Saturday, June 15, 2024
HomeEthiopian Newsሽማግሌዎች ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን አነጋገሩ፤ አስመራጩ መግለጫ ሰጠ

ሽማግሌዎች ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን አነጋገሩ፤ አስመራጩ መግለጫ ሰጠ

(ደጀ ሰላም፤ የካቲት 18/2005 ዓ.ም፤ ፌብሩዋሪ 25/2013)፦ ቅዳሜ የካቲት 16/2005 ዓ.ም ቀርበው በአብዛኛው የቅ/ሲኖዶስ አባላት ይሁንታ አግኝተዋል የተባሉት አስምት ሊቃነ ጳጳሳት በመጪው ሐሙስ ለሚካሄደው የፓትርያርክ ምርጫ ያለፉ መሆናቸውን አስመራጭ ኮሚቴው ዛሬ በጋዜጣዊ መግለጫው ገልጿል።

ከፍተኛ ታቃውሞና የከረረ ተግሳጽ የደረሰባቸውን አቡነ ማትያስ ዘኢየሩሳሌምን ጨምሮ ሌሎቹ አራት አባቶች የተካተቱበት የአስመራጭ ኮሚቴው ጥቆማ ለቅ/ሲኖዶስ ቢቀርብም ተጨማሪም ተቀናሽም ሳይደረግበት መጽደቁ ዛሬ ይፋ ሆኗል። በዚህም መሠረት ሐሙስ በሚደረገው ምርጫ ከፍተኛ ቁጥር የሚያገኘው ተወዳዳሪ ስድስተኛ ፓትርያርክ ተብሎ ይሾማል ማለት ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ስድስተኛውን ፓትርያርክ ምርጫ ተከትሎ ሰሞኑን የተፈጠረውን  አለመግባባት ለመፍታት የአስመራጭ  ኮሚቴው  ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ከሌሎች ብፁዐን ሊቃነ  ጳጳሳት ጋር በመሆን  የምርጫውን  ሒደት የታቃወሙትን ብጹዕ አቡነ ሳሙኤልን ማነጋገሩን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ለደጀ ሰላም ገልጸዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ለማነጋገር ያደረጉት ሙከራም በብፁዕነታቸው በአካባቢው አለመኖር ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱን እነዚሁ ውስጥ አዋቂዎች አስረድተዋል።
በምርጫው ላይ ያነሱትን የዘገየ ነው የተባለ ተቃውሞ እንዲያቀዘቅዙ ለማግባባትና ምርጫው በተጀመረው መሠረት እንዲጠናቀቅ ለማሸማገል የተላኩት አባቶች የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሐሳብ ለማስቀየር የቻሉ አይመስልም። ብጹዕነታቸው በተቃውሟቸው በመግፋት በቅዳሜ የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ያንጸባረቁትን ሐሳብ ደግመውላቸዋል ተብሏል። እንዲያውም አስመራጩ ኮሚቴ መግለጫውን ካወጣ እነርሱም (አቡነ ሳሙኤልና አቡነ አብርሃም?) በበኩላቸው ተቃውሟቸውን በመግለጫ ይፋ እንደሚያደርጉ ለሽማግሌዎቹ አስረድተዋቸዋል ሲሉ ምንጮቻችን ያብራራሉ። ይሁን እንጂ አስመራጭ ኮሚቴው በያዘው ሐሳብ በመግፋት በቅዳሜው ስብሰባ ያስጸደቃቸውን አመስት አባቶች እና አጠቃለይ የጥቆማውን ሒደት በመግለጽ ዋነኛውን ክፍል የምርጫ ጉዞ አጠናቋል።
ይኸው ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት በዛሬው ዕለት እንደተገለጸው በነዚህ ሦስት ቀናት ብፁዓን አባቶችን ጨምሮ ምእመኑ በሙሉ ጉዳዩን በጾም በጸሎት እንዲያስብና የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲጠይቅ አስመራጭ ኮሚቴው አሳስቧል። ምርጫው ካርድ በመጣል እንጂ እንደ አበው ሥርዓት ዕጣ በማውጣት እንዳልሆነ፣ ይህ ሐሳብ በምርጫ ደንብ ማጽደቁ ወቅት ውድቅ እንደተደረገ፣ ይህንን ሐሳብ ያቀረቡ አባቶች ተሰሚነት እንዳላገኙ ይልቁንም “ምርጫው ልክ በመንግሥት እንደሚደረገው በካርድ ይሁን” የሚል ሐሳብ እንደተንጸባረቀ መዘገቡ ይታወሳል። በርግጥ በዕጣ ቢሆንና ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቁ ቢባል እንዴት ባማረ፣ እንዴትስ ሃይማኖታዊ በመሰለ ነበር። የመንግሥት እጅ ለሚዋኝበት፣ ፈቃደ ቤተ መንግሥት ፈጻሚ ሞገስ ለሚያገኝበት፣ ሁሉም ወገን “አባቴ ነው፣ ይደልዎ፣ መመረጥ ይገባዋል” ለማይልበት ምርጫ በጾምና በጸሎት አስቡን ማለት ሰውን ለመፈታተን እና ሃይማኖታዊ መስሎ ለመታት ካልሆነ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነው።
ከዚህ አስቀድመን በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘኢየሩሳሌም ፓትርያርክ እንዲሆኑ የመንግሥት ዓላማ መሆኑን ምንጮችን ጠቅሰን ዘግበን ነበር። በወቅቱ በግልም በሚዲያ ደረጃም ይህ የደጀ ሰላም ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን ለመጠቆም ብዙ መልእክቶች ደርሰውን ነበር። ጊዜው ሲደርስ እየሆነ ያለው ይኸው ይመስላል።
ደጀ ሰላም ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ላይ ተቃውሞ የላትም። ለሃይማኖታቸው ተቆርቋሪ፣ በብዙ ሰዎችም ዘንድ የመሰገኑ ንፁህ መነኩሴ መሆናቸውን የሚሰጠውን ምስክርነት ደጀ ሰላምም ታውቃለች። የምርጫው ሒደት ትክክል አይደለም ማለት አቡነ ማቲያስ መጥፎ ናቸው እንደማለት መቆጠር የለበትም። ሌለቾዩን ብፁዓን አባቶች አሠራራቸውን በየጊዜው እያየን ሊመሰገኑ ሲገባቸው የምናመሰግናቸው፣ ትክክል አይደሉም ብለን በምናስብበት ወቅት የምንቃወማቸው በዚያ ወቅት ባራመዱት ዓላማ ምክንያት ብቻ ነው።
ከዚህ በፊት አቡነ ሳሙኤልንና አቡነ አብርሃምን ታደንቁ ነበር አሁን ለምን የያዙትን አቋም አልተቀበላችሁም ለሚሉን የምንሰጠው መልስ ይኼው ነው። አቡነ ሳሙኤል በተለይ የቀድሞው ፓትርያርክ ያራምዱት በነበረው አውዳሚ እንቅስቃሴ ላይ በነበራቸው ተቃውሞ፣ ሙስናን ለማጥፋት ባደረጉት ትግል እኛም ደግፈናቸዋል። አሁንም ለዚያ እንቅስቃሴያቸው ያለን አክብሮት ትልቅ ነው። አቡነ አብርሃምም አሜሪካ በነበሩበት ወቅት ለሠጡት ትልቅ አገልግሎት ስናመሰግናቸው ቆይተናል፣ አሁንም እናመሰግናቸዋለን። ሁለቱም አባቶች ዕርቀ ሰላሙን በተመለከተ ባራዱት አቋም ደግሞ እንኮንናቸዋለን። ተሳስተዋል እንላለን።
ከዚህ ባሻገር ምርጫውን በተመለከተ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳለበት መግለጻቸው ትክክል ነው። ስንቃወመው የነበረው፣ አሁንም የምንቃወመው ተግባር ነው። በዕጣ መሆኑን ስንመኝበት ከነበረው ምክንያት አንዱ ለእግዚአብሔር ፈቃድ የተመቸ ሥራ መሥራት እንዲቻል ነበር። አልሆነም። በካርድ የሚመረጠው አባት ማንም ይሁን ማን “የመንግሥት ወገን” ተደርጎ መቆጠሩ አይቀርለትም። ያሳዝናል።
advertisment

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here