሞ ሮብ  ሮብ መብራት ይጠፋ ነበር። በዚያ ምክንያት ረቡዕ ማታ አካባቢ ጥናት የለም ። ወክ ነው የምናደርገው። ወደ ገደራ እየሄድን ስናወራ የነበረውን ከኋላ ይሰማ የነበረ አስቁሞን መታወቂያችንን ከጠየቀ በኋላ እዚያው እካባቢ ወደ ነበረ ፓሊስ ጣቢያ ተወስደን ተመዝግበን የሚጠይቁትን ጠይቀው ተመልሰናል።  ሌላ ጊዜ እንዲሁ አራት ኪሎ ላይ የከተማ አውቶብስ ይዞ የነበረ የትግሪኛ ተናጋሪ ሾፌር  በራሱ ስህተት እና ትክምህት ምክንያት ተሳፋሪውን ከአራት ኪሎ ይዞ ሚኒሊክ እካባቢ ወደነበረው ፓሊስ ጣቢያ ወሰደን። በትግሪኛ አወራ ከሰዎቹ ጋር። እኛ “ጥፋተኞች ሆንን።” የተማሪዎች ዲን ነው ጣልቃ ገብቶ ነገሩ ያለቀው።

የሌሎችን ተሞክሮ በሚመለከት እዚያው ያደኩባት ደሴ ከተማ ላይ በጠራራ ጸሃይ አፉን በደንብ ያልፈታ የህወሃት ታጣቂ እንድ ባዶ እጁን የነበረ ወጣት አሯሩጦ ከደረሰበት በኋላ ሰው እየተጯጯኽ የክላሹን አፈሙዝ ደረቱ  ላይ አድርጎ ተኩሶ ከገደለው በኋላ ክላሹን እንቆ እንደያዘ  ሲሄድ ያስቆመው ፓሊስ አልነበረም። ሌሎች ታጣቂዎችም ያሉት ነገር የለም። (በነገራችን ላይ ያኔ እስከማውቀው ድረስ የልጁ ገዳይ ለፍርድ እልቀረበም)

Screen Shot from my facebook home page
Screen Shot from my facebook home page

እንደዛ እይነቱ የህወሃት ጭራቅነት በርሃ ባልነበሩት ዘመድ እዝማዶቻቸው ላይ ተጋብቶ “ምክንያታዊ” በሚመስል ሁኔታ  ስለፍትህ በሚጮሁ ኢትዮጵያውያን የሚያሳዩትን ቅጥ ያጣ ንቀት ማየት እሁን የተጀመረው እይነት ዘመቻ በበታችነት ስሜት በሚናጥ ስብናቸው እና እስተሳሰባችው ላይ የበላይነት እና የገዠነት ካባ ከሚደርብላቸው በስተቀር ትርጉም ያለው ጩኽት ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። የማስጮህ ስሜት እንዲሰማቸው አልፈልግም። ዛሬ ፌስ ብክ ላይ እንዲህ ያለ ዘመቻ ባለበት ሰዐት እዚሁ ፌስ ቡክ ላይ እስክንድር ነጋን በሚመለክት የነዚሁ የህወሃት ወገን የሚመስሉ ሰዎች ያደረጉትን ምልልስ ለአብነት እንዲሆን ያህል ከ’ሆም ፔጂ ላይ ስክሪን ሾት’ ወስጃለሁ፡፡

ከዚያ ውጭ የህግ ስርኦት ያለበት ሃገር ቢሆን ኖሮ እንደ ዳንኤል ብርሃነ ያሉ የህወሃት ደጋፊዎች ሃገር ውስጥ ያለው የሃሳብ ሙግት በጸጥታ ሃይል እና በ”ፍትህ አካላት” እየታፈነ ባዶ ሆኖ ሙግታቸውን እና የሃሳብ ክርክራቸውን ከውጭ ሃገራት ሰዎች ጋር ሲያደርጉ ማየት የህወሃት ደጋፊዎች እና ዘመዶች ባይሆኑ ኖሮ ሊያስገርም ይችል ነበር።  ከታች በሊንክ ባስቀመጥኩት የዳንኤል ጽሁፍ የሂውማን ራይቱ ቤን ራውለንስ የእንግሊዝ መንግስት የዕርዳታ እሰጣጥ የሚተች የመጽሃፍ ሪቪው  አወጣ ብሎ  የእንግሊዝ መንግስት ትችት ሳይሆን ምስጋና ነው የሚገባው የሚል ጽህፍ አውጥቶ ብሎጉም ላይ ጭምር ለጥፎታል። የጽሁፉ ዓላማ ምን ነበር የሚለው ሌላ ጥያቄ ሆኖ መነሳት ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ እንደ ዳንኤል ያለው የህወሃት ፖለቲካ ደጋፊ ስለሆነ ብቻ ሃገር ቤት በሚታተሙም ራሱ በፈጠረውም ብሎግ ላይ የመጻፍ ነጻነት ሲሰጠው ሌሎች ዜጎች (ለምሳሌ የዞን ዘጠኝ ብሎገር አባላት) የሚታፈኑበት ምክንያት ከላይ የገለጽኩት ነው። እፈናውን ተቃውሞ የሚደረገውን ተቃውሞ ያልተቀላቀልኩበት ምክንያት የሚጨምርላቸውን -ተዋጋን እያሉ ለሚያወሩት ብቻ ሳይሆን ያኔ ልጆች ለነበሩት እና የደም ትስስር በሚመስል ምክንያት ብቻ እፈናን በምክንያታዊነት ለማስተባባል እና ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ለሚሞክሩትም ጭምር- ለትምክህታቸው  የሚጨምረላቸውን ሃሴት ላለመስጠት ነው።  የዳኤል ፓስት

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አምባገነናዊነት ሌላ ዓለም ከሚስተዋለው በመሰረታዊነት የሚለይ እንደሆነ እምኖ ተቀብሎ የሚደረገው ተቃውሞ የህወህትን እምባገነናዊ ባህሪ ግምት ውስጥ ያስገባ እና ህወሃቶች በመንፈስም በፖለቲካም የማይጠቀሙበት እና ትምክህት የማይጨምርላቸው መሆነ አለበት ብየ ስለማምን ነው፡፡  በሌላ አንጻር ደሞ የሚደረገው ዘመቻ መሬት ላይ ያለ እና ለህዝቡ ስነ-ልቦና እና አስተሳሰብ ቅርበት ያለው ፣ በቀላሉ የሚገባ ቢሆንም ጥሩ ነው። ምን ያህል ኢትዮጵያዊ ነው በፌስ ቡክ እና ትዊተር ላይ ያለው? ፌስ ቡክ ላይ ካለውስ የህወሃት ደጋፊ ከሆነው ውጭ ስለ ህወሃት መራሹ መንግስት አፈና እና ቅጥ ያጣ እምባገነናዊነት የማያውቀም ምን ያህሉ ነው? ለ “ዓለማቀፉ” ማህበረሰብ ነው እንዳይባል ለዚሁ አፈና ለሚያደርሰው መንግስት ትብብር እና ርዳታ የሚሰጡት እነዚሁ ወገኖች ናቸው። ዳንኤል የእንግሊዝን የእርዳታ አሰጣጥ በመደገፍ የእንግሊዝን መንግስት የሚከላከል ጽሁፍ መጻፍ ደረጃ ላይ የደረሰበት ”የዲፕሎማሲ” ልምምድ ሳይሆን የፖለቲካ ትስስርንም ጭምር የሚያመላክት ይመስለኛል። ለሃወሃት የጥጸጥታ ሃይሎች ስልጠና እና ሎጂስቲክ የሚያቀርበው ማን ነው? ብዙዎቹ የህወሃት ፖሊሲዎች በርግጥ ከህወህት ብቻ የመነጩ ናቸው? “የመለስ” ራዕይን ጨምሮ?
______________________________
ይህ ጽሁፍ በመጀመሪያ ቦርከና ብሎግ ላይ የወጣ ነው። ለጸሃፊው በግል አስተያየት ለመስጠት በኢሜይል dbirku@gmail.com  ወይንም በትዊተር @dimetrosላይ ማግኘት ይቻላል
advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here